የአውሮፓው ፍርድ ቤት ለደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ካስተር ሴሜኒያ ያደላ ውሳኔ አስተላለፈ

ካስተር ሴሜኒያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በሴት አትሌቶች ውስጥ መገኘት ካለበት የቴስቴስትሮን መጠን ጋር በተያያዘ የሁለት ጊዜ የ800 ሜትር የኦሊምፒክ ወርቅ አሸናፊዋ ካስተር ሴሜኒያን ደግፎ ውሳኔ አስተላለፈ።

በተለየ የጾታ ዕድገት የተወለደችው የ32 ዓመቷ ደቡብ አፍሪካዊት አትሌት፣ በሰውነቷ ውስጥ ያለውን የቴስቴስትሮን መጠን የሚቀንስ መድኃኒት ሳትወስድ እንዳትወዳደር በዓለም አትሌቲክስ ታግዳ ነበር።

የሦስት ጊዜ የ800 ሜትር የዓለም ሻምፒዮን እና የሁለት ጊዜ የ1500 ሜትር የኮመን ዌልዝ ውድድር አሸናፊዋ ሴሜኒያ፣ በሰውነቷ ውስጥ ካለው የቴስቴስትሮን መጠን ጋር በተያያዘ ከዓለም አትሌቲክስ ጋር በፍርድ ቤት ስትከራከር ቆይታለች።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት በጉዳዩ ላይ ባስተላለፈው ውሳኔ ሴሜኒያን የተመለከተው የዓለም አትሌቲክስ የተለየ ጾታ ዕድገት መመሪያ እና አፈጻጸም የመድልዎ ምንጭ ነው በማለት መመሪያው ከአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ኮንቬሽን ጋር የሚጣጣም አይደለም ብሏል።

ካስተር ሴሜኒያ በሰውነቷ ውስጥ ያለው የቴስቴስትሮን መጠን እንዲቀንስ መድኃኒት እንድትወስድ የተወሰነው እአአ 2018 ላይ ነበር። አትሌቷ ይህን ውሳኔ ለመቀልበስ ያደረገቻቸው ሁለት የፍርድ ቤት ክርክሮች ውድቅ ተደርገውባት ነበር።

ይሁን እንጂ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ውሳኔም የስፖርት አስተዳዳሪ አካላትን የተመለከተ ሳይሆን የስዊዘርላንድ መንግሥት የሴሜኒያን መብቶች አልጠበቀም የሚል እና ከሦስት ዓመት በፊት የስዊዘርላንድ ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን የተመለከተ ነው።

የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ዛሬ ባስተላለፈው ውሳኔ ከሦስት ዓመታት በፊት የስፖርት ገላጋይ ፍርድ ቤት የዓለም አትሌቲክስ ውሳኔን ካጸና በኋላ ሴሜኒያ ይግባኝ ለማለት ጉዳዩን ወደ የስዊዝ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ስትወስድ፣ የስዊዘርላንድ መንግሥት የአትሌቷን መብት አልጠበቀም ብሏል።

አትሌቷ መድልዎ ተፈጽሞብኛል የሚል ቅሬታ እያቀረበችው ቅሬታዋ በአግባቡ አልተመረመረም ብሏል የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ባስተላለፈው ውሳኔ።

የዓለም አትሌቲክስ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ካስተላለፈው ውሳኔ ጋር እንደማይስማማ ገልጾ፣ ጉዳዩ “የመጨረሻ እና ቁርጥ ያለ ውሳኔ እንዲሰጠው” የስዊዘርላንድ መንግሥት ወደ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ችሎት እንዲመራው ጠይቋል።

የዓለም አቀትሌቲክስ በቅርቡ የቴስቴስትሮን መጠናቸው ከፍ ያሉ አትሌቶች ለውድድር ብቁ የሚሆኑት ከውድድሩ ከስድስት ወራት በፊት የሆርሞን መጠን የሚቀንስ ሕክምና መውሰድ አለባቸው ይላል።

ካስተር ሴሜኒያ ቴስቴስትሮን የሚቀንሱ መድኃኒቶችን ብትወስድ ለጤናዋ አደጋ እንደሆነ እና እርሷን ጨምሮ የቴስቴስትሮን መጠናቸው ከፍ ያሉ አትሌቶች በተፈጥሯዊ አቅማቸው እንዳይወዳደሩ እክል እንደሆነባቸው ስትከራከር ቆይታለች።

የዓለም አትሌቲክስ ውሳኔን ተከትሎ ካስተር ሴሜኒያ እአአ 2021 ከተካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ውጪ ተደርጋለች።