በስፓይደር ማን ፊልሞቹ የሚታወቀው ቶም ሆላንድ የአልኮል ሱስ ጥገኛ ሆኜ ነበር አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በስፓይደር ማን ፊልሞች በስፋት የሚታወቀው ተዋናይ ቶም ሆላንድ በከፍተኛ የአልኮል መጠጥ ሱስ ውስጥ ተዘፍቆ እንደነበር ተናገረ።
የአልኮል መጠጥ ቁራኛ ሆኜ ነበር የሚለው ቶም አልኮል መጠጣት ማቆሜ “እስካሁን ካደረኩት ነገር ሁሉ ትልቁ ነገር ነው” ሲል ኦን ፐርፐስ ለተባለ ፖድ ካስት ተናግሯል።
ቶም የአልኮም መጠጥ ሱሱ ተጽእኖ ሲበረታበት ለአንድ ወር ያህል አልኮል አልጠጣም ሲል ባለፈው ታኅሣሥ ወር ለራሱ ቃል መግባቱን ይናገራል።
ለአንድ ወር አልጠጣም ብሎ የተነሳው ቶም በወቅቱ “ሳስብ የነበረው ስለ መጠጥ ብቻ ነበር። እጅግ በጣም አስፈርቶኝ ነበር። ‘ትንሽ ብቻ ልቅመስ’ እያልኩ ነበር የማስበው” ይላል።
ቶም የአልኮል ቁራኛ መሆኑን ሲረዳ ለአንድ ወር አልጠጣም ያለውን ወደ ሁለተኛ ወር ከፍ አደረገው። ነገር ግን በዙሪያው ካለው ሁኔታ አንጻር ከአልኮል መላቀቅ ቀላል ሆኖ አላገኘውም።
“ያለ አልኮል ማኅበራዊ ሕይወት ያለ አልመስል ነበር። ወደ መዝናኛ ቦታ ሄጄ ለስላሳ መጠጣት እንደማልችል ይሰማኝ ነበር። ወደ የእራት ግብዣ መሄድ እንደማልችል ነበር የሚሰማኝ። በጣም በጣም ተቸግሬ ነበር” ብሏል ቶም የሁለት ወራት ከአልኮል ነጻ የመሆን ጉዞውን ሲያስረዳ።
“ከዚያ እራሴን መጠየቅ ጀመርኩ። ለምን? ለምንድነው እራሴን የአልኮል ተገዢ ያደረኩት? አልኮል ከመጠጣት ሐሳብ እራሴን መለየት ያቃተኝ ለምንድነው?”
ቶም ሁለት ወራት ሳይሆን ለስድስት ወራት የአልኮል መጠጥ ወደ አፌ አይደርስም ብሎ ወሰነ። ይህንንም በግንቦት ወር መጨረሻ የ27ኛ ዓመት ልደቱ ላይ ማሳካት ቻለ።
በዚህ ጊዜ ይላል ቶም፤ “በሕይወቴ ከፍተኛ ደስታ የተሰማኝ ጊዜ ላይ ነበርኩ” በማለት ስኬቱን ይገልጻል።
“በተሻለ ሁኔታ መተኛት ቻልኩ። ችግር ሲያጋጥመኝ የተሻለ መፍትሄ መስጠት ጀመርኩት። ሥራ ቦታ ላይ ያበሳጩ የነበሩ ነገሮችን አምኜ መቀበል ቻልኩ። በጣም የተሻለ የአእምሮ ሰላም አገኘሁ። ጤነኝነት ይሰማኛል” በማለት ያገኘውን ጥምቅ ይገልጻል።
“በእርግጠኝነት የአልኮል ሱሰኛ ነበርኩ። ይህን ለማለት አላፍረም” የሚለው የስፓይደር ማን ፊልሞች ኮከቡ፤ እራሱን ከአልኮል ለማራቅ ሲወስን ታዳሚ ከነበረበት የራግቢ ስፖርት ተመልካቾች ስብስብም መራቅ ግዴታ ነበር።
የዚያ ስብስብ አባል መሆን “ምን ያህል አልኮም መጠጣት ትችላለህ ማለት ነው” የሚለው ቶም፣ ከራሱ አልፎ ወላጅ እናቱም እራሷን ከአልኮል እንድታርቅ አርዓያ እንደሆናት ይገልጻል።
“በጣም ደስተኛ ናት። በጣም አስደሳች ነገር ነው” በማለት ጉዞውን ይገልጻል።
እንግሊዛዊው ቶም ሆላንድ - ስፓይደር ማን፡ ሆምካሚንግ፣ ስፓይደር-ማን፡ ፋር ፍሮም ሆም፣ ካፒቴን አሜሪካ፣ ሲቪል ዎር እንዲሁም ዘ ኢምፖስብል በሚሉት ፊልሞቹ ዝናን አትርፏል።












