የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት በኢትዮጵያ ያቋረጠውን እርዳታ ለስደተኞች ብቻ እንደሚጀምር አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ተራድ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) በኢትዮጵያ አቋርጦት ከቆየው የምግብ እርዳታ ውስጥ ለስደተኞች የሚሰጠውን ድጋፍ መልሶ ለመጀመር መወሰኑን አስታወቀ።
ይህ የምግብ እርዳታ አቅርቦትን መልሶ ለመጀመር በዩኤስኤአይዲ የተደረሰው ውሳኔ ሁሉንም የእርዳታ ፈላጊዎች የሚመለከት ሳይሆን፣ በአገሪቱ ላሉት ስደተኞች የሚደረገውን እርዳታ ብቻ መልሶ በመጀመር ላይ ያተኮረ ነው።
በኢትዮጵያ ለረጅም ዓመታት ሰብአዊ እርዳታዎችን በማቅረብ ቀዳሚ የሆነው የአሜሪካው ተራድኦ ድርጅት በአገሪቱ የሚያሰጠውን የእርዳታ አቅርቦት መጀመሪያ ያቆረጠው በትግራይ ክልል ውስጥ ነበር። በማስከተልም ከወራት በፊት በመላው አገሪቱ የሚያካሂደውን የምግብ እርዳታ አቋርጧል።
ከዩኤስኤአይዲ በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራምም በተመሳሳይ የእርዳታ አቅርቦቱን ያቆመ ሲሆን፣ ሁለቱም በአገሪቱ የሚቀርበው የምግብ እርዳታ በከፍተኛ መጠን እና በተቀናጀ ሁኔታ ከታቀደለት አላማ ውጪ ጥቅም ላይ ውለዋል ሲሉ መክሰሳቸው ይታወሳል።
በአገሪቱ እየተካሄዱ ባሉ ግጭቶች እና በድርቅ ምክንያት እርዳታን የሚሹ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚገኙ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም የእርዳታ አቅርቦቱ እንዲቋረጥ መደረጉ ተቀባይነት የሌለው ፖለቲካዊ እርምጃ ነው ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል።
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ባወጣው መግለጫ አሁን እርዳታ መልሶ ለመጀመር መወሰኑን ያሳውቅ እንጂ፤ አቅርቦቱ ለስደተኞች ብቻ የሚቀርበውን ብቻ የሚመለከት መሆኑን ገልጿል።
እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው የኢትዮጵያ መንግሥት እና አጋሮቹ የስደተኞች የምግብ እርዳታ አቅርቦት መዋቅር ላይ ለውጦችን በማድረጋቸው መሆኑን ጠቅሶ፣ “የኢትዮጵያ መንግሥት የስደተኞች የምግብ እርዳታን የማጓጓዝ፣ የማከማቸት እና የማሰራጨት ኃላፊነትን ለሌሎች አጋሮች በማስተላለፉ” መሆኑንም አመልክቷል።
በእርዳታ ስርጭቱ ላይ የተደረገው ለውጥ አቅርቦቶችን በትክክል ለተጠቃሚዎች መድረሳቸውን ለመቆጣጠር በሚያስችል ሁኔታ መሆኑ ተገልጿል።
ዩኤስኤአይዲ ለስደተኞች የሚቀርበው እርዳታ እንደሚጀመር ባሰወቀበት መግለጫው፣ “የምግብ እርዳታ በሚያስፈልግባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ድጋፉ ለታለመላቸው ተጠቃሚዎች እንደሚደርስ ማረጋገጫ አስክናገኝ ድረስ ተቋርጦ ይቆያል” ብሏል።
የምግብ እርዳታው ቢቋረጥም የጤና እና የአልሚ ምግቦች እርዳታዎችን ጨምሮ ሌሎች የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ አቅርቦቶች ግን ይቀጥላሉ ተብሏል።
በኢትዮጵያ የሰብአዊ እርዳታ ከሚያቀርቡ ድርጅቶች መካከል ዋነኛ የሆነው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በአብዛኛው በምግብ እርዳታ የቀረበ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ድጋፍ ለአገሪቱ አድርጓል።
በድርቅ እና በጦርነት ምክንያት ለችግር የተጋለጡ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ የምግብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት መግለጻቸው ይታወቃል።












