ጃማይካ ውስጥ ከሃሺሽ የተሠራ ከረሜላ የበሉ ከ60 በላይ ተማሪዎች ሆስፒታል ገቡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ጃማይካ ውስጥ ሃሺሽ (ካናቢስ) ያለበት ከረሜላ የበሉ ከ60 በላይ ልጆች ሆስፒታል መግባታቸውን የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስትር አስታወቁ።
ሚኒስትሯ ፋይፋል ዊሊያምስ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ (ትዊተር) ላይ እንዳሰፈሩት፣ ልጆቹ ከጃማይካ ዋና ከተማ ኪንግስተን 80 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው።
ሚኒስትሯ እንዳሉት ልጆቹ ከረሜላውን ከበሉ በኋላ ማስታወክ እና መቃዠት አጋጥሟቸው ነበር።
ነገር ግን ከተማሪዎቹ መካከል አንዳቸውም ከባድ የጤና ችግር አልተከሰተባቸውም።
“ሐኪሞች እና ዶክተሮች ተማሪዎቹ እንዲሻላቸው የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ ነው” ብለዋል ሚኒስትር ዊሊያምስ፣ ጨምረውም አብዛኞቹ ተማሪዎች በሐኪም ቤት ውስጥ በደም ስር የሚሰጥ ጉሉኮስ ተደርጎላቸዋል።
“ከተማሪዎቹ መካከል አንድ ትንሽ ልጅ አንዲት ከረሜላ ብቻ ነው የበላሁት ብሏል። ይህም ከረሜላው ምን ያህል ጠንካራ መሆኑን ያሳያል” በማለት በተማሪዎቹ ላይ የገጠመውን ችግር “አደጋ” ብለውታል ሚኒስትሯ።
የአካባቢው መገናኛ ብዙኃን ልጆቹ ሚኒስትሯ ካሉት ውጪ ካለ ትምህርት ቤት የመጡ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ዕድሜያቸውም በሰባት እና በ12 ዓመት መካከል የሚገመት ነው ብለዋል።
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር “ጃማይካ ኦብሰርቨር” ለተባለ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት፣ ከረሜላዎቹን ለተማሪዎቹ የሸጠው አንድ ቸርቻሪ መሆኑን አመልክተዋል።
ትምህርት ቤቱ ያለበት አካባቢ ፖሊስ ከረሜላዎቹን ለተማሪዎቹ የሸጠው ግለሰብ ወይም መረጃ ያለው ነዋሪ ለፖሊስ እንዲያመለክት ጥሪ አቅርቧል።
ሚኒስትሯ የከረሜላዎቹን ማሸጊያ ፎቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋሩ ሲሆን፣ ከረሜላዎቹ ለሕጻናት የማይሰጡ መሆናቸው ተጽፎበታል።
ከረሜላው የተመረተው ሃሽሽ (ካናቢስ) በሕግ የተፈቀደ በሆነባት የአሜሪካ ግዛት ካሊፎርኒያ ውስጥ ሲሆን፣ በአሜሪካ የመድኃኒት አስተዳደር ፈቃድ ያገኘ ነው።
ከስምንት ዓመት በፊት ጃማይካ ማሪዋና ተብሎ የሚታወቀውን የካናቢስ እጽ በተወሰነ መጠን ይዞ መገኘትን በሕግ ፈቅዳለች።
ነገር ግን የአገሪቱ የጤና ሚኒስትር ክሪስቶፈር ቱፍተን እንደተናገሩት የጃማይካ መንግሥት እንደከረሜላ የተዘጋጀው እጽ ወደ አገሩ እንዲገባ አልፈቀደም።
ይህ ሁኔታ ጃማይካ ውስጥ የተከሰተው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ 90 የሚደርሱ ልጆች እጽ የተቀባ ኬክ ከጎዳና ላይ ቸርቻሪ ገዝተው በመብላታቸው መተመማቸው ከተነገረ ከሳምንት በኋላ ነው።












