ኬንያ በሄይቲ ሥርዓተ አልበኝነትን ለመቆጣጠር ፖሊሶቿን ለማሰማራት ከተመድ ፍቃድ አገኘች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኬንያ በካሪቢያኗ አገር ሄይቲ ያለውን ሥርዓተ አልበኝነት ለመቆጣጠር ፖሊሶቿን ለማሰማራት ያቀረበችው ጥያቄ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፈቃድ ተሰጠው።
የሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር በተደራጁ ወንጀሎች አገራቸው እየተናወጠች መሆኗን ጠቅሰው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ እንዲያደርግ በጠየቁት መሰረት ኬንያ ዓለም አቀፍ የደኅንነት ኃይል ለመምራት ጥያቄ አቅርባ ነበር።
ሄይቲ ለበርካታ ዓመታት በተደራጁ ወሮበላ ቡድኖች ሁከት ስትፈተን ብትቆይም የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ጆቬኔል ሞይስ ከተገደሉ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከቁጥጥሯ ውጭ ሆኗል።
እነዚህ ቡድኖች ሰፊውን የአገሪቱን ክፍል በመቆጣጠር በነዋሪዎች ላይ ሽብር እየፈጠሩ ነው።
እንዲሁም በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችንም ገድለዋል ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ወሮበሎችን ትጥቅ ለማስፈታት እና ሥርዓቱንም ወደነበረበት ለመመለስ “ጠንካራ የኃይል እርምጃ” እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በሄይቲ የሚሰማራውን የኃይል ተልዕኮ ለአንድ ዓመት ያጸደቀ ሲሆን ከዘጠኝ ወራት በኋላም ይገመገማል።
በሄይቲ የሚሰማራው ኃይል የጋራ የደኅንነት ሥራዎችን ያከናውናል። ከሄይቲ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት በቁጥጥር ሥር የሚውሉ አካላትንም ለማሰር ሥልጣን ተሰጥቶታል።
በዚህም አገሪቷ ምርጫ ለማካሄድ ሁኔታዎችን ያመቻችላታል። ሄይቲ ከአውሮፓውያኑ 2016 ጀምሮ ምርጫ አላደረገችም።
የሄይቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን ቪክቶር ጄነስ ውሳኔውን “ለረጅም ጊዜ በስቃይ ለነበሩ ሰዎች የተስፋ ጭላንጭል የፈነጠቀ” ሲሉም ጠርተውታል።
ኬንያ በዚህ ተልዕኮ 1 ሺህ ፖሊሶችን በሄይቲ እንደምታሰማራ ተናግራለች። ለመጀመሪያ ጊዜ ሃሳቡ በቀረበበት ከጥቂት ወራት በፊት የኬንያ ባለስልጣናት የሚያሰማሯቸው ፖሊሶች የመንግሥት ሕንጻዎችን እና መሰረተ ልማቶችን ይጠብቃሉ ብለው ነበር።
ነገር ግን ኬንያ ሁኔታውን ለመገምገም አጣሪ ልዑካንን ከላከች በኋላ እቅዱ ተቀይሯል።
ኬንያ በሄይቲ የምታሰማራቸው ፖሊሶች የተደራጁ ቡድኖችን ትጥቅ የሚያስፈታ፣ ሰላማዊ ዜጎችን የሚጠብቅ እንዲሁም በአገሪቱ ሰላም፣ ደኅንነት እና ጸጥታን በማምጣቱ ረገድ ሚና የሚጫወቱ ይሆናሉ።
የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልፍሬድ ሙቱዋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት አገራቸው ሄይቲ ጠቃሚ መሰረተ ልማቶችን መልሳ እንድትገነባ እንዲሁም የተረጋጋ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት እንድትመሰርት ማገዝ ትፈልጋለች።












