የዛሬ 10 ዓመት በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ የደረሰው የላምፔዱዛው እልቂት

ከ10 ዓመት በፊት ከሊቢያ የተነሳችው ጀልባ በጣልያኗ ደሴት ላምፔዱሳ ሰምጣ 366 ስደተኞች ሞተዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ልክ የዛሬ 10 ዓመት፣ በዕለተ ሐሙስ እኤአ ጥቅምት 03 ቀን 2013፣ 368 ኤርትራውያን ስደተኞች በላምፔዱዛ የባሕር ዳርቻ በጀልባ አደጋ ሞቱ።

ሟቾቹ ከቀናት በፊት ጉዞ መጀመራቸውን በስልክ የነገሯቸው ዘመዶቻቸው እና ጓደኞቻቸው “በሰላም ገብተናል” የሚል ምሥራች እየጠበቁ ሳለ ነበር በመላው ዓለም የመገናኛ ብዙኃን ይህ አስደንጋጭ ዜና ተሰማው።

ከላምፔዱዛ የባሕር ዳርቻ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የደረሰው አደጋ፣ በካሜራ እና በሕዝቡ ዐይን በመታየቱ ቢቢሲን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በመቶዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በአስከፊ አደጋ ማለቃቸውን ዘገቡ።

ከአደጋው በሕይወት መትረፍ የቻሉትን ኤርትራውያን አድሃኖም ፍትዊ፣ እስክንድር ገብሪት እና አብርሃለይ አማረ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሱታል።

ኤርትራውያን በላምፔዱዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሦስቱም ስደተኞች ጣልያን ላምፔዱዛ የምታደርሳቸውን ጀልባ ከመሳፈራቸው በፊት አገራቸውን ጥለው፣ ቤተሰቦቻቸውን ተሰናብተው መጀመሪያ የተሰባሰቡት ሱዳን ነበር።

አሰባሳቢዎቻቸው ደግሞ ከእያንዳንዳቸው ጠቀም ያለ ገንዘብ የተቀበሉ ሕገ ወጥ ደላሎች ናቸው።

በሰሃራ በረሃ ላይ ካደረጉት አስቸጋሪ ጉዞ በኋላ፣ ከ500 በላይ ስደተኞችን ባሳፈረው ጀልባ የሜዲትራንያንን ባሕር አቋርጠው፣ ሰላምና ፀጥታ በሰፈነባቸው የአውሮፓ አገራት ሕይወታቸውን ለመለወጥ አቅደው ነበር።

ምንም እንኳን ሁሉም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ምክንያቶች ቢኖራቸውም፣ እያንዳንዱ ደግሞ የራሱ የሆነ ልዩ ታሪክ አለው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በእርግጥ ከሊቢያ የባሕር ዳርቻ ላምፔዱዛ ለመድረስ የሁለት ቀን የባሕር ላይ መንገድ ሲሆን፣ ፀሎት እና ዕድል ካልታከለበት ባሕሩ ውጦ የሚያስቀር ሰፊ መቃብር ነው።

እነ አድሃኖም ወደ ላምፔዱዛ ጉዞ ከመጀመራቸው በፊት፣ ዋዜማው ላይ በርካቶች በተስፋ እና በጭንቀት ተሞልተው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ጣልያን ባሕር ዳርቻ የምታደርሳቸው ጀልባ እስክትሞላ ድረስ “መዝርዓ” እየተባሉ በሚጠሩ የባሕር ዳርቻ መንደሮች ላይ ተሰባስበው ነበር።

በርከት ያለ ተሳፋሪ ከተሰባሰበ በኋላ ያቺ ተለቅ ያለች ጀልባ ወደ ባሕር ዳርቻው እየተጠጋች መጣች።

የሊቢያ የባሕር ጠረፍ ጠባቂዎች እንዳያገኙዋቸው፤ በቶዮታ መኪና እያስጠጉ ነበር የሚያሳፍሩዋቸው።

እነ አድሐኖም ወደ ጣልያን የምታደርሳቸውን የአሳ አጥማጆች ጀልባ ከመሳፈራቸው በፊት ወደ ፈጣርያቸው ፀሎት ማድረሳቸውን ያስታውሳሉ።

በሜድትራኒያን ባሕር ሞት በሽ ነው። ስደተኞች በሰላም አውሮፓ ተሻገሩ ብቻ ሳይሆን ጀልባው ተገልብጦ ሰጥመው ሞቱ የሚል ወሬ በሁሉም አፍ ላይ ቤቱን ሰርቷል።

ይህንን የሚያውቀው አብርሃለይ ፍርሃት አድሮበት እንደነበር ያስታውሳል። ፍርሃቱ ግን ተስፋ ያረገዘ ነው።

“ጉዞ የምትጀምርበት ዋዜማ ላይ ተስፋ እና ፍርሃት ይፈራረቅብሃል። በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ ብዙ ጊዜ አደጋዎች እንደሚኖሩ እናውቃለን፤ ስለዚህ በአንድ በኩል ፈርተንም ቢሆን በሰላም እንድንገባ እንመኛለን” ይላል አብርሃለይ በወቅቱ የነበረውን እያስታወሰ።

አብርሃለይ ሁሉንም ነገር ለፈጣሪ ሰጥቷል። አምላኩን ደጋግሞ እየጠራ በሰላም ደረቅ መሬት ላይ እንዲደርሱ ይጸልይ ነበር።

አብርሃለይ 500 ያህል ስደተኞችን እንደያዘች በተገመተችው ጀልባ ላይ የተሳፈረው በዚህ ስሜት ነው።

እስክንድር በበኩሉ “በፈጣሪ ኃይል ሁሉንም ነገር እንወጣዋለን” ብሎ ያምን እንደነበር ያስታውሳል።

ጀልባዋ ከአፍ እስከ ገደፏ በርካታ ሰዎች ጭና ትንሽ ከተንቀሳቀሰች በኋላ ካፕቴኑ ደላሎችን ጠርቶ ጀልባዋ ሚዛን ስለሳተች የተወሰኑትን እንዲቀንሱ ጠየቃቸው።

ደላሎቹም ባልተወለደ አንጀታቸው በዱላ እየቀጠቀጡ እና እየገረፉ 26 ሰዎችን አውርደው በትናንሽ ጀልባዎች ወደ ባሕር ዳርቻው መለሷቸው።

ወደ ላምፔዱዛ የተሳፈሩትን 518 ተጓዦችን የሚያመሳስላቸው በሰላም ጣልያን ገብተው ለመማር፣ ቤተሰብ ለማፍራት እና ሕይወታቸውን ለመለወጥ ማለማቸው ነው።

ሁሉም በየፊናው ወደ አምላኩ መፀለዩም፣ በአሳ አጥማጆች ጀልባ ላይ ተሳፍረው የሚጓዙ ስደተኞችን የሚያመሳስላቸው ሌላው ነጥብ ነው።

ኤርትራውያን በላምፔዱዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እስክንድር “አውሮፓ ልግባ እንጂ ተምሬ እና ሰርቼ ሕይወቴን እቀይራለሁ” የሚለው ሕልሙ ሩቅ እንዳልሆነ ሲሰማው ተደሰተ።

ከፊት ለፊቱ የነበረው እና ጩራ የተባለ ወጣት በቀጥታ ወደ እሱ መጥቶ “እስክንድር፣ አንተ ተወዳጅ ሰው ነህ” ሲለው “ይሄ ልጅ ምን ሆነ?” ሲል ራሱን ጠየቀ።

ብዙም ሳይቆይ ሌላ ስደተኛ ከኋላው መጥቶ፣ “እስክንድር ሲጋራ ካለህ ለሁሉም ስጥ፣ ዶላር ካለህም ጣለው፤ አይጠቅምህም” ሲለው “ሰዉ ምን ሆኗል?” ብሎ መገረሙን ያስታውሳል።

ሕገ ወጥ የሰዎች አሸጋጋሪዎች 518 መንገደኞችን ከእንጨት በተሰራች ጀልባ በመጫን፣ ስደተኞቹን እየደበደቡ እና እያንገላቱ ጉዞው ተጀመረ።

ሌሊቱን በሙሉ ሰላማዊ ጉዞ ነበር፤ ለፈጣሪያቸው ምስጋና እያቀረቡ ሳለ ከርቀት የሚፍለቀለቅ ብርሃን በመመልከታቸው ላምፔዱዛ መድረሳቸው፣ ወደ ደረቅ መሬት መቅረባቸው ተነገራቸው።

ስደተኞቹም የከተማዋን መብራት አይተው “ገባን!” አሉ።

አንዳንዶቹ በደስታ እየጮኹ ዘመሩ።

ሌሎች ደግሞ ጣሊያን ውስጥ አሻራ ትተው ቀጣዩ ጉዟቸው እንዳይሰናከል፣ በተከታይነት ማድረግ ስላለባቸው ነገር ያስቡ ነበር።

“የላምፔዱዛን ከተማ መብራቶች ስናይ ‘ገባን’ አልን። በጉዞው ደክመን ነበር፤ ብዙዎቻችን ደግሞ በነበርንበት ተኝተን ነበር” ይላል አድሃኖም።

የደስታቸው ሰበብ ላምፔዱዛ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ላይ መሆኗ ብቻ አይደለም።

በርካቶቹ እዚህ ለመድረስ የራሳቸውን ብቻ ሳይሆን የቤተሰቦቻቸውን ጥሪት አሟጠዋል።

ከሊቢያ ብቻ ወደ ጣልያን ለመሻገር እያንዳንዳቸው 1600 ዶላር ከፍለዋል።

ከሰላሳ ስድስት ሰዓታት የማያቋርጥ አደገኛ የባሕር ላይ ጉዞ እና የጋዝ ሽታ በኋላ በርቀት የአውሮፓ መሬትን ሲመለከቱ በተወሰነ መልኩ የቅዠታቸው መጨረሻም መስሏቸው ለመውረድ ዝግጅት የጀመሩም ነበሩ።

ካፕቴኑ የጀልባዋ ሞተሩን አጥፍቶ የጣልያን ባህር ጥበቃዎች ገፍተው እንዲያስገቧቸው እየተጠባበቁ ነበር።

በጀልባዋ በላይኛው ክፍል ላይ የነበሩት ብርድ ልብሳቸውን ለብሰው ተቀምጠው የነበረ ሲሆን፣ የተወሰነም ንፋስ ነበረው።

የታችኛው የጀልባው ክፍል ተጨናንቋል፤ የባሕሩ ሽታ እያጥወለወላቸው በርካቶችም ታጉረዋል። በዚህም ወቅት ነው የባሕሩ ውሃ ወደ ጀልባዋ መግባት የጀመረው።

በወቅቱ የነበሩ የዐይን እማኞችም እንደሚናገሩት ካፕቴኑ ከላይኛው የጀልባው ክፍል ወደ ታችኛው ወርዶ ሞተሩን ሊያስነሳ ቢሞክርም እምቢ አለው።

የተጨነቀው ካፕቴን ጋዝ ብርድ ልብስ ላይ አርከፍክፎ ባሕር ዳርቻው ላይ በማሳየትም ትኩረት ለመሳብ እና እርዳታ ለማግኘት ሞከረ።

ሆኖም ያ ከመሆኑ በፊት እሳቱ እጁን ስላቃጠለው ጣለው። እሳት ጀልባው ላይ መንደድ ጀመረ። ተኝተው የነበሩ ስደተኞች በጩኸት እና በእሳቱ በድንጋጤ ተነሱ። በስደተኞች የታጨቀችው ጀልባም በረብሻ፣ በጩኸት እና በዋይታ ተሞላች።

በርካቶች ከእሳቱ ለማምለጥም ሲሞክሩ እና ሲረጋገጡ ጀልባዋም እያጋደለች መስመጥ ጀመረች። በታችኛው የጀልባዋ ክፍል የነበሩትም የመትረፍ ዕድል አልነበራቸውም።

ከላይ የነበሩት ደግሞ ወደ ባሕሩ ተወረወሩ፤ የተወሰኑት በደመ ነፍስ ጀልባዋን የሙጥኝ ብለው ለመትረፍ ሞከሩ።

ኤርትራውያን በላምፔዱዛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አብርሃለይ እሳቱ እና ጩኸቱ ሲባባስ እንቅልፍ ላይ ስለነበረ ህልም መስሎ ተሰማው።

ሰዎች ከእሳት ለማምለጥ ወደ ባሕሩ ዘለው ሲገቡ፣ ዋኝቶ የማያውቀው አብርሃለይ ደነገጠ፤ ፈራ።

“አምላኬ ሆይ ራስህ አድነኝ!” ብሎ ጀልባው ውስጥ ለረጅም ጊዜ መቆየቱን እና ዘግይቶ ወደ ባሕሩ መግባቱን ያስታውሳል።

“ከዚያ ጩኸት ብቻ ሆነ፤ ምንም የማደርገው ነገር ስላልነበረ ዝም ብዬ እጮኻለሁ። ሁሉም ሰው ይጮሃል። አንዳንዶቹ እንዳይደክምህ ዝም በል ይሉኛል። . . . በመጨረሻ ግን ባሕር ላይ መሆኔን ረስቼ ቤተሰቦቼ ይታዩኝ ጀመር። በማዕበሉ እየተገፋሁ ሀሳብ ውስጥ ሰመጥኩ። በመጨረሻም በእግዚአብሔር ቸርነት ተረፍኩ።”

አድሃኖም በበኩሉ ሁኔታውን ሲያስታውስ “ደክሞኝ ነበር፣ ሰው ሁሉ ወደ ባሕር ሲገባ ልክ ወራጅ ውሃ ውስጥ እንደተሰበሰቡ ጊንጦች ሆንን። በጣም ደክሞኝ ስለነበር የተወረወረልኝን የነብስ ማዳኛ ጎማ እንኳን መያዝ አልቻልኩም። ነገር ግን በተዓምር ከዳኑት መካከል እንድሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበር” ይላል።

እስክንድርም ተመሳሳይ ነገር ነው የሚያስታውሰው።

“እግዚአብሔር ቀንህን ካልቆረጠው አትሞትም የሚለው አባባል እውነት መሆኑን ያመንኩት ያኔ ነው። ውሃ ውስጥ ገብተው የማያውቁ ሰዎች ይድኑ ነበር፣ ነገር ግን የቀድሞ የባሕር ኃይል አባላት እና ዋናተኞች ግን አልተረፉም” ሲል በሕይወት መትረፉን ከፈጣሪ ፈቃድ ጋር ያስተሳስረዋል።

የስደተኞች መቃብር ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, YOSEPH AND ADHANOM

የላምፔዱዛን እልቂት በመገናኛ ብዙኃን ሲዘገብ የተጎጂ ቤተሰቦች እና የዓለም ማኅበረሰብ አሰቃቂውን አደጋ በጥልቅ ሐዘን ነበር ተከታተለው።

የተጎጂ ቤተሰቦች የወንድሞቻቸውን፣ የእህቶቻቸውን እና የልጆቻቸውን ሞት መርዶ ሰሙ።

ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሞክሩ የነበሩ ሰዎች ምስሎች፣ የአስከሬኖች ምስሎች፣ በእሳት የተቃጠለው ጀልባ ሲሰምጥ የሚያሳዩ ምስሎች በስፋት በመገናኛ ብዙኃን ታዩ።

“ትናንት አብረውን የበሉና የጠጡትን፣ ለወራት አብረውን የተጓዙትን፣ ብዙ ተስፋ እና ህልም ያላቸው፣ አንዳንዶቹ ቦርቀው ያልጠገቡ ህጻናት ድንገት ባሕር ላይ ቀርተው አስክሬናቸው ሲወጣ ማየት ከባድ ነበር” ይላል አድሃኖም።

ከጥቂት ቀናት በኋላ ከአደጋው በሕይወት መትረፍ የቻሉት ሰዎች ምን እንደተፈጠረ ለዘመዶቻቸው መንገር ጀመሩ።

እስክንድር ከስድስት ቀናት በኋላ ደቡብ ሱዳን ጁባ ወደ ሚገኘው ታላቅ ወንድሙ ስልክ ደውሎ በሕይወት መትረፉን ተናገረ።

“በሰላም ገብቻለሁ፤ ነገር ግን በመቶዎች የሚቆጠሩ መንገደኞች በመጎዳታቸው መጥፎ ሁኔታ ላይ ነኝ” ብሎ ስልኩን ዘጋ።

አድሃኖም ግን ብዙ የቤተሰቡ አባላት ስለተጎዱ ሐዘኑ ከባድ ነበር። ቤተሰቦቹ የአድሃኖምን በሕይወት መትረፍ ከጓደኛው ነበር የሰሙት።

አብርሃለይ ደግሞ አዲስ አበባ ይኖር ወደ ነበረው ታላቅ ወንድሙ እና አሥመራ ወደ ምትገኘው እናቱ ደውሎ ከአደጋው መትረፉ ነገራቸው።

ዛሬ ከአስር ዓመታት በኋላ ክስተቱን ሲያስታውሱ ሁሉም አሰቃቂው አደጋ ትናንት የተከሰተ ያህል ነው የሚሰማቸው።

“የ369 ሰዎች ሕይወት ተቀጥፎ እንዴት በሰላም ትኖራለህ?” ሲል አድሃኖም ያለበትን ሁኔታ ይናገራል።

ከሁሉም በላይ ተጎጂዎቹ የተለመደው የቀብር ሥነ ሥርዓት ሳይፈጸምላቸው በየቦታው መቀበራቸው እረፍት ይነሳዋል።

“የሟች ቤተሰቦች ልጆቻቸውን አልቀበሩም። ብዙ እናቶች የተከሰተውን ነገር አልተቀበሉትም፤ ልጄ የሆነ ቦታ ላይ ሆኖ ነው እንጂ ይኖራል እንደሚሉ እንዳሉ ስለምታውቅ እንዴት ተብሎ እረፍት ይገኛል?” ይላል።

አድሃኖም በአሁኑ ወቅት የሁለት፤ እስክንድር ደግሞ የሦስት ልጆች አባት ሆነዋል።

አብርሃለይ በቅርቡ ትዳር ለመመሥረት ሂደት ላይ ነው።