ለ1977ቱ የኢትዮጵያ ረሃብ እርዳታ ማሰባሰቢያ የነበረው የሙዚቃ ዝግጅት ወደ መድረክ ሊመጣ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢትዮጵያ ለተከሰተው የ1977ቱ አስከፊ ረሃብ እርዳታ እንዲውል በገንዘብ ማሰባሰቢያነት ከ38 ዓመታት በፊት የተዘጋጀው የሙዚቃ ዝግጅት ዳግም ወደ መድረክ ሊመጣ ነው።
‘ላይቭ ኤይድ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው እና በርካታ ሙዚቀኞችን ያሰባሰበው የሙዚቃ ዝግጅት በዝነኛነቱ አሁንም ዓለማችን ከምታወሳቸው አንዱ ነው።
በቀጥታ የተላለፈው የሙዚቃ ዝግጅትም ተዘጋጅቶ በመድረክ ሙዚቃነት በሚቀጥለው ዓመት በለንደን ይቀርባል።
የመጀመሪያው የሙዚቃ ዝግጅት በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 13/1985 በዌምብሌይ ስታዲየም የቀረበ ነው።
ታዋቂው ሙዚቀኛ ቦብ ጌልዶፍ እና ሚጅ ዩሬ ናቸው ከ38 ዓመታት በፊት የነበረውን ኮንሰርት ያዘጋጁት።
‘ጀስት ፎር ዋን ደይ’ በሚል ስያሜ ወደ መድረክ የሚመለሰው ይህ የሙዚቃ ቅንብር ኩዊን፣ ሰር ኤልተን ጆን፣ ሰር ፖል ማካርቲኒ እና ስቲንግ የተጫወቷቸው ዘፈኖችን አካቷል።
በለንደን ኦልድ ቪክ ቲያትር ከጥር አጋማሽ እስከ መጋቢት የሚቀርብም ይሆናል።
ለዚህም የሙዚቃ ዝግጅት መነሻ የሆነው በኢትዮጵያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ እየረገፉ መሆኑን አስመልክቶ ቢቢሲ በአውሮፓውያኑ 1984 የሰራው ዘገባ ነበር።
የቢቢሲው ሚካኤል ቡኤርክ “በ20ኛው ክፍለ ዘመን የተከሰተ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የምናውቀው ረሃብ”፣ “በምድር ላይ ለገሃነም ቅርቡ” ሲልም ነበር የኢትዮጵያውን ረሃብ የዘገበው።
ይህንንም ዘገባ ተከትሎ ነበር በሙዚቀኛው ጌልዶፍ አሰባሳቢነት የሙዚቃ ዝግጅቱ እውን የሆነው። በፊላደልፊያ እና በለንደን፣ዌምብሌይ የተካሄዱት ቀጥታ የተላለፉ የሙዚቃ ዝግጅቶች ዓለም ምንጊዜም በታላቅነታቸው የምታስታውሳቸውን ቦብ ዲላን፣ ሊድ ዘ ፔሊን እና ዘ ሁን አካተው ነበር።
በወቅቱ በሥፍራው ተገኝተው ከተከታተሉት በተጨማሪ 1.5 ቢሊዮን ሕዝብ በቴሌቪዥን እንደተከታተለው የሚገመት ሲሆን ለረሃቡም በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ተሰባስቧል ተብሏል።
በዓለማችን ለተካሄዱ የእርዳታ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ዝግጅቶች መሰረቱን የጣለው ይሄ የሙዚቃ ኮንሰርት እንዲሁም ሰብዓዊ እርዳታዎች በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አጀንዳ እንዲሆን አስችሏል።












