በስፔን በምሽት መዝናኛ ክለብ ውስጥ በተነሳ የእሳት አደጋ 13 ሰዎች ሞቱ

አንድ የእሳት አደጋ ሠራተኛ እሳቱን ለመቆጣጠር ሲሞክር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በደቡባዊ ምሥራቅ ስፔን፣ ሙርሲያ ከተማ ሦስት የምሽት መዝናኛ ክለቦችን ባያያዘው የእሳት አደጋ ቢያንስ 13 ሰዎች ሞቱ።

የእሳት አደጋው የተነሳው እሑድ ማለዳ ሲሆን 'ላ ፎንዳ' ተብሎ በሚታወቀው ፎንዳ ሚላግሮስ የምሽት ክለብ ውስጥ ነው።

ከዚያም በአቅራቢያ ወዳሉ ሌሎች የምሽት መዝናኛ ክለቦች መዛመቱን ፖሊስ አስታውቋል።

የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሟቾቹ መከካል ልደት ሲያከብሩ የነበሩ የቤተሰብ አባላት ይገኙበታል።

በልደት መርሃ ግብር ላይ ከነበሩት ታዳሚዎች መካከል አንዱ የሆነውና ከአክስቱ እና ከአክስቱ ልጆች ጋር የተገኘው ግለሰብ ትርምሱ ሲፈጠር ወደ ቤቱ መመለሱን የተናገረ ሲሆን፣ አንደኛው የአክስቱ ልጅ ብቻ አለመመለሱ እንደተነገረው ላ ቨርዳድ ዲ ሙርሲያ ጋዜጣ ዘግቧል።

ነገር ግን የአክስቱ ልጅ ከሟቾቹ መካከል ይገኝበት እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ፖሊስ እንዳለው በአደጋው የሞቱት ሁሉም ሰዎች ላ ፎንዳ ክለብ ውስጥ የነበሩ ሲሆን ፣ ሌሎች 14 ሰዎች እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም። በመሆኑም የሟቾቹ ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቋል።

የምሽት ክለቡ የሚገኘው በሙርሲያ ከተማ አትላያስ አካባቢ ሲሆን የእሳት አደጋው የተቀሰቀሰው ትናንት ማለዳ 1 ሰዓት አካባቢ እንደሆነ ይታመናል።

የአደጋው መንስኤ እስካሁን አልታወቀም።

ሆኖም የሙርሲያ ከተማ ከንቲባ ጆሴ ባሌስታ የእሳት አደጋው ክለቡ በሚገኝበት ሕንጻ የመጀመሪያ ወለል ላይ መነሳቱን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ፖሊስ በበኩሉ የላ ፎንዳ ክለብ ጣሪያው በመደርመሱ ተጎጂዎችን ለማግኘት እና ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ አዳጋች አድርጎታል ብሏል።

እሳቱ ሲነሳ በክለቡ ውስጥ የነበረች የ28 ዓመቷ ወጣት “ እናቴ እወድሻለሁ፣ ልንሞት ነው” ስትል ለእናቷ የድምጽ መልዕክት መላኳን ላ ቨርዳድ ዲ ሙርሲያ ጋዜጣ ዘግቧል።

ወጣቷ ከፍቅረኛዋ እና ከቅርብ አካባቢ ከመጡ ጓደኞቿ ጋር ለመዝናናት ነበር የወጣችው። ሕይወቷ ስለመትረፉ እስካሁን የታወቀ ነገር የለም።

ሌሎች አራት ሰዎች በጭስ ታፍነው በሆስፒታል ውስጥ ሕክምና እየተደረገላቸው ሲሆን በአደጋው የተጎዱት በአካባቢው በሚገኝ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታ የሥነ ልቦና ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።

የከተማዋ ከንቲባ ጆሴ ባሌስታ በአደጋው ማዘናቸውን የገለጹ ሲሆን በከተማዋ ሦስት የሐዘን ቀናትን አውጀዋል።

ይህ አደጋ ከ30 ዓመታት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ በአገሪቷ በምሽት የመዝናኛ ሥፍራ የተከሰተው አስከፊው አደጋ እንደሆነ ይታመናል።

እንደ አውሮፓውያኑ 1990 በዛራጎዛ በተነሳ እሳት አደጋ 43 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።