እውቋ ድምጻዊት ሻኪራ ታክስ በማጭበርበር ለሁለተኛ ጊዜ ተከሰሰች

ሻኪራ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሻኪራ በዚህ ወር በኤምቲቪ የሙዚቃ ሽልማት የሕይወት ዘመን ስኬት ተሸላሚ ሆናለች

የስፔን መንግሥት ኮሎምቢያዊቷን ታዋቂ ድምጻዊት ሻኪራን ለሁለተኛ ጊዜ ታክስ በማጭበርበር ክስ መሰረተባት።

ድምጻዊቷ እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 የስፔን መንግሥትን የ7.1 ሚሊዮን ዶላር ታክስ አጭበርብራለች ሲሉ ዐቃቢያነ ሕጎች ከሰዋታል።

ሻኪራ ከነበሯት የሙዚቃ ኮንሰርቶች መካከል ‘ኤል ዶራዶ ዎርልድ ቱር’ ለተባለው የሙዚቃ ዝግጅት የተቀበለችው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ቅድሚያ ክፍያን ለመንግሥት ቀድማ አለማሳወቋ ተገልጿል።

የስፔን መንግሥት አቀቢያነ ሕጎች ሁለተኛውን ምርመራቸው ባለፈው ሐምሌ ወር የከፈቱ ቢሆንም ዝርዝር መረጃዎችን ይፋ ያደረጉት ግን ማክሰኞ ዕለት ነው።

የ46 ዓመቷ ድምጻዊት ሰለተከፈተባት አዲስ ክስ መረጃ እንዳላት አንድ የስፔን መገናኛ ብዙኃን ቢዘግብም፣ አሁን በምትኖርበት የአሜሪካዋ ግዛት ሚያሚ ያለው የሕግ ቡድኗ ግን ስለክሶቹ እሳካሁን እንዳልተነገራቸው ሮይተርስ ዘግቧል።

ጠበቆቿ አሁን ላይ ከ2012 እስከ 2014 (እአአ) ባለው የበጀት ዓመት የሚያተኩረው እና ከሁለት ወራት በኋላ በሚጀምረው የክስ ሂደት ላይ እንደሚያተኩሩ ለሮይተርስ በላኩት መግለጫ አሳውቀዋል።

ሻኪራ ከእውቁ እግር ኳስ ተጫዋች ጄራርድ ፒኬ ጋር በነበራት የፍርቅር ሕይወት ስፔን ባርሴሎና ውስጥ ትኖር የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ወቅት ካገኘቻቸው ዓለም አቀፍ ገቢዎች በሙሉ ለስፔን መንግሥት ታክስ መክፈል ይጠበቅባት ነበር። የቀረበባት አዲሱ የሚያተኩረውም አውሮፓውያኑ 2018 ላይ ነው።

የስፔን ዐቃቢያነ ሕጎች የሚከራከሩት ሻኪራ ግብሯን ለስፔን መንግሥት ከመከፈል ይለቅ ገንዘቧን “ዝቅተኛ ታክስ ወደ ሚከፈልበት እና ግልጽነት በሌላቸው” አገራት ውስጥ ወደ ሚገኙ ኩባንያዎች አዘዋውራለች በማለት ነው።

ሻኪራ በተለያዩ ከስድስት በላይ ከግብር ማጭበርበር ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ባርሴሎና ውስጥ ክስ ቀርቦባታል። እሷ ግን ክሶቹን ታስተባብላለች።

ሻኪራ ቀደም ሲል በቀረበባት ክስ ከአውሮፓውያኑ 2012 አስከ 2014 ባለው ጊዜ ለስፔን መንግሥት መክፈል የነበረባትን ከ15 ሚሊዮን ዶላር በላይ ግብር ሳትከፍል ቀርታለች የሚል ነው። ነገር ግን እሷ ምንም ወንጀል እንዳልፈጸመች በመግለጽ ክሱን ተቃውማለች።

“መከራከሪያዬን የሚያስረዱልኝ በቂ ማስረጃዎችእንዳሉኝ እርግጠኛ ነኝ፤ እኔን የሚደግፍ ፍትሕ አገኛለሁ” በማለት ለአንድ መጽሔት በቅርቡ ተናግራለች።