የሩሲያ ሰላዮች ናቸው የተባሉ አምስት ሰዎች ለንደን ውስጥ ፍርድ ቤት ቀረቡ

በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚንቀሳቀስ የሩሲያ የስለላ ቡድን አባላት ናቸው የተባሉ አምስት ሰዎች ለንደን ውስጥ ፍርድ ቤት ቀረቡ።
የቡልጋሪያ ዜጎች የሆኑት ኦርሊን ሩሴቭ፣ ቢዜር ዣምባዞቭ፣ ካትሪን ኢቫኖቫ፣ ኢቫን ስቶያኖቫ እና ቫንያ ጋቤሮቫ “ለጠላት ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ለመስብሰብ በማሴር” ነው የተከሰሱት።
ግለሰቦቹ ባለፉት ሦስት ዓመታት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በሩሲያ ኢላማ የተደረጉ ሰዎችን እና ቦታዎች ላይ ስለላ አካሂደዋል ተብለዋል።
ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት ከቀረቡ በኋላ በእስር ቤት እንዲቆዩ ተደርገዋል።
የተጠርጣሪዎቹ የስለላ ተግባር ሩሲያ በኢላማዎቹ ላይ አፍኖ መሰወርን ጨምሮ እርምጃ እንድትወስድ ለማድረግ የሚያስችል ነው ተብሏል።
እስረኞቹ በአራት የተለያዩ አስር ቤቶች ውስጥ ሆነው በቪዲዮ ግንኙነት አማካይነት ፍርድ ቤት የቀረቡ ቢሆንም፣ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ግን አልሰጡም።
አምስቱም ተከሳሾች ስማቸውን እና የትውልድ ጊዜያቸውን ለማረጋገጥ ለችሎቱ ምላሽ ከመስጠት ውጪ ዝምታን መርጠዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም ፖሊስ የፀረ ሽብር መኮንኖች ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር ያዋሏቸው ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ነው።
ክሱን ያቀረቡት ዐቃቤ ሕግ ካትሪን ሴልቢ በችሎቱ እንደተናገሩት “የስለላ ድርጊቱን በአገሪቱ ውስጥ ለማካሄድ እንደ ማዕከል የሆነው” የአንደኛው ተከሳሽ ሚስትር ሩሴቭ ቤት ነው።
ግለሰቡ የስለላ ሕዋሱ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ የሚያካሂደውን ተግባር በማስተባበር እና በመምራት ተከሷል። በተጨማሪም ይህ ተልዕኮ በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ ሳይሆን በአውሮፓ ውስጥም ሲካሄድ ነበር ተብሏል።
አምስቱ ተከሳሾች ጃን ማርሳሌክ በተባለ ግለሰብ የሚመራ የስለላ ቡድን አባል ናቸው ተብለዋል። ነገር ግን ግለሰቡ በዚህ ክስ ውስጥ አልተካተተም።
ቡድኑ በአስተባባሪው ሩሴቭ አማካይነት ከጃን ማርሳሌክ ከውጭ አገር የስለላ ተልዕኮዎችን ሲቀበል ነበር ተብሏል።
ጃን ማርሳሌክ የአንድ የአውስትራሊያ ካምፓኒ ሠራተኛ እንደነበረ የሚታወቅ ሲሆን፣ የማጭበርበር ድርጊት ፈጽሟል ተብሎ ጀርመን ውስጥ ተፈላጊ ነው። ከዚያም ወደ ቤላሩስ በመሸሽ በአሁኑ ጊዜ ሩሲያ ውስጥ እንደሚገኝ ይነገራል።
ዛሬ ማክሰኞ ዌስትሚኒስተር ፍርድ ቤት የቀረቡት ተጠርጣሪዎች በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ተመልሰው ችሎት እንደሚቀርቡ ዐቃቤ ሕግ ገልጿል።












