ኢራቅ ውስጥ በሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ቢያንስ 100 ሰዎች ሞቱ

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እና ወታደሮች በአል-ሃምዳኒያ ሆስፒታል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች እና ወታደሮች በአል-ሃምዳኒያ ሆስፒታል ውስጥ

በሰሜናዊ ኢራቅ በሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ በተከሰተ የእሳት አደጋ ቢያንስ 100 ሰዎች መሞታቸውን እና ሌሎች 150 እንደተጎዱ የአገሪቱ መንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ዘገቡ።

ማክሰኞ ምሽት በኢራቅ ሰሜናዊ ግዛት ኒኔቬህ ውስጥ በምትገኘው አል-ሃምዳኒያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በታደሙበት የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ነው የእሳት አደጋው የተከሰተው።

ለእሳቱ አደጋ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም፣ አንዳንድ ዘገባዎች ግን ርችት መተኮሱን ተከትሎ አደጋው እንደተከሰተ አመልክተዋል።

አስካሁን ሙሽሮቹ ከሞቱት ወይም ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ስለመሆናቸው የታወቀ ነገር የለም።

ነገር ግን ቀድመው የወጡ ዘገባዎች ሙሽሮቹ በአደጋው ሞተዋል ቢሉም፣ ኒና የተባለው የዜና ወኪል በኋላ ላይ እንደዘገበው ሙሽሮቹ ጉዳት ደርሶባቸው ሕክምና ላይ መሆናቸውን ዘግቧል።

ከአደጋው ስፍራ የወጡ ፎቶግራፎች የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳቱን ለመቆጣጠር ጥረት ሲያደርጉ እና በእሳት የተቃጠሉ የሰዎች አስከሬኖችን አሳይተዋል።

የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ የተካሄደበት ሕንጻ የተገናባበት ተቀጣጣይ ነገሮች እሳቱ በቀላሉ እንዲስፋፋ እና ለበርካታ ሰዎች ሞት እና ጉዳት ምክንያት ሳይሆን እዳልቀረ የኢራቅ ባለሥልጣናት መናገራቸው ተዘግቧል።

የእሳት አደጋ ሠራተኞች አስከ ዛሬ ረቡዕ ጠዋት ድረስ በእሳት በወደምው የሕንጻው ፍርስራሽ ውስጥ የሞቱ ወይም ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ለማግኘት ፍለጋ እያደረጉ ይገኛሉ።

የዐይን እማኞች እንዳሉት የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ እየተካሄደ ሳለ በአገሩ የሠዓት አቆጣጠር ምሽት 4፡45 ላይ ነበር አደጋው የተቀሰቀሰው።

አደጋውን ተከትሎ የእሳት አደጋ ሠራተኞች እና የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ወደ ስፍራው መሰማራታቸውን ባለሥልጣናት ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል።

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር “በድንገተኛው አደጋ የተጎዱትን ለመርዳት አስፈላጊው ጥረት ሁሉ እንዲደረግ” ማዘዛቸውን ጽህፈት ቤታቸው በኤክስ (ትዊተር) ገጹ ላይ ገልጿል።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በኒኔቬህ ውስጥ ወዳሉ የተለያዩ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን የግዛቲቱ አስተዳዳሪ አመልክተው፣ የሟቾች እና የተጎጂዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችልም ተናግረዋል።

ከግዛቲቱ ዋና ከተማ ሞሱል በስተምሥራቅ ባለችው ሃምዳኒያ ውስጥ በሚገኘው ዋነኛ ሆስፒታል በእሳት አደጋው ለተጎዱ ሰዎች የሚውል ደም ለመለገስ በርካቶች መገኘታቸው ተዘግቧል።