ሕጻኗን ከናዚ ጭፍጨፋ የታደገው ምስጢራዊው ክፍል

የፎቶው ባለመብት, Sotheby's
አሰቃቂ ስለሆነው የናዚ ጭፍጨፋ ስናወሳ የአናን ማስታወሻ እናገኛለን።
አንደበተ ርቱዕዋ፣ አርቆ አሳቢዋ መጨረሻም ላይ በማንነቷ በጭካኔ የተቀጠፈቸው እና ጭካኔን ፍንትው አድርጋ ያሳየችን አና።
በቅርቡ ደግሞ ከዚህ ጭፍጨፋ የተረፈችው የሰባት ዓመቷ ዶሊ ታሪክ እንደ አዲስ እየተነሳ ነው።
ለዚህ ደግሞ በቅርቡ ለንደን ውስጥ በጨረታ ለሽያጭ ሊቀርብ የታቀደው የታዋቂው ሩሲያዊ ሠዓሊ ዋሲሊ ካንዲንስኪ ታሪካዊ ሥዕል ነው።
በከፍተኛ ዋጋ እንደሚሸጥ የተገመተው ይህ ሥዕል ከጀርባው የአንድ ቤተሰብ አሳዛኝ እና የጀግነነት ታሪክን አዝሏል።
ሥዕሉና ዶሊን ምን አገናኛቸው?
ለህትመት ባልበቃ ማስታወሻ ውስጥ በሰፈረው ታሪክ መሠረት ከአስርት ዓመታት በፊት የሰባት ዓመት ልጅ ምስጢራዊ በሆነች ክፍል ውስጥ ተደበቀች።
“ድምጽ ማሰማት አይደለም። ትንፋሽሽም ጮክ ብሎ በጭራሽ ሊሰማ አይገባም። እዚህ መሆንሽን ማንም ሊያውቅ አይገባም። ትሰሚኛለሽ? ማንም” የሚል ማስጠንቀቂያም ቀድሞ ከሞግዚቷ ተነገራት።
አያቷ፣ እናቷ እና አባቷ በአደራ ለሞግዚቷ በሰጧትም ወቅት ነው ይህ የተነገራት።
“ድምጽ ካሰማሽ እና ድንገት አንድ ሰው ቢሰማ ሁላችንም በጀርመኖች ልንገደል እንችላለን” የሚል ማስጠንቀቂያ ቢሰጣትም፣ የሕጻንነት አዕምሮዋ ቤቷን፣ እናቷን ወይም አያቷን ለዓመታት እንደማታያቸው አላወቀችም ነበር።
ቤቱ የሞግዚቷ ነው። የሞግዚቷን ቤተሰቦችም ሆነ ቤቱን አይታቸው አታውቅም።
ሆኖም ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ተኩል ሞግዚቷ በሰጠቻት ትንሽ ክፍል ውስጥ ተደበቀች። ጃምቦ ከሚባል የዝሆን አሻንጉሊት በስተቀር በእነዚህ ዓመታት አንድም ሰው አላየችም።
ዶሊ ትባላለች፣ አይሁዳዊት ነች። ወቅቱም በአውሮፓውያኑ 1943 ሲሆን፣ በናዚ ቁጥጥር ስር በነበረችው አምስተርዳም ውስጥ ነዋሪ ነበረች።
የዶሊ ታሪክ ከታዋቂዋ የአና ፍራንክ ታሪክ ጋር የሚያስገርም ተመሳሳይነት አለው። በእርግጥም አና በዚሁ ተመሳሳይ ጊዜ ነው የኖረችው። ይህ ብቻም አይደለም፣ በሁለት ማይሎች ርቀት በሚገኝ ቤት ውስጥ ነበር አና የተደበቀችው። ሁለቱ ታዳጊዎች አይተዋወቁም፣ ተገናኝተውም አያውቁም።
አና እና ቤተሰቧ ከተደበቁበት በአውሮፓውያኑ 1944 ተይዘው ወደ ኦሽዊትዝ ተላኩ። የዶሊ እናት፣ አባት እና አያት በኦሽዊትዝ ሲገደሉ፣ ትረፊ ያላት ዶሊ ከሞት አመለጠች።
በድብቅ የኖረችው አና ታሪክ ‘የአና ማስታወሻ’ በሚል ታትሟል። ማስታወሻዋ የጀርመኖችን የጅምላ ግድያ እና ጭፍጨፋን በሕጻን ልጅ ዕይታ ከሚነግሩ የታሪክ ሰነዶች አንዱ ለመሆን በቅቷል።
ከጭፍጨፋው የተረፈችው የዶሊ ታሪክ ባልታተመ ማስታወሻ ላይ ሰፍሮ የሚገኝ ሲሆን፣ ከመጽሐፍ ይልቅ ከአንድ ታዋቂ ሥዕል ጋር ጥብቅ ቁርኝት አለው።

የፎቶው ባለመብት, Sotheby's
በዘመናዊ የሥነ ጥበብ ዘርፍ ድንቅ የተባለው ሥዕል ለንደን በሚካሄደው ጨረታ ላይ 42 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሸጥም ተገምቷል። ይህም ለአርቲስቱ ክብረ ወሰን የሆነ ዋጋ ነው። ሥዕሉ የዶሊ ቤተሰቦች እነማን እንደነበሩ እና ምን እንደረሰባቸው ማስታወሻም ነው።
ይህ የጥበብ ሥራ ሙራናኡ ሚት ኪርቼ (ሙርናኡ በቤተ ክርስቲያን) የሚሰኝ ሲሆን፣ የተሳለው በሩሲያዊው ድንቅ ሠዓሊ ዋሲሊ ካንዲንስኪ ነው። ወቅቱም በአውሮፓውያኑ 1910 ነበር።
ይህ ሥዕል በአንድ ወቅት ከበርሊን ወጣ ብላ በምትገኘው ፖስዳትም በሚገኝ ውብ ቪላ ውስጥ ተሰቅሎ ነበር። በዚህ ቪላ ነዋሪዎች የነበሩት የዶሊ አያቶች ሲግበርት ስቴር እና ጆዋና ማርጋሬት ስቴርን ሲሆኑ፣ በሳሎናቸው የተሰቀለውን ይህንን ሥዕል የሚያሳይ ፎቶም አለ። ከሥዕሉ ጀርባም ሲግበርት “ላንድቻፍት” (መልክዓ ምድር) የሚል ጽሁፍ አስፍሮበት ነበር።
የዶሊ አያቶች ከመቶ ዓመት በፊት ስኬታማ የሆኑ የጨርቃ ጨርቅ ነጋዴዎች ነበሩ። ውሏቸውም ሆነ ግንኙነታቸው ጀርመን ካፈራቻቸው ፀሐፊያን፣ ታዋቂ ሰዎች ጋር ነበር። ከእነዚህም ውስጥ ቶማስ ማን፣ ፍራንዝ ካፍካ እና አልበርት አንስታይን ይገኙበት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Sotheby's
የዶሊ አያቶች የሥነ ጥበብ ሥራዎች አድናቂ ነበሩ። በርካታ ስዕሎችን አሰባስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ በአይሁድ ማኅበረሰብ ውስጥ ታዋቂና ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉም ነበሩ።
ከምሥራቅ አውሮፓ ሸሽተው በጀርመን በድህነት የሚኖሩ አይሁዶችንም የሚረዳ ድርጅት በአውሮፓውያኑ 1916 ማቋቋም ችለው ነበር።
የናዚዎች መምጣትን ተከትሎ ስተርኖችም ሆነ የአይሁድ ማኅበረሰብ የጥቃት ኢላማ ሆኑ። በተለይም የሲግበርት በአውሮፓውያኑ 1935 ሕይወት ማለፉን ተከትሎ ኑሮ ፈታኝ ሆነ። የተወሰኑ ልጆቻቸውም ወደ ሆላንድ ተሰደዱ። ባለቤቱ ጆዋና ማርጋሬትም አንዳንድ የቤት እቃዎቿን እና ሥዕሎቿን ይዛ ልጆቿን ተከተለች።
በወቅቱ እንደነበሩት በርካታ የአይሁድ ቤተሰቦች ስተርኖችም ውድ የሆኑ የሥነ ጥበብ ሥራዎቻቸውን ባልረባ ዋጋ በመሸጥ ገንዘብ አሰባሰበዋል።
በአውሮፓውያኑ 1941 ጆዋና ማርጋሬት በናዚዎች አገር አልባ ተብላ ተብላ ተፈረጀች። በዚህ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ነጻነቷን እንዴት ልታገኝ እንደምትችል ከናዚዎች ሃሳብ ቀረበላት።
ቪዛ እንደሚሰጣትና ከቤተሰቦቿም ጋር ሆላንድን ለቃ መውጣት እንደምትችል ነገር ግን ለነጻነቷ በምትኩም የፈረንሳይ አርቲስት ሄንሪ ፋንቲን ላቱርን ሥዕል እንድትከፍል ተጠየቀች።
ሆኖም የቀረበላት አማራጭ ማጭበርበር ነበር። ሥዕሉን ብትሰጣቸውም ቪዛ ማግኘት አልቻለችም።
ጆዋና ማርጋሬትም ሆነ የዶሊ ወላጆች ተደበቁ ነገር ግን በአውሮፓውያኑ 1943 ተያዙ። ዶሊ በማስታወሻዋ ውስጥ እንዳሰፈረችው ወላጆቿ በናዚ ቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት ለሞግዚቷ አና በአደራ ሰጧት።
ይህንንም ያደረጉት ከቤተሰቡ ቢያንስ አንዲት ልጅ ለዘር ብትተርፍ በሚል ነበር።
“አስታውሳለሁ ሌሊት ነበር። የእናቴ ዶሊ መነሳት አለብሽ የሚለው ለስለስ ያለ ድምጽ ነበር የቀሰቀሰኝ። ስነሳ አባቴ እና እናቴ አልጋዬ ላይ ተቀምጠው ነበር። ጀርመኖች ውጡ ስላሏቸው ለሁለት ሳምንታት ሌላ አገር እንደሚሄዱና ተመልሰው እንደሚመጡ ነገሩኝ።
“ድንገትም የበሩ ደወል በከፍተኛ ሁኔታ ጮኽ፣ በተደጋጋሚ። አባቴ በሩን ከፈተ። የናዚ ፖሊሶች ነበሩ። ተንደርድረው ገቡ። ሽኔል፣ ሽኔል፣ ሶንስት ሺሸን ዊር’ አሉ በጀርመንኛ “ቶሎ ቶሎ ውጡ፤ አለዚያ እንተኩሳለን የሚል ነበር። ከአና ጀርባ ተደበቅኩ። ፈራሁ፣ በጣም ፈራሁ!” የሚል ነበር።
የዶሊ ወላጆች ተወሰዱ። ለመጨረሻ ጊዜም ያየቻቸው በዚያች ሌሊት ነበር። በማግስቱ ከተማዋን አቋርጣ ወደ አና ቤት ብቻዋን አደገኛ የሚባል ጉዞ አደረገች። ናዚዎች እንደ ዶሊ ያሉ አይሁዶችን ለመለየት ቢጫ ኮከብ እንዲለብሱ ያስገድዷቸው ነበር።
በዶሊ ጃኬት ላይ የነበረውን ቢጫ ኮከብ አና የገነጠለችው ሲሆን፣ ከዚያች ዕለት ጀምሮም አክስቴ ብላ እንድትጠራት ነገረቻት። የአና ቤት ከፊሉ ለአንድ ዶክተር ማማከሪያ ክፍልነት ያገለግል የነበረ ሲሆን፣ ከዚያችም ጎን ጠባብ እና የተደበቀች ቦታ ነበረቻት። ይህች ክፍልም ለሚቀጥሉት ሰላሳ ወራት የዶሊ መኖሪያ ቤት ሆነች።

የፎቶው ባለመብት, Sotheby's
ዶሊ በዚያች ክፍል ውስጥ ስትደበቅ ሁለት መጽሐፎች ነበሯት፤ እነሱም የልጆች መጽሐፍ ቅዱስ እና የተረት ስብስብስ። መጽሐፎቹንም ደጋግማ አንብባቸዋለች።
በዚያች ጠባብ ክፍል ግድግዳ ላይም ‘አምላክ ሁሉን ያያል’ የሚል የደበዘዘ ፖስተር ነበር። እናም ዶሊም አምላክ እሷን ጨምሮ እንዴት ሁሉንም ሰው ሊመለከት ይችላል የሚለውም ያስገርማት ነበር።
“አመሻሹ ላይ ዶክተሮችን ለማማከር የሚመጡ ሰዎች ነበሩ። በጨለማ ውስጥም ተቀምጬ የህመምተኞችን የጫማ ዱካ እቆጥር ነበር” ትላለች።
አንዳንዴም ፖሊሶች እየመጡ ይፈትሻሉ። በዚህ ወቅት ዶሊን ከጣውላው ወለል ስር ወይም ከመታጠቢያ ገንዳ ስር ወዳለችው ቁም ሳጥን ውስጥ ታስገባታለች። በቁም ሳጥኑም ላይ መወልዋያና መጥረጊያ ታቆማለች።
የጀርመን ፖሊሶችንም በቀልድ አዋዝታ ብትሸኝም፤ ሁልጊዜ ውስጧ እንደተንቀጠቀጠ ነበር።
ለአንዲት ህጻን ልጅ በጣም ከባድ ከሆኑ ነገሮች አንዱ ምንም ቃል ሳታወጣ፤ በዝምታ መሸበብ ነበር።
በመጨረሻም የናዚ ሠራዊት በጥምር አገራት ኃይሎች ተሸንፈው፣ ሆላንድ በአውሮፓውያኑ 1945 ነጻ ስትወጣ የተሰማትን እፎይታ እና ደስታ እንዲህ አስፍራለች።
“ልክ እንደሌሎች ልጆች ጫማ አልነበረኝም። ጣውላ ሶል ከሁለት ማሰሪያዎች ጋር ተሰጠኝ። እሱንም አድርጌ ስራመድ ይጮህ ነበር። ድምጹ በጣም ደስ ይለኝ ነበር። ሁሉም ሰው ይሰማዋል። እንደገና መኖር ተፈቀደልኝ፤ በሙሉነት የመኖር ስሜት።”
ዶሊ እስከ 70ዎቹ እድሜ ድረስ ኖራለች፤ ከማስታወሻዋ መረዳት እንደሚቻለው እያንዳንዷን ቀን፣ ሕይወቷን አጣጥማ ነው የኖረችው።
በአውሮፓውያኑ 1935 የተወለደችው ዶሊ ከአይሁዳውያን የጅምላ ፍጅት [ከሆሎኮስት] ተደብቀው ከተረፉ መካከል አንዷ ሆናም ተመዝግባለች።

የፎቶው ባለመብት, Sotheby's
ይፋዊ የሆኑ ከሆላንድ የተገኙ ሰነዶች እንደሚያሳዩት አገሪቷ በናዚ ቁጥጥር ስር በነበረችበት ወቅት ከሞግዚቷ አና ጋር ትኖር ነበር።
ከዓመታት በኋላ የዶሊ ቤተሰቦች የጠፉትን የሥነ ጥበብ ሥራዎች የት እንዳሉ ለማወቅ ማፈላለግ ጀመሩ።
በአውሮፓውያኑ 2013 በአይንድሆቨን ሙዚየም ውስጥ የካንዲስኪ ስዕል እንዳለ ደረሱበት። የሥዕል አዋቂዎች ይህንን ሥራ ሲመረምሩ ከሥዕሉ ጀርባ “ላንድቻፍት” (መልክዓ ምድር) የሚል ጽሁፍ አገኙ።
ይህንንም ጽሁፍ ሲግበር ስቴርን የጻፈበት እንደሆነም አረጋገጡ። በኑዛዜውም ላይ በዚሁ ቃል ሥዕሉን ለመመዝገብ የተጠቀመበት ሲሆን የእጅ ጽሁፉም ተመሳሳይ ነበር።
ዶሊ ይህ ሥዕል የአያቶቿ ስለመሆኑ ከመረጋገጡ በፊት ነው ሕይወቷ ያለፈው። ሆኖም ፍለጋ ላይ እንደነበሩ ታውቅ ነበር።
ከረዥም እና አታካች ዘመቻ በኋላ ሥዕሉ ለቤተሰቡ ተመልሶላቸዋል። ከሳምንታት በኋላ በጨረታ የሚሸጥ ሲሆን ገቢውም በሕይወት ለተረፉት 13 የልጅ ልጆች ወራሾች እና ሌሎች ሥዕሎች የት ደረሱ ለሚለው ምርመራም ይውላል ተብሏል።
ሙራናኡ ሚት ኪርቼ በሥነ ጥበብ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ሥራ ነው። የሥነ ጥበብ ታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት ሠዓሊው ‘ሲንዢያ’ የተሰኘ ቀለም አይቶ ሙዚቃን መስማት የሚችልበት ሁኔታ ስጦታ ነበረው።
የዶሊ ቤተሰቦች ማንነቷ እንዲገለጽ ስላልፈለጉ በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የአባቷን ስም አልተጠቀምንም።












