ትራምፕ በአሜሪካ በመወለድ የሚገኝ ዜግነትን አስቆማለሁ አሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወላጆቻቸው በውጭ አገራት ቢወለዱም በአሜሪካ የተወለዱ ልጆቻቸው ዜግነት የሚያገኙበትን መብት እሽራለሁ አሉ።
ትራምፕ አስቆመዋለሁ የሚሉት በተለያዩ ምክንያቶች ተሰደው ወደ አሜሪካ የሄዱ ሰዎች የመኖሪያም ሆነ የዜግነት መብት ባያገኙም አሜሪካ ውስጥ የወለዷቸው ልጆች ዜግነትን ማግኘት የሚችሉበትን ነው።
ሆኖም በልጅነታቸው ወደ አሜሪካ የመጡ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ለመርዳት ከዴሞክራቶች ጋር እሰራለሁ ብለዋል።
በጥር ወር ወደ ዋይት ሃውስ የሚገቡት ዶናልድ ትራምፕ ስልጣንን ከተቆናጠጡ በኋላ በስደተኞች፣ ኃይል እና ምጣኔ ኃብትን ጨምሮ በፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ ስር ነቀል ለውጦችን እንደሚያመጡ ከኤንቢሲ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ረዘም ያለ ቆይታ ቃል ገብተዋል።
ትራምፕ ወላጆቻቸው ሌላ ቦታ ቢወለዱም በአሜሪካ የሚወልዷቸው ልጆች የአሜሪካ ፓስፖርት የማግኘት መብት የሚሰጠውን በመወለድ የሚገኝ የዜግነት መብት ለማስቆም ፕሬዚዳንታዊ ትዕዛዝ አስተላልፋለሁ ሲሉ ለኤንቢሲ ገልጸዋል።
በመወለድ የሚገኝ የዜግነት መብት የአሜሪካ ህገ መንግሥት አንቀጽ 14ን መሰረት ያደረገ ነው።
''ማንኛውም አሜሪካ ውስጥ የተወለደ ወይም ተገቢውን ግዴታዎች የተወጣ ሰው የአሜሪካ ዜጋ የመሆን ሙሉ መብት አለው'' ይላል።
"እኛ ይህንን መቀየር አለብን። ምናልባት ወደ ህዝቡ እንወስደዋለን። ነገር ግን ልናስቆመው ይገባል" ሲሉ ነው ትራምፕ የተናገሩት።
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው የቤተሰብ አባላት ያላቸውን ጨምሮ ህጋዊ ሰነዶች ያላሟሉ ስደተኞችን ከአገር ለማባረር የገቡትን ቃል ተግባራዊ አደርጋለሁ ብለዋል።
"ቤተሰብ መበተታተን አልፈልግም። ስለዚህ ቤተሰቦች የማይለያዩበት ብቸኛው መንገድ ሁሉንም አንድ ላይ ከአገር ማባረር ነው" ብለዋል።
ትራምፕ በአንድ ወቅት ለመሰረዝ ሞክረው የነበረውን ወደ አሜሪካ ብቻቸውን ለሚመጡ ህጻናት ከለላ የሰጠውን የኦባማ 'ዲፈርድ አክሽን ፎር ቻይልድ ሁድ አራይቫልስ' በተሰኘው ፕሮግራም የታቀፉትን በተመለከተ ከምክር ቤቱ ጋር አብሬ እሰራለሁ ብለዋል።
"ከዴሞክራቶች ጋር በአንድ ዕቅድ ላይ እሰራለሁ" ያሉት ትራምፕ ከነዚህ ስደተኞች መካከል ጥቂቶች ጥሩ ስራ የያዙ በንግድ ላይ የተሰማሩም አሉ ሲሉ አክለዋል።
ተመራጩ ፕሬዚዳንት ከሶስት ዓመታት በፊት በአሜሪካ የካፒቶል አመጽ በማስነሳት የተከሰሱ ግለሰቦችን ወደ ስልጣን በመጡ የመጀመሪያ ቀን ይቅርታ አደርግላቸዋለሁ ብለዋል።
"እነዚህ ሰዎች በገሃነም ውስጥ ነው" ያሉት ብለዋል በምርጫው ካሸነፉ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሰጡት ምልልስ።
በወንጀል የተከከሰ ልጃቸውን ይቅርታ ባደረጉት ባይደን ላይ ምርመራ እንደማይከፍቱ ቢጠቁሙም የካፒቶል አመጽን የመረመሩ የህግ አውጭዎችን ጨምሮ አንዳንድ የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸው መታሰር አለባቸው ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ትራምፕ በተቃዋሚዎቻቸው ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ በተደጋጋሚ የገቡትን ቃል ያሳካሉ በሚለው ላይ የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።












