ኢትዮጵያ ወደ ጁባላንድ የጦር መሳሪያ አስገብታለች ሲል የሶማሊያ መንግሥት ከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Villa Somalia/fb
በሶማሊያ መንግሥት እና በራስ ገዟ ጁባላንድ መካከል ያለው ውዝግብ በተባባሰበት ጊዜ ኢትዮጵያ ወደ ጁባላንድ የጦር መሳሪያ አስገብታለች ሲል የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ከሰሰ።
የሶማሊያ መንግሥት እንዳለው ሁለት የኢትዮጵያ አውሮፕላኖች ባለፉት ሳምንታት ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ፍጥጫ ውስጥ ወደገባባት ጁባላንድ ዋና ከተማ ኪስማዮ ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ጭነው ገብተዋል ብሏል።
በተጨማሪም አውሮፕላኖቹ የቀድሞው የጁባላንድ ምክትል ፕሬዝዳንት ማህሙድ ሳኢድ አደንን እና አጃቢዎቻቸውን አሳፍረው ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘዋል በማለት በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
እነዚህ የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራት አገሪቱ ክልሉ የበለጠ እንዳይረጋጋ እና ታጣቂ ቡድኖችን በመደገፍ የጌዶ ክልልን ለመቆጣጠር የምታደርገው ጥረት አካል ነው በማለት ከሷል።
የሶማሊያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው በግዛቱ ውስጥ ኢትዮጵያ በቅርቡ አካሄደች ያለው እንቅስቃሴ ብርቱ የዓለም አቀፍ ሕግ የሚጥስ እንዲሁም ለሶማሊያን ሉዓላዊነት እና መረጋጋት ስጋት ነው ብሏል።
የሶማሊያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ እንዲህ ያለውን ክስ ሲያሰማ ይህ የመጀመሪያው አይደለም ከዚህ በፊትም ኢትዮጵያ በፑንትላንድ፣ በጋልሙዱግ እና በሂርሻበሌ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ታጣቂዎች መሳሪያ እና ሥልጠናን እየሰጠች ነው በማለት በተደጋጋሚ ሲከስ ነበር።
እሁድ ዕለት በሶማሊያ የማስታወቂያ ሚኒስቴር በኩል የወጣው መግለጫ ግን ኢትዮጵያን የጦር መሳሪያ ከማስገባት ባሻገር ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ፈጸመቻቸው ያላቸውን ድርጊቶች "ግዛት ማስፋፋትን ዓላማ ያደረገው ነው" ሲል ከሷል።
የሶማሊያ መንግሥት በመግለጫው ኢትዮጵያ እየፈጸመቻቸው ናቸው ያላቸው ድርጊቶች ዓለም አቀፍ ደንቦችን የሚጥሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን አለመግባባት በሰላም ለመፍታት የሚደረገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብሏል።
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል አንድ ዓመት ያስቆጠረውን ውዝግብ ለማርገብ የኬንያውን ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶን ጨምሮ ምሥራቅ አፍሪካ መሪዎች ጥረት እያደረጉ መሆኑ በቅርቡ መገለጹ ይታወሳል።
የሶማሊያ መንግሥት ኢትዮጵያን በከሰሰበት መግለጫው ላይ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ጥሰቶችን የምትፈጽም ከሆነ የግዛት አንድነቱን እንደሚከላከል እንዲሁም ከሶማሊያ መንግሥት እና ነጻ አገርነት በተቃራኒ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በሚተባባሩ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንሚወስድስ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላለፍፏል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነታቸው የተበላሸው ባለፈው ዓመት ታኅሣሥ ማብቂያ ላይ ኢትዮጵያ ሶማሊያ የግዛቴ አካል ናት ከምትላት ሶማሊላንድ ጋር የባሕር ጠረፍ አጠቃቀም የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ ነው። ኢትዮጵያ በምላሹ ለሶማሊላንድ የአገርነት ዕውቅና ተሰጣለች መባሉ ሶማሊያ የሉዓላዊነት ጥሰት ነው ስትል መክሰሷ ይታወሳል።
አሁን ደግሞ ከሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ጋር በምርጫ ሂደት አለመግባባት ውስጥ ገብቶ ግንኙነቱን ያቋረጠው የራስ ገዙ ጁባላንድ አስተዳደር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ግንኙነት አለው በሚል ሶማሊያ ኢትዮጵያን ትጥቅ በማቅረብ እየከሰሰች ነው።
በዚህም ኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳዬ ጣልቃ እየገባች ነው ከማለቷ በተጨማሪ በጁባላንድ ውስጥ ጌዶ በተባለ አካባቢ በጎሳዎች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ አድርጋለች በማለትም ከቀናት በፊት ኢትዮጵያን ከሳለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት ከሶማሊያ ባለሥልጣናት በኩል አሁን የቀረቡበትን ክሶች በተመለከተ እስካሁን የሰጠው ምላሽ የለም።















