ኢትዮጵያ ውስጥ "አጥፍተው የሚጠፉ ድሮኖች በከፍተኛ ቁጥር እየተመረቱ" መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

በወታደራዊ ዘመቻዎች ወቅት "የጠላት ስብስብን" ዒላማ ለማድረግ የሚውሉ "አጥፍተው የሚጠፉ ድሮኖች በከፍተኛ ቁጥር እየተመረቱ" መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አየር ኃይል፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) እንዲሁም የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት (ኒስ) ድሮኖችን "እያመረቱ" መሆኑን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን የገለጹት ሐሙስ ነሐሴ 29/2017 ዓ.ም. ከኢኮኖሚ ዘርፍ ባለሥልጣናት ጋር በመሆን "ኤሮአባይ" (AEROABAY) የተባለውን የድሮን ማምረቻ ተቋም በጎበኙበት ወቅት ነው።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ስር እንደሚገኝ የተገለጸው ይህ ተቋም፤ ሦስት ዓይነት ድሮኖችን እያመረተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ዐቢይ፤ በተቋሙ ያደረጉትን ጉብኝት በተመለከተ በሰጡት ገለጻ፤ "የምናመርታቸው [ድሮኖች] በውስን ቦታ የታጠሩ ሳይሆን፤ ለኮሜርሻል [ንግድ] ዓላማ የሚውሉ፣ ለሰርቬላንስ [ቅኝት] ዓላማ የሚውሉ፣ ለኦፕሬሽን [ለወታደራዊ ተልዕኮ] ዓላማ የሚውሉ በጣም በርካታ ድሮኖችን እያመረትን ነው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ"ኤሮአባይ" እንደሚመረት በቀዳሚነት የጠቀሱት አጥፍቶ ይጠፋል ያሉትን ድሮን ዓይነት ነው።

ዐቢይ በገለጻቸው፤ "አጥፍተው የሚጠፉ ድሮኖችን በከፍተኛ ቁጥር እያመረትን እንገናኛለን" ሲሉም ተደምጠዋል።

እነዚህ የድሮን ዓይነቶች በሚሰማሩበት ወቅት "ራሳቸውን አጥፍተው ዒላማን የሚያጠፉ" እንደሆኑም አስረድተዋል።

አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች "በ swarm (በከፍተኛ ቁጥር) መልክ" በሚደረጉ ውጊያዎች ወቅት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ገልጸዋል።

"ባደጉት ሀገራት የሚሰማ" ያሉትን ልምድ በመጥቀስም እነዚህ ድሮኖች "የጠላትን ስብስብ ሊያጠፉ" እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ድሮኖቹ "የሚሸከሟቸው payloads (መሳሪያዎች)" እንደሚኖሩም አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይመረታል ያሉት ሌላኛው ድሮን ለቅኝት (surveillance) ተግባር የሚውል ነው። መጠናቸው "አነስ አነስ" ያለ የሆኑት እነዚህ ድሮኖች፤ "በእጅ፣ በኪስ ውስጥ የሚገቡ፤ በቦርሳ የሚያዙ" እንደሆኑም ጠቅሰዋል።

አነስተኛዎቹን ድሮኖች የሚታጠቁት "ትናንሽ ዩኒቶች"፤ "አካባቢያቸውን ለመቃኘት" እንደሚጠቀሙባቸውም ተናግረዋል። "ለኦፕሬሽን በጣም ወሳኝ" እንደሆኑም አንስተዋል።

"ለኮሜርሻል ዓላማ" የሚውሉ ድሮኖችን እየተመረቱ እንደሆነ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "ከዚህ ቀደም አንዴ ለአርፊሻል ኢንተለጀንስ እና ለኢንሳ ኮንፈረንስ "show" [ትዕይንት] አድርገው ነበር" ሲሉ ግንቦት ላይ የቀረበውን የድሮኖች የአየር ላይ ትርዒት አስታውሰዋል።

"አሁንም በቅርቡ ለሚኖረን ፕሮግራም ትልቅ ሾው አዘጋጅተዋል። ይህንን ሾው የሚያዘጋጁት እዚሁ እያመረቱ ነው። ለኮሜርሻን ፐርፐዝ ነው" ብለዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የታዩ አነስተኛ ድሮኖች

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ትርዒት የሚቀርብበት ሥርዓት "በአንድ ጊዜ ሦስት ሺህ፣ ሁለት ሺህ ምናምን ድሮኖች (UAVs) ማነጋገር የሚያስችል" መሆኑንም ተናግረዋል።

እነዚህን ድሮኖች "በሀገር ውስጥ ማምረት" ከመጀመር ባሻገር "ገበያ የሚፈለግበት ጊዜ" እንደሆነም አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ "ከጥቂት ዓመታት በፊት" ሰው አልባ አውሮፕላኖችን "የመግዛት ፈተና" እንደነበረባት ጠቅሰዋል። "ገዝተን መጠቅም ከቻልን በኋላ፤ [ኢትዮጵያ] በተለያየ ደረጃ ማምረት የምትችል ሀገር ሆናለች" ብለዋል።

ድሮኖች በሀገር ውስጥ "በብዙ ቦታዎች እየተመረቱ" መሆኑን የሚናገሩት ጠ/ሚ ዐቢይ፤ ከእነዚህም መካከል የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢንሳ) እንዲሁም የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎትን (ኒስ) ዘርዝረዋል።

"የኢትዮጵያን ህልውና፣ ኢትዮጵያን ሉዐላዊነት የሚገዳደር አደጋ ሲመጣ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም፤ ያ የጀመርነውን ብልጽግና ለማስጠበቅ የምናውልበት መሳሪያ ይሆናል ማለት ነው" ሲሉ በምን ዓይነት መልኩ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአንድ ሀገር "አጠቃላይ ኢኮኖሚ ጉዞ መስመር እየያዘ ሲሄድ" በቀጣይነት መታሰብ የሚገባው የወታደራዊ አቅም ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።

"እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በኢኮኖሚ ዕድገት፣ በወታደራዊ አቅም... እኩል እንኳ ባይሆኑ በቅደም ተከተል አብረው ማደግ ካልቻሉ፤ ኢኮኖሚው በአቅም ማነስ ምክንያት ተመልሶ ሊበላ ይችላል" በማለት ተናግረዋል።

በኢኮኖሚው ዘርፍ የተጀመሩ ጉዞዎችን "በወታደራዊ አቅም እያስደገፉ መሄድ" እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።

"በእርሻ ያመጣነው ውጤት፣ በማዕድን ያመጣነው ውጤት፣ በእንደዚህ ያለ አቅም ካልተደገፈ፤ ብዙ ባንዳ እና ባዳ ባለበት ከባቢ ላይ አቅም ወሳኝ ነው። አቅም ከሌለ ማስጠበቅ ያስቸግራል" ሲሉም ተደምጠዋል።