የአሜሪካ ኤምባሲ፤ መንግሥት "በራሱ ሕዝብ ላይ" የሚፈጽማቸውን የድሮን ጥቃቶች "በአፋጣኝ እንዲያቆም" የጠየቀበትን ልጥፍ አሻሻለ

የፎቶው ባለመብት, U.S. Embassy Addis Ababa
የአሜሪካ ኤምባሲ፤ ከሰዓታት በፊት አውጥቶት የነበረውን እና አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ የፌደራል መንግሥት "በራሱ ሕዝብ ላይ" የሚፈጽማቸውን የድሮን ጥቃቶች "በአፋጣኝ እንዲያቆም" ጥሪ ያቀረቡበትን ልጥፍ ከፌስቡክ እና ከቲውተር ገጾቹ ላይ አንስቶ ለውጥ አደረገ።
እንደ አዲስ በወጣው የአምባሳደሩ መልዕክት ላይ የድሮን ጥቃትን በተመለከተ ለፌደራል መንግሥት የቀረበው ጥሪ "መንግሥት ከኃይል ውጪ ያሉ ሰላማዊ አማራጮችን መፈለጉን እንዲቀጥል" በሚጠይቅ ጥሪ ተተክቷል።
አምባሳደር ማሲንጋ ያስተላለፉት የመጀመሪያ መልዕክታቸውን በኤምባሲው የፌስቡክ እና ቲውተር ገጾች ላይ የተለጠፈው ዛሬ አርብ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም. ከቀኑ 4 ሰዓት ተኩል ገደማ ነበር። በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶችን ማቆምን የተመለከተው የአምባሳደሩ መልዕክት፤ ለፌደራል መንግሥት እንዲሁም የፋኖ ኃይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የተለያዩ ጥሪዎች የቀረቡበት ነበር።
ለፌደራል መንግሥቱ ቀርቦ የነበረው የአምባሳደሩ መልዕክት ሁለት ሀሳቦችን ያዘለ የነበረ ሲሆን፣ አንደኛው በመንግሥት የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች እንዲቆሙ የሚጠይቅ ነው። የአምባሳደሩ የተጠቀሙት አገላለፅ የመንግሥት የድሮን ጥቃቶች "በራስ ሕዝብ ላይ" የሚፈጸሙ እንደሆኑ የሚያመለክት ነበር።
አምባሳደሩ በመጀመሪያው መልዕክታቸው፤ "የፌደራል መንግሥት በአፋጣኝ በራሱ ሕዝብ ላይ ድሮን መጠቀም እንዲያቆም እና ስምምነትን እንዲያመቻች እንጠይቃለን" ብለዋል።
አምባሳደሩ ያስተላለፉት መልዕክት በአክቲቪስቶች እና ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች እንደገና ሲጋራ እና አስተያየት ሲሰጥበት ነበር።

የፎቶው ባለመብት, U.S. Embassy/Facebook Screenshot
ይህ ጥሪ የተካተተበት የአምባሳደር ማሲንጋ መልዕክት ከሰዓታት ቆይቷ በኋላ ከኤምባሲው የፌስቡክ እና የቲውተር ገጾች ተነስቷል።
ሰባት ሰዓት ገደማ ላይ በድጋሚ የተለጠፈው የአምባሳደሩ መልዕክት የድሮንን ጥቃትን የተመለከተውን ክፍል ያስወጣ እና ለፌደራል መንግሥት የቀረበውን ጥሪ ያሻሻለ ነው።
አዲሱ መልዕክት "የፌደራል መንግሥት ከኃይል ውጪ የሆኑ ሰላማዊ አማራጮችን መፈለጉን እንዲቀጥል" የሚጠይቅ ሲሆን፣ በተጨማሪም አምባሳደሩ መንግሥት "የዜጎቹን ደኅንነት እና የመኖር ዋስትና እንዲያስቀድም" ጥሪ አቅርበዋል።
በአምባሳደሩ መልዕክት ላይ ከዚህ ውጪ የተደረገው ሌላው ማሻሻያ ለፋኖ ኃይሎች በተላለፈው መልዕክት ላይ "ጥሪ እናቀርባለን" የሚለውን "እናሳስባለን" በሚል የተካ ነው።
በመጀመሪያው መልዕክት ላይ፤ "ዩናይትድ ስቴትስ ፋኖ ከተጨባጭ እና ሰላማዊ ዓላማዎች ጋር ወደፊት እንዲመጣ ጥሪ ታቀርባለች" ይል ነበር።
አምባሳደሩ፤ "በኦሮሚያ የሚካሄደውን ግጭትን ለማቆም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ድርድሮችን እንዲቀጥል ጥሪ እናቀርባለን" በማለት ለሌላኛው ታጣቂ ቡድን ያስተላለፉት ጥሪ አልተቀየረም።
አምባሳደር ማሲንጋ ዛሬ ያስተላለፉት መልዕክት በአጠቃላይ ግጭቶችን ማቆምን የተመለከተ ነው። መልዕክቱ ኢትዮጵያ "በቀጠሉ ግጭቶች ውስጥ ወደ ሌላ ዓመት" እየተሻገረች መሆኑን ይገልጻል።
እነዚህ ግጭቶች "በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ መለስ ብሎ ማሰብ አስፈላጊ" እንደሆነ በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።
"ሕዝቡን ለማስቀደም ጊዜው አሁን ነው" ያሉት አምባሳደር ማሲንጋ፤ ይህንን ለማድረግም "ለኢትዮጵያ ውስጣዊ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ መተግበር" እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
"የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቤታቸውን እንዲመለሱ ማድረግ" እንዲሁም "ሕጻናት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ" ማድረግም አስፈላጊ እርምጃዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
አምባሳደሩ፤ "የትጥቅ ትግል አካል እንደሆነ በማስመሰል [የተንሰራፋውን] ሕገ የለሽነት እንዲያበቃ ማድረግም" አምባሳደሩ "ሕዝብን ለማስቀደም" መተግበር አለባቸው ካሏቸው እርምጃዎች መካከል ነው። አምባሳደሩ መልዕክታቸውን የቋጩት "ሰላም እና መረጋጋትን ለመምረጥ ጊዜው [አሁን] ነው" በማለት ነው።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
የአሜሪካ ኤምባሲ የመጀመሪያውን የአምባሳደሩን መልዕክት ለምን ከገጹ እንዳነሳው እና ለምን ለፌደራል መንግሥት ቀረበውን ጥሪ እንደቀየ እስካሁን አልገለጸም።
ጠንከር ያሉ ቃላትን የሚጠቀሙት የአሜሪካ አምባሳደር ከዚህ ቀደም በሰጡት አስተያየት ምክንያት ከመንግሥት ነቀፋን አስተናግደው ነበር።
መንግሥትን ያስቆጣው የአምባሳደሩ አስተያየት ባለፈው ዓመት በዚሁ ግንቦት ወር በቀድሞው የአሜሪካ ቆንስላ ግቢ (አሜሪካ ግቢ) ባደረጉት ጠንከር ያለ ንግግር ላይ የተነሳ ነበር። አምባሳደሩ በዚህ ንግግራቸው፤ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ ጠይቀው ነበር።
ማሲንጋ፤ "ሽፍቶች፣ ታጣቂ ቡድኖች እና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሕይወት የመኖር እና የመከባበር መብቶች ላይ ጥሰት መፈፀማቸው የሕግ ሂደትን እና የሕግ የበላይነት አለማክበርን የሚያሳይ ነው" ሲሉም በመንግሥት እና ታጣቂዎች ላይ ጠንካራ ትችት አቅርበዋል።
ያልተገደበ ሰብአዊ አቅርቦት እንዲኖር እና ለዚህም መነሻ የሚሆን ጊዜያዊ አገር አቀፍ የተኩስ አቁም አንዲደረግም በዚህ ንግግራቸው ጠይቀው ነበር። አምባሳደሩ በተመሳሳይ ለፋኖ ኃይሎች እና ለኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ምክር አዘል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ በወቅቱ ያቀረቡት ወቀሳ ግን ከመንግሥት በኩል ጠንካራ ምላሽን አስከትሎ ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአምባሳደሩን ንግግር ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ ማሲንጋ "ያልተጠየቁትን ምክር" ሰጥተዋል በማለት ወቅሶ ነበር።
የአምባሳደሩን ንግግርም "በደንብ ያልተጤነ" እና "ብልሃት የሚጎድለው" ሲል ተችቷል። አምባሳደር ማሲንጋ "ሳይጠየቁ" ለኢትዮጵያ መንግሥት ምክር ለመለገስ ሞክረዋል ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ "ያልተገባ ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቀርቧል" ሲልም የአምባሳደሩን ወቀሳ አጣጥሏል።
የመንግሥት ኃይሎች በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ጋር በሚያደርጉት ግጭት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ከመሆኑ በተጨማሪ የሕዝብ መደበኛ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጓጎለ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ከእነዚሁ ግጭቶች ጋር በተያያዘ በሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን መንግሥታዊው የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች ሪፖርቶች ማመልከታቸው ይታወሳል።















