ከፓሪስ ሙዚየም 102 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ጌጣጌጦችን በመስረቅ የተጠረጠሩ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ላይ ክስ ተመሰረተ

የፎቶው ባለመብት, © RMN - Grand Palais (Musée du Louvre) Mathieu Rabeau
ከፓሪስ ሉቨር ሙዚየም 102 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ በወርቅ እና በእንቁ የተንቆጠቆጡ ታሪካዊ ቅርሶችን በመስረቅ የተጠረጠሩ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ።
የ38 ዓመቷ ሴት የተደራጀ ስርቆት እና የወንጀል ሴራ ላይ በመሳተፍ ክስ ሲመሰረትባት ሌላ የ37 ዓመት ወንድ ደግሞ በስርቆት እና በወንጀል አሻጥር ላይ በመተባበር ተከስሷል።
ሁለቱም ተከሳሾች የቀረበባቸውን ክስ አስተባብለዋል።
ከዚህ ቀደም በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ሁለት ወንዶች በስርቆት እና በወንጀል በማሴር ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ባለሥልጣናት በወንጀሉ ላይ ያለቸውን ተሳትፎ "በከፊል አምነዋል" ብለዋል።
በዓለማችን ላይ በከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ጎብኚዎች ከሚታወቀው ሙዚየም 102 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡት ጌጣጌጦች የተሰረቁት ጥቅምት 9/2018 ዓ.ም ነበር።
ስርቆቱ የተፈጸመው ሙዚየሙ ለጎብኚዎች ክፍት እንደተደረገ ማለዳ ላይ ሲሆን አራት ግለሰቦች በአጠቃላይ ስምንት ደቂቃ ብቻ በፈጀ ፍጥነት ስርቆቱን አከናውነው ተሰውረዋል።
ከዚህ በፊት ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉት ሰዎች በኋላ ላይ በወንጀሉ ላይ መሳተፋቸውን አምነዋል።
ቅዳሜ ዕለት በወንጀሉ ውስጥ ባላት ተሳትፎ ከዳኛ ፊት የቀረበችው ሴት ነዋሪነቷ በፓሪስ ላ ኮርኔቭ የሚባል አካባቢ መሆኑን ገልጻ ስታለቅስ መታየቷን የኤኤፍፒ ዘጋቢ ገልጿል።
ዳኛው ስሟ ያልተገለፀው ተከሳሽ በማረሚያ ቤት እንድትቆይ ወስነዋል።
ሌላው ስሙ ያልተገለፀ የ37 ዓመቱ ተከሳሽ እንዲሁ በማረፊያ ቤት ቆይቶ ጉዳዩን እንዲከታተል ተወስኗል።
ግለሰቡ ከዚህ ቀደም በተፈጸሙ ዝርፊያዎች ላይ በነበረው ተሳትፎ በፖሊስ ዘንድ የሚታወቅ ነው ተብሏል።
በፈረንሳይ የፍትህ ስርዓት ብዙ ጊዜ "በምርመራ ላይ እንዲቆይ" የሚደረግ ተጠርጣሪ ለፍርድ ይቀርባል።
ዳኛው አንድ ተጠርጣሪ በማረሚያ ቤት እንዲቆይ የሚወስኑት ግለሰቡ ወይንም ግለሰቧ ለማኅበረሰቡ ተጨባጭ አደጋ ናቸው ብለው የሚያምኑ ወይም ሊጠፉ አልያም ከሌሎች ጋር በመሆን ማስረጃ ሊሰውሩ ይችላሉ ብለው ካመኑ ነው።
የ38 ዓመቷ ተጠርጣሪ በማረሚያ ቤት እንድትቆይ የተወሰነው ማስረጃ ልትሰውር ትችላለች የሚል መከራከሪያ ከቀረበ በኋላ ነው።
የ37 ዓመቱ ግለሰብ የተጠረጠረበት ወንጀል ግልጽ ባይሆንም ረቡዕ ዕለት ከሌሎች አምስት ግለሰቦች ጋር ሆኖ ሲያዝ የዓቃቤ ሕግ ቢሮ አንዱ ተጠርጣሪ በወንጀሉ በተፈጸመበት ስፍራ ከተገኘ ዲኤንኤ ጋር ይያያዛል ብሎ ነበር።
ምናልባት ዘረፋው በተፈጸመበት ወቅት በውጭ ከነበሩት ሁለት ግለሰቦች መካከል አንዱ ተደርጎ ተቆጥሮ ሊሆን ይችላል።
በዘረፋው ላይ ከተሳተፉ አራት ሰዎች መካከል አንዱ አሁንም አልተያዘም።
በዚህ ሳምንት ከስርቆቱ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው በመጠርጠር በቁጥጥር ስር የዋሉ ሦስት ሰዎች ያለ ምንም ክስ ተለቅቀዋል።
ጥቅምት 9 ማለዳ በፈረንሳይ በሚገኘው ግዙፉ ሉቨር ሙዚየም አራት ሰዎች በመኪና ላይ የተገጠመ መሰላል ይዘው በመምጣት በአንደኛው የሙዚየሙ መስኮት በኩል ሰብረው በመግባት ነበር ዝርፊያውን የፈጸሙት።
ከአራቱ ዘራፊዎች መካከል ሁለቱ በመሰላሉ በመወጣጣት ወደ ሙዚየሙ መስኮት የደረሱ ሲሆን ከዚያም በመቁረጫ መሳሪያ መስኮቱን በመስበር ወደ ውስጥ መግባት ችለዋል።
ከዚያም ውስጥ የነበሩትን ጠባቂዎች በማስፈራራት እንዲሸሹ ካደረጉ በኋላ ውድ ጌጣጌጦችን ከያዙ የመስታወት ሳጥኖች መካከል ሁለቱን ቆርጠው ለዕይታ የተቀመጡ ውድ ጌጦችን ወስደዋል።
ከዝርፊያው በኋላ የወጣ ቀዳሚ ሪፖርት እንዳመለከተው ዝርፊያው ከተፈጸመባቸው የሙዚየሙ ክፍሎች መካከል አንዱ የደኅንነት ካሜራ እንዳልነበረው የፈረንሳይ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
በሚሊዮኖች ዶላር የሚያወጡትን ጌጣጌጦች ከሙዚየሙ የዘረፉት ሌቦች በሙዚየሙ ውስጥ የቆዩበት ጊዜ አራት ደቂቃ ብቻ ነበር። ከዚያም በገቡበት በመውጣት በትንንሽ ሞተሮች ተፈናጥጠው ከአካባቢው ተሰውረዋል።















