የልብ ቀዶ ሕክምና ከተደረገላት በኋላ ወደ ጦርነት ቀጣና እንድትመለስ የተገደደችው የጋዛዋ ጨቅላ

በዮርዳኖስ የልብ ቀዶ ጥገና ተደርጎላት ወደ ጋዛ እንድትመለሰ የተገደደችው የ7 ወሯ ኒቨን
የምስሉ መግለጫ, በዮርዳኖስ የልብ ቀዶ ጥገና ተደርጎላት ወደ ጋዛ እንድትመለሰ የተገደደችው የ7 ወሯ ኒቨን

በጋዛ ሰርጥ በስተሰሜን በሚገኘው አል ሻቲ ካምፕ በአንድ ድንኳን ውስጥ የ33 ዓመቷ ኢናስ አቡ ዳቃ ጨቅላ ልጇን አቅፋለች።

እናት ጨቅላዋን ኒቨንንም በስስት ታያታለች።

የልጇ የጤና ሁኔታ ሊከፋም ይችላል በሚል ጭንቀት ውስጥ ትመላለሳለች።

ኒቨን ገና የሰባት ወር ልጅ ናት። የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ በኋላ ሲሆን የተወለደችው።

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ልቧ ላይ ቀዳዳ ይዛ ነው ወደዚች ዓለም የመጣችው።

በጦርነቱ ምክንያት የጤና ሥርዓቱ በፈራረሰባት ጋዛ ውስጥ ልጇን በሕይወት ለማቆየት ምን ያህል ትግል እንደሆነባት እናት ስትናገር በኃዘን ነው።

ጨቅላዋ ህጻን ታለቅሳለች፤ ምቾት ነስቷት ትፈራገጣለች።

"ጦርነቱ በጣም ከብዷታል። ክብደት አልጨመረችም፤ እንዲሁ በቀላሉ ነበር የምትታመመው" ትላለች ኢናስ።

ኒቨን በሕይወት ለመትረፍ ያላት ብቸኛው ዕድል ከጋዛ ውጭ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ነበር።

እናም መጋቢት መጀመሪያ ገደማ በዮርዳኖስ ይህ ዕድል ተመቻቸላት።

የጋዛን የተኩስ አቁም ስምምነት ተከትሎ ኒቨንን ጨምሮ 29 የጋዛ ሕሙማን ወደ ዮርዳኖስ ተወስደው ሕክምና እንዲያገኙ ተደርገዋል።

የ7 ወሯ ጨቅላ ኒቨን ከእናቷ ጋር
የምስሉ መግለጫ, የ7 ወሯ ጨቅላ ኒቨን ከእናቷ ጋር
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እናቷ እና ታላቅ እህቷም አብረዋት ወደ ዮርዳኖስ አቅንተው ነበር።

የዮርዳኖስ ንጉሥ አብዱላህ 2 ሺህ የታመሙ የጋዛ ሕጻናትን በአገራቸው ሆስፒታሎች እንደሚያሳክሙ ዕቅዳቸውን ማሳወቃቸውን ተከትሎ ወደ ዮርዳኖስ ከተወሰዱት መካከል አንዷ ኒቨን ናት።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ወደ ዮርዳኖስ ለሕክምና የሚሄዱ ሕጻናት ጋር አብረዋቸው የሚጓዙ ቤተሰቦች ላይ ምርመራ ካደረጉ በኋላ ነው ጉዞው የሚደረገው።

ኒቨን በዮርዳኖስ የተሳካ የልብ ቀዶ ሕክምና ተደረገላት፤ ቀስ በቀስም ማገገም ጀመረች።

ነገር ግን ሕጻኗ ሆስፒታል ከገባች በሁለት ሳምንቷ የጋዛው የተኩስ አቁም ፈርሶ ጦርነቱ እንደገና ቀጠለ።

ልጇን እያስታመመች የነበረችው ኢናስ በጋዛ ያሉ ባለቤቷ እና ሌሎች ልጆቿ ሁኔታ አሸበራት።

ከዚያም ግንቦት 4 ምሽት ላይ ኒቨን ሕክምናዋን እንደጨረሰች እና በማግስቱም እሷና እና ቤተሰቧ ወደ ጋዛ መመለስ እንዳለባቸው በዮርዳኖስ ባለሥልጣናት ለኢናስ ተናገራት።

ኢናስ ይህንን ስትሰማ በከፍተኛ ሁኔታ ደነገጠች።

"ስንመጣ የተኩስ አቁም በነበረበት ወቅት ነው። ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ እንዴት ይመልሱናል?" ስትል እናት በብስጭት ትጠይቃለች።

ሆኖም ኢናስ ወደ ጋዛ ተመለሰች።

ኒቨን ወደ ጋዛ እንድትመለስ ከመደረጓ በፊት ሕክምናዋን ያላጠናቀቀች ሲሆን፣ ሕመሟም ሊባባስ ይችላል በሚል ወላጆቿ እየተጨነቁ ነው።

"ልጄ በጣም የከፋ ሁኔታ ላይ ናት፤ ለሞት ሊዳርጋት ይችላል" ትላላች ኢናስ።

"የልብ ሕመሟ እንዳለ ነው። አንዳንድ ጊዜ ያፍናትና ፊቷ ወደ ሰማያዊነት ይቀየራል። በዚህ ድንኳን ውስጥ ኑሮዋን ልትቀጥል አትችልም" ስትል ታስረዳለች።

ግንቦት 5 ዕለት ዮርዳኖስ 17 ሕጻናት "ህክምናቸውን ካጠናቀቁ በኋላ" ወደ ጋዛ መመለሳቸውን ዮርዳኖስ አስታውቃለች።

ሕጻናቱ በጥሩ የጤነንነት ላይ ወደ ጋዛ እንደተመለሱ የሚናገሩት የዮርዳኖስ ባለሥልጣናት ህክምናቸውን አላጠናቀቁም የሚለውን ቅሬታ ውድቅ አድርገዋል።

ሕጻናቱ ከተሻላቸው በኋላ ወደ ጋዛ የመመለስ ዕቅድ ከመጀመሪያው እንደተያዘ ባለሥልጣናቱ ይናገራሉ።

"የዮርዳኖስ ፖሊሲ ፍልስጤማውያን በመሬታቸው ማቆየት እንጂ የሚፈናቀሉበትን ሁኔታ ማገዝ አይደለም" ሲል የዮርዳኖስ መንግሥት ለቢቢሲ በላከው መግለጫ አትቷል።

ሆኖም የጋዛ የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ሕጻናቱ አሁንም ሕክምና እንደሚያስፈልጋቸው እና ወደ ጦርነት ቀጣና መመለሳቸው ሕይወታቸውን አደጋ ላይ እንደጣለው ለቢቢሲ ተናግሯል።

ወደ ጦርነት ቀጣና ለመመለስ መገደድ

የ30 ዓመቷ ኒሃያ ባሴልም ከጦርነቱ በተጨማሪ ሕመምተኛ ልጅ ይዛ እየተንገላታች ትገኛለች።

ከአንድ ዓመት ከፍ ያለው ልጇ መሐመድ በአስም እና በከባድ የምግብ አለርጂ ይሰቃያል።

ልጇ በዮርዳኖስ ተገቢውን ሕክምና እንዳላገኘ ታምናልች።

እስራኤል የጋዛ ሰርጥን በከፋ ከበባ ውስጥ ከከተተቻት አስር ሳምንታት ተቆጠሩ።

ምግብ፣ መድኃኒት፣ ነዳጅን ጨምሮ መሰረታዊ የሚባሉ አቅርቦቶች እንዳይገቡ አድርጋለች።

እስራኤል ይህንን የምታደርገው ሐማስ በጋዛ የሚገኙ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለመፍጠር ነው ትላለች።

ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶች ፍልስጤማውያን የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል በሚል እያስጠነቀቁ ይገኛሉ። እስራኤል የአሜሪካን ጫና ተከትሎ "አነስተኛ" ምግብ ወደ ጋዛ እንዲገባ እንደምትፈቅድ አስታውቃለች።

ኒሃያ ልጇን ልታሳክም ወደ ዮርዳኖስ በሄደችበት ወቅት እስራኤል ጥቃቷን አጠናክራ መቀጠሏን ተከትሎ ባሏና ሶስት ልጆቿ ከአል ሻቲ ካምፕ ሸሽተው ሄዱ።

በዮርዳኖስ ህክምና አድርጎ ወደ ጋዛ እንዲመለስ የተገደደው የአንድ አመቱ መሀመድ ከእናቱ ጋር
የምስሉ መግለጫ, በዮርዳኖስ ሕክምና አድርጎ ወደ ጋዛ እንዲመለስ የተገደደው የአንድ አመቱ መሐመድ ከእናቱ ጋር

በአሁኑ ወቅት ኒሃያ ከአማቷ ቤተሰቦች ጋር በካምፑ ውስጥ በትንሽ ድንኳን ትኖራለች።

"ልጆቼን፣ ባለቤቴን እዚህ ትቻቸው ሄድኩ። ባልነበርኩበት ወቅት ገሃነም ውስጥ ነበሩ" ትላለች ኒሃያ እንባዋን እያፈሰሰች።

"ዮርዳኖስ እያለሁ ልቤ ሁልጊዜም ከነሱ ጋር በጋዛ ነበር። ይህ ሁሉ ልጄ ሕክምና እንዲያገኝ ነው። ታዲያ ለምን ሕክምናውን ሳይጨርስ ለምን እንዲመለስ አስገደዱን?" ስትል ትጠይቃለች።

ኒሃያ ስትናገር የእስራኤል የቅኝት ድሮንም ድምጿን መሃል ላይ ሽፍን ያደርገዋል።

ወደ ጋዛ ስትመለስ ጉዞዋ በአስከፊ መከራ የተሞላ ነበር።

የጋዛ ድንበር ላይ ሲደርሱ በእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች እንደተዋከቡም ስትናገር በቁጣ ተሞልታ ነው።

"ይዘልፉን እና ይሰድቡን ጀመር። እንደሚደበድቡን አስፈራሩን። ገንዘባችንን በሙሉ ወሰዱብን። ሞባይል ስልካችንን፣ ቦርሳችንን እንዲሁም ያለንን ነገር ወሰዱብን" ስትል የምትናገረው ኒሃያ የሌሎችም ገንዘብ በእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች ተወስዷል ትላለች።

ኢናስም ተመሳሳይ ነገር እንዳጋጠማት ተናግራለች። የሕክምና ቁሳቁሷም እንዲሁም በጸጥታ ኃይሉ ተወስዷል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ ከዮርዳኖስ የሚመለሱ ፍልስጤማውያን "ከመደበኛው ገደብ በላይ ያልተገለጸ ገንዘብ በጋዛ ውስጥ ለሽብርተኝነት ጥቅም ላይ ይውላሉ" በሚል ጥርጣሬ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።

ገንዘቡ እስኪጣራ ድረስ በእስራኤል ጦር ስር እንደሚቆይ አክሎ ገልጿል።

ሌሎች ከፍልስጤማውያን የተወሰዱ የግል ንብረቶች በእስራኤል ጸጥታ ኃይሎች የተወረሱበትን ምክንያት ላይ ጦሩ የሰጠው አስተያየት የለም።

ኒሃያ ከዮርዳኖስ "ባዶ እጇን" ወደ ጋዛ እንደተመለሰች ትናገራለች።

የልጇ የሕክምና ሰነዶች እንኳን የእስራኤል የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት ቦርሳ ውስጥ እንዳሉ ለቢቢሲ አስረድታለች።