በቻይና በኮቪድ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 900 ሚሊዮን መድረሱን ጥናት አመለከተ

የቻይናን አዲስ ዓመት ለማክበር የሚጓዙ ሰዎች፣ በዚህ ወቅት በሽታው የበለጠ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, የቻይናን አዲስ ዓመት ለማክበር የሚጓዙ ሰዎች፣ በዚህ ወቅት በሽታው የበለጠ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት አለ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየተስፋፋባት እንደሆነ በተነገረባት ቻይና አስካለፈው ረቡዕ ድረስ 900 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን የፔኪንግ ዩኒቨርስቲ ጥናት አመለከተ።

በተጫማሪም የጥናቱ ሪፖርት እንደገመተው ከአገሪቱ ዜጎች መካከል 64 በመቶ የሚሆኑት ቫይረሱ አለባቸው ብሏል።

ከቻይና ግዛቶች መካከልም 91 በመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎቿ በወረርሽኙ የተያዙባት የጋንሱ ግዛት ቀዳሚ ስትሆን፣ ዩናን 84 በመቶው እንዲሁም ኪንጋሃይ 80 በመቶ ነዋሪዎቻቸው በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጿል።

በቻይና ዋነኛ የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ በዚህ ወር መጨረሻ ላይ በሚከበረው የቻይናውያን አዲስ ዓመት ወቅት ወረርሽኙ ወደ ገጠራማው የቻይና ክፍል ሊስፋፋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

የቀድሞው የቻይና የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል ኃላፊ የሆኑት ዜንግ ጉዋንግ ጨምረውም፣ የወረርሽኙ ማዕበል ከሁለት አስከ ሦስት ወራት ሊቆይ እንደሚችል ገልጸዋል።

ለበዓሉ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቻይናውያን ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይህም ለአንዳንዶቹ ከኮሮናቫይረስ ክስትት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።

ቻይና የኮሮናቫይረስን ለመቆጣጠር የምታደርገውን ጥብቅ ቁጥጥር ካቆመች በኋላ ዕለታዊ የበሽታውን መረጃ ይፋ ማድረግ ትታለች።

ነገር ግን በሽታው በመላው አገሪቱ እየስፋፋ በመሆኑ በትልልቅ ከተሞች ውስጥ ያሉ ሆስፒታሎች በኮቪድ በሽተኞች እየተጨናነቁ ይገኛሉ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቻይናዋ ማዕከላዊ ግዛት ሄናን በበሽታው የተያዙ ሰዎች ዝርዝር አሃዝን ይፋ በማድረግ ብቸኛ ስትሆን፣ ከአንድ ሳምንት በፊት የግዛቲቱ የጤና ባለሥልጣን 90 በመቶ የሚሆኑት ነዋሪዎች ኮቪድ እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን በርካታ የቻይና ግዛቶች እና ከተሞች በሽታው በከፍተኛ መጠን የሚስፋፋበትን ወቅት አልፈውታል ይላሉ።

ቻይና ከሁለት ሳምንት በፊት በድንገት ጥብቅ የወረርሽኙ መከላከያ ፖሊሲዋን በመተው፣ ባለፈው ሳምንትም ድንበሮቿን ክፍት አድርጋለች።

በበሽታው የሞቱ ሰዎች ቁጥርን በተመለከተ ከመንግሥት የሚወጣው መረጃ ባለፈው ወር በቀን አምስት እና ከዚያ በታች መሆኑን ቢያሳይም፣ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚወጡ መረጃዎች እና በቀብር ማስፈጸሚያ ስፍራዎች የሚታየው ወረፋ ግን የሚያመለክቱት ከዚህ ተቃራኒውን ነው።

ታኅሣሥ ወር ላይ የቻይና ባለሥልጣናት እንዳሉት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የኮቪድ ሁኔታ በተመለከተ በየቀኑ መረጃ ከመስጠት ይልቅ ወርሃዊ እንዲሆን አቅደዋል።

ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በኮቪድ ምክንያት የሚያጋጥመውን ሞት ይፋ ማድረግ ያቆመችው ቻይና፣ የሞት መጠኑን አሳንሳ ሪፖርት እያደረገች ነው ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ተችቷል።

ነገር ግን የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሰጡት ምላሽ፣ አገራቸው ወረርሽኙን በተመለከተ “በሕጉ መሠረት ወቅታዊ፣ በይፋዊ እና ግልጽ በመሆነ መንገድ” መረጃ እያጋራች መሆኗን ገልጸዋል።

ዓለም አቀፍ የጤና ባለሙያዎች እንደሚገምቱት በተጀመረው የፈረንጆች ዓመት ቢያንስ አንድ ሚሊዮን ሰዎች በቻይና ውስጥ ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ሊሞቱ ይችላሉ።

ቻይና የኮቪድ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ከ5,000 ብዙም ያልበለጡ ሰዎች በበሽታው መሞታቸውን ይፋ ያደረገች ሲሆን፣ ይህም በዓለም ላይ በበሽታው የሞቱ ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ከተመዘገበባቸው አገራት አንዷ አድርጓት ቆይቷል።