የዓለም ጤና ድርጅት ለልጆች በሚታዘዙ ሁለት ሽሮፖች ላይ ማስጠንቀቂያ አወጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሕንድ የተመረቱ ሁለት ሽሮፕ መድኃኒቶች በርካታ ልጆች ላይ ሞት ማጋጠሙን ተከትሎ ለልጆች እንዳይሰጡ የዓለም ጤና ድርጅት አስጠነቀቀ።
አምብሮኖል እና ዶክ-11 ማክስ የተባሉት የሕንድ ምርት የሆኑ ሽሮፖች ናቸው ኡዝቤክስታን ውስጥ የሞት ጉዳት በማስከተላቸው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው።
ድርጅቱ እንዳለው ማሪዮን ባዮቴክ በተባለ የመድኃኒት ፋብሪካ የተመረቱት እነዚህ ሽሮፖች “ከሚጠበቀው የጥራት ደረጃ በታች” መሆናቸው ተመላክቷል።
አምራቹም ቢሆን ስለመድኃኒቶቹ ደኅንነት ማረጋጋጫ መስጠት አልቻለም።
ማስጠንቀቂያው የወጣው ማሪዮን ባዮቴክ ያመረታቸውን እነዚህን ሽሮፖች የወሰዱ 18 ልጆች ኡዝቤክስታን ውስጥ መሞታቸው ከተገለጸ ከሳምንታት በኋላ ነው።
መድኃኒት አምራቹ ድርጅት አስካሁን ስለተሰጠው ማስጠንቀቂያ ምላሽ አልሰጠም።
ቢቢሲም ማሪዮን ባዮቴክ እና የሕንድ የጤና ሚኒስቴር ምላሽ እንዲሰጡ ጥያቄ አቅርቧል።
ነገር ግን ኡዝቤክስታን ውስጥ ከመድኃኒቱ ጋር በተያያዘ ሞት መከሰቱ ከተዘገበ በኋላ የሕንድ ጤና ሚኒስቴር መድኃኒት ፋብሪካው ምርቱ እንዲያቆም አድርጓል።
በዚህ ሳምንት ሰሜናዊ ሕንድ ግዛት የሆነችው እና ማሪዮን ባዮቴክ የሚገኝባት የኡታር ፕራዴሽ ግዛት የምግብ ደኅንነት ቁጥጥር መሥሪያ ቤት የፋብሪካውን ፈቃድ አግዶታል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዛሬ ሐሙስ ባወጣው ማስጠንቀቂያ ላይ እንዳለው፣ የኡዝቤክስታን ጤና ሚኒስቴር የጥራት ቁጥጥር ቤተ ሙከራ ባደረገው ምርመራ አምብሮኖል እና ዶክ-11 ማክስ በተባሉት የሳል ሽሮፖች ላይ ጎጂ የሆኑ ንጥረ ነገሮች ተገኝተዋል።
“እነዚህ መድኃኒቶች በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ አገራት ውስጥ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተፈቅደው ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም መደበኛ ከሆነው ገበያ ውጪ ወደ ሌሎች አገራት እና አካባቢዎች ተሰራጭተው ሊሆን ይችላል” ሲል የዓለም ጤና ድርጅት አስጠንቅቋል።
ጨምሮም እነዚህ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ምርቶች “ደኅንነታቸው ያልተጠበቀ ከመሆኑ በላይ በተለይ ለልጆች ከተሰጡ ከባድ ጉዳት ወይም ሞትን ሊያስከትሉ ይችላሉ” ብሏል።
ሕንድ ለዓለም ከሚቀርቡት መድኃኒቶች ውስጥ አንድ ሦስተኛውን የምታመርት በመሆኗ “የዓለም መድኃኒት ቤት” በመባል ትታወቃለች።
አብዛኞቹ ታዳጊ አገራትም መድኃኒቶችን የሚያገኙት ከሕንድ ነው።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ሕንድ በፍጥነት እያደጉ የሚገኙ ግዙፍ የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች አገር ናት።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕንድ ውስጥ ከተመረቱ መድኃኒቶች ጋር በተያያዘ በሌሎች አገራት ውስጥ በልጆች ላይ ሞት በማጋጠሙ በመድኃኒት ፋብሪካዎቹ ላይ ያለው አመለካከት አሉታዊ እየሆነ ነው።
በተመሳሳይ አንድ ሌላ የሕንድ መድኃኒት ፋብሪካ ያመረታቸው አራት የሳል ሽሮፖች አስከተሉት በተባለ የኩላሊት ጉዳት ሳቢያ 66 ልጆች ጋምቢያ ውስጥ በመሞታቸው ባለፈው ጥቅምት የዓለም ጤና ድርጅት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ አውጥቶ ነበር።
ነገር ግን የሕንድ መንግሥት እና ሜይደን የተባለው የመድኃኒቶቹ አምራች የቀረበውን ክስ አስተባብለዋል።












