ሞዛምቢክ ‘ካንሳር የሚያመጡ’ ናቸው የተባሉ የመዋቢያ ምርቶቸን በማቃጠል አስወገደች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሞዛምቢክ ባለሥልጣናት የካንሰር በሽታ ሊያመጡ ይችላሉ የተባሉ 10 ሺህ የመዋቢያ ምርቶችን በማቃጠል አስወገዱ።
ባለሥልጣናቱ ይህን ያደረጉት ከአውሮፓ ኅብረት ምርቶቹን በተመለተከ የጤና ማስጠንቀቂያ ከደረሳቸው በኋላ ነው።
በእሳት እንዲወድሙ ከተደረጉ ምርቶች መካከል የፀጉር መታጠቢያ ሻምፑዎች፣ የገላ መታጠቢያ ፈሳሽ ሳሙናዎች (ሻዎር ጄል)፣ የሰውነት ቅባቶች እና የሚረጩ መዋቢያዎች ይገኙበታል።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት ምርቶቹ የካንሰር በሽታን ሊያመጣ የሚችል ንጥረ ነገር ይዘዋል ይላሉ።
እንዲወገዱ የተደረጉት የመዋቢያ ምርቶች ሰዎችን ለበሽታ ከማጋለጣቸው በተጨማሪ፣ ማሃንነትን ጨምሮ የሥነ ተዋልዶ ጤና መቃወስን ሊያስከትሉ ይችላሉም ብለዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ከጥቂት ወራት በፊት ምርቶቹን በተመለከተ ማሳሰቢያ አውጥቶ እንደነበረ የሞዛምቢክ የመድኃኒት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ኢንስፔክተር ሺይላ ሜርሲስ ተናግረዋል።
“ምርቶቹን በማቃጠል ቢያንስ በገበያው ላይ ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትል ምርት አለመኖሩን ማረጋገጥ ችለናል” ያሉት ደግሞ የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ዳይሬክተር ፖል አጉአይር ናቸው።
እንዲወገዱ የተደረጉት የመዋቢያ መገልገያዎቹ አምራች ኩባንያዎች ከምርቶቻቸው ውስጥ የጤና ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉ ንጥረ ነገሮችን በማስወጣ ዳግሞ ወደ ምርት ተመልሰው ምርቶቹን ወደ ሞዛምቢክ ለማስገባት ጥያቄ ማቅረባቸው ተመልክቷል።
“በአውሮፓ ያሉ አምራቾች እነዚህን ንጥረ ነገሮች አስወጥተዋል። ወደፊት ወደ አገር የሚገቡት ምርቶች እነዚህ ነጥረ ነገሮች አይኖሯቸውም” ብለዋል ፖል አጉአይር።
ባለሥልጣናቱ ለጤና ጠንቅ ናቸው ያሏቸውን የመዋቢያ እና የንጽህና መጠበቂያ ምርቶችን ማስወገዳቸውን ከመናገራቸው ውጪ ስለምርቶቹ ማንነት ያሉት ነገር የለም።












