ሐሰተኛ መድኃኒት በግብፅ ሕጻናትን ገደለ

መድኃኒት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በግብፅ ሐሰተኛ አንቲባዮቲክስ የተሰጣቸው በርካታ ልጆች መሞታቸው ተገለጸ።

አንድ የሁለት ዓመት ሕጻን ከፍተኛ ሙቀት ገጥሞት ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ ሐኪሞች መርፌ ወግተውት ሕይወቱ አልፏል። ልጁ የተወጋው መድኃኒት ሐሰተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

የግብጽ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት፣ ባለፈው ወር ብቻ 160 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ሐሰተኛ መድኃኒቶች ተይዘዋል።

የሐሰተኛ መድኃኒት ስርጭት በተለያዩ አገራት እየተስፋፋ ይገኛል።

የአሜሪካው ‘ጆርናል ኦፍ ትሮፒካል ሜድስን ኤንድ ሀይጅን’ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በሐሰተኛ መድኃኒቶች በዓመት 300 ሺል ሕጻናት ይሞታሉ።

የግብፅ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ከሆነ ሴፍትሪአግዞን የተባለው አንቲባዮቲክስ ጥቅም ላይ እንዳይውል እያሳሰቡ ነው።

ካፍር ዚያት በተባለው ከተማ ፈቃድ የሌላቸው ፋብሪካዎች ላይ ፍተሻ ተደርጓል።

ሐሰተኛ መድኃኒት ከሚበዛባቸው የመድኃኒት ዓይነቶች መካከል አንቲባዮቲክስ ይጠቀሳል።

ጥቅምት ላይ በጋምቢያ ወደ 70 የሚጠጉ ሕጻናት የሕንድ ምርት የሆነ የሳል መድኃኒት ወስደው ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።

ይህንን ተከትሎ፣ የሕንድ የጤና ባለሥልጣናት የሕጻናቱ ሕይወት እንዲያልፍ ምክንያት ሆኗል የተባለውን የሳል መድኃኒት የሚያመርተው ተቋም ምርቱን እንዲያቆም ማገዷ ይታወሳል።

ከዚያ በኋላ ግን መድኃኒቶቹ ምንም ብክለት እንደሌላቸው ሕንድ ገልጻለች። የዓለም ጤና ድርጅት ግን አራት መድኃኒቶች ላይ ተቀባይነት የሌለው የተበከለ ኬሚካል እንደተገኘ አሳውቋል።