ናይጄሪያዊው ሼኽ ነብዩ መሐመድን በመሳደብ ሞት ተፈረደባቸው

ሼኽ አብዱልጀባር ናስር ካባራ

በሰሜናዊ ናይጄሪያ ካኖ ግዛት የሚገኝ የሸሪዓ ፍርድ ቤት ነብዩ መሐመድን ተሳድበዋል ያላቸውን ታዋቂ ሼኽ በስቅላት እንዲቀጡ ወሰነ።

ሼኽ አብዱልጀባር ናስር ካባራ፣ ነብዩ መሐመድን የተመለከቱ ሐሰተኛ ወሬዎችን አሰራጭተዋል ከመባላቸው በተጨማሪ ስብከታቸው ግጭት ቀስቃሽ ነው ብሏል የሸሪዓው ፍርድ ቤት።

ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በቁጥጥር ሥር ውለው የሚገኙት በርካታ ተከታይ ያላቸው ሼኽ ግን የቀረቡባቸውን ክሶች ያስተባብላሉ።

ካኖ ግዛትን ጨምሮ በበርካታ የሰሜን ናይጄሪያ ግዛቶች ከሃይማኖት እና መንግሥት ጣልቃ ገብነት ነጻ ከሆነ ሕግ ጎን ለጎን የሸሪዓ ሕግ ተግባራዊ ይደረጋል።

ናይጄሪያውያን በተለይ በካኖ ግዛት ከፍተኛ ተከታይ ያላቸውን ሼኽ የፍርድ ሂደት በትኩረት እየተከታተሉ ነው።

የ52 ዓመቱ የሃይማኖት መሪ ቃዲሪያ ከተባለ ቡድን ሲሆኑ ወላጅ አባታቸው ደግሞ እአአ በ1996 ሕይወታቸው እስኪያልፍ ድረስ በምዕራብ አፍሪካ የቡድኑ መሪ ነበሩ።

የሞት ቅጣት የተላለፈባቸው ሼኽ አብዱልጀባር ይግባኝ የማለት መብት አላቸው።

በናይጄሪያ የሞት ቅጣቶች ብዙ ጊዜ ተፈጻሚ አይሆኑም። ይልቁንም ሞት የተፈረደባቸው እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ በእስር እንዲቆዩ ይደረጋሉ።