በጅማ ዞን በ'ነብር' የተነከሱ ባልና ሚስት ሕይወታቸው አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጅማ ዞን ሸቤ ሶምቦ ወረዳ ጳጉሜ 1/ 2014 ዓ.ም ነብር ባደረሰው ጉዳት ባልና ሚስት ሕይወታቸው ሲያልፍ ሁለት የሚሊሻ አባላት ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው የወረዳው ፖሊስ ለቢቢሲ አስታወቀ።
በወረዳው የአደጋ ቴክኒክ ምርመራ አስተዳደር ረዳት ኢንስፔክተር ተረፈ ሁንዴሳ ለቢቢሲ አንደተናገሩት አደጋው የደረሰው ጳጉሜ 1/ 2014 ከቀኑ ስድስት ሰዓት አካባቢ ነው።
በዚህ የዱር አውሬ ንክሻ ሕይወታቸው ያለፈው አቶ ምቺሎ ማሞ የ65 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ ሲሆኑ ባለቤታቸው ወ/ሮ አበበች ወልደ ማርያም ደግሞ 50 ዓመታቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ባልና ሚስቱ ነዋሪነታቸው በሶምቦ ወረዳ ሸቤ ከተማ ድሬ ጉዲና ቀበሌ ልዩ ስሙ ሰበቃ የሚባል አካባቢ ሲሆን አደጋው በደረሰባቸው ዕለት ከግብርና ስራ እየተመለሱ ነበር ተብሏል።
ነብሩ በመንገድ ላይ የነበሩትን ባልና ሚስት ከሰው ግቢ በመውጣት ነክሶ አንደገደላቸው ረዳት ኢንስፔክተር ጨምረው አስረድተዋል።
“ፉአድ የሚባል የአካባቢው ልጅ የውሻ ጩኸት ሰምቶ ከቤቱ ሲወጣ በግቢያቸው ውስጥ ነብር ዛፍ ላይ ተቀምጦ ተመለከተ” የሚሉት ምክትል ኢንስፔክተር ፣ ልጁ በፍርሃት ተመልሶ በሩን በዘጋበት ወቅት ባልና ሚስት ነብሩ በታየበት ቤት አካባቢ ማለፋቸውን ይናገራሉ።
“ ባልና ሚስቱ በግቢው በኩል ወደ ቤታቸው በሚያልፉበት ወቅት ነብሩ ዘሎ ባደረሰባቸው ጉዳት ወድያውኑ ሊሞቱ ችለዋል” በማለት አሟሟታቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ይህንኑ ክስተት ተከትሎ የአካባቢው የጸጥታ መዋቅር ከማኅበረሰቡ ጋር በመሆን በዱር አውሬው ላይ ክትትል አድርገው እንደ ነበር የፖሊስ ባልደረባው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህም ወቅት በሁለት የቀበሌው የሚሊሻ አባላት ላይ የአካል ጉዳት ማድረሱን ረዳት ኢንሰፔክተር ጨምረው አብራርተዋል።
አውሬው በሚሊሻ አባላቱ ላይ ጉዳት ያደረሰው አንደኛው ግለሰብ ከተኮሰበት በኋላ መሆኑን የገለፁት ኢንስፔክተሩ ሁለቱም የሚሊሻ አባላት በአሁኑ ሰዓት በሰቃ ሆስፒታል ተኝተው ሕክምና እየተከታተሉ መሆኑን ገልፀዋል።
የዱር አውሬው ትንኮሳ ካልተፈፀመበት በስተቀር ጉዳት እንደማያደርስ ኢንስፔክተር ተረፈ አስረድተው፣ እስካሁንም በምን ምክንያት የተነሳ የአካባቢው ነዋሪዎችን ለሞት ያበቃውን ጥቃት እንዳደረሰ አለመታወቁን ገልፀዋል።
በአካባቢው እንዲህ ዓይነት የዱር አውሬ ጥቃት ያልተለመደ ሲሆን ከዚህ በኋላም ተመሳሳይ ጉዳት እንዳይደርስ የጸጥታ መዋቅሩ ክትትል እያደረገ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል።
ሸቤ ወረዳ ከጅማ ከተማ በደቡብ አቅጣጫ ወደ 50 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኝ ሲሆን የጅማ ወረዳ በለጠ ጌታ የተሰኘ ደን ይዞታን ከሚያዋስኑ ወረዳዎች መካከል አንዷ ነች።
በዚህ የደን ይዞታ ውስጥ ሕገ ወጥ ሰፈራ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን እና በዚህ የተነሳም አውሬዎች ከደኑ በመውጣት እንስሳት ላይ ጉዳት እንደሚያደርሱ ኢንስፔክተር ያስረዳሉ።
ረዳት ኢንስፔክተር ተረፈ አክለውም፣ ጫካው የበርካታ ዛፍ ዝርያዎች መገኛ እና አውሬዎች መኖርያ ነው። ስለዚህም “አጥር ቢኖረው እና ለዱር አውሬዎቹ ጥበቃ ቢደረግላቸው መልካም ነው” ብለዋል።












