ሪሺ ሱናክ ቀጣዩ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ ነው

ሪሺ ሱናክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በተሾሙ በሰባት ሳምንት ስልጣን በቃኝ ያሉትን የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመተካት በተደረገው ውድድር ሪሺ ሱናክ አሸናፊ ሆኑ።

ሪሺ ሱናክ የዩናይትድ ኪንግደም የመጀመሪያው እስያዊ ዝርያ ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ።

ሪሺ ሱናክ ዩናይትድ ኪንግደም በከፍተኛ የምጣኔ ኃብት ተግዳሮት ባለችበትም ወቅት ነው የመሪነት ቦታውን የሚረከቡት

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት ከሰባት ሳምንታት በተደረገው ፉክክር ተወዳድረው የነበሩት ሪሺ ሱናክ በሊዝ ትረስ መሸነፋቸው ይታወሳል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት ከሰባት ሳምንታት በተደረገው ፉክክር ተወዳድረው የነበሩት ሪሺ ሱናክ በሊዝ ትረስ መሸነፋቸው ይታወሳል።

ሊዝ ትረስ ግብር እቀንሳለሁ፤ ንግድን አሳልጣለሁ ያሉት አዲስ ፖሊሲ ፍጹም ያልተጠበቀ የገበያ ምስቅልቅልና ብሔራዊ ጦስ ይዞባቸው መጥቶ ነው ሥልጣን እንዲለቁ የሆኑት።

ሊዝ ትረስ ሥልጣን እንዲለቁ ጫናው ከበረታባቸው በኋላ እጅ አልሰጥም ብለው ለጥቂት ቀናት ቢፋለሙም አልሆነላቸውም።

ትረስ በይፋ በቃኝ ያሉት ባለፈው ሐሙስ ‘ነምበር ቴን’ በሚል ከሚታወቀው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር መኖርያና ቢሮ ደጅ ላይ ሆነው ነበር። 

ለ45 ቀናት ስልጣን ላይ የቆዩት ሊዝ ትረስ በዩኬ ታሪክ ለአጭር ጊዜ የቆዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመዝግበዋል። 

ሱናክ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲወዳደሩ ከሊዝ ትረስ ጋር ባደረጓቸው እልህ አስጨራሽ ክርክሮች የሊዝ ትረስ የታክስ ቅነሳ ከባድ ቀውስ ይዞ እንደሚመጣ ተምብየው ነበር። 

ያን ጊዜ ሰሚ ቢያጡም ትንቢታቸው በ45 ቀናት እውን ሆኖ ታይቷል። 

ይህንንም ተከትሎ የዩናይትድ ኪንገግደም ቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ሪሺ ሱናክን ጨምሮ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ድጋፍ ለማግኘት እየተወዳደሩ ነበር። 

በፓርቲው አሠራር መሠረት ወደ ሥልጣን የሚመጣው ሰው ቢያንስ መቶ የሕዝብ እንደራሴዎችን ድጋፍ ማግኘት አለበት።

ሪሺ ሱናክ የቀድሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አጋሮችን ጨምሮ ከፓርቲያቸው 128 የፓርላማ አባላትን ድጋፍ በመሰብሰብ ውድድሩን እየመሩም ተብሎ ነበር።

የወግ አጥባቂው ወይም በሌላ ስሙ የቶሪ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ቁጥር ደግሞ 357 ነው። 

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በ53 የድምጽ ድጋፍ ሁለተኛ ሆነው እየተከተሉ ስለመሆናቸው ቢቢሲ መረጃ አግኝቷል።

ሆኖም ቦሪስ ጆንሰን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት በድጋሚ እንደማይወዳደሩ ማስታወቃቸውን ተከትሎም ሪሺ ሱናክ ሙገሳቸውን አቅርበውላቸዋል

“ቦሪስ ጆንሰን ብሬግዚት እና የክትባት ስርጭት ላይ ስኬታማ ነበሩ” ሲሉ ሪሺ ሱናክ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል። 

“ፈታኝ ከሆኑ ጊዜያቶች በአንዱ አገራችንን መርተዋል። ፑቲን በዩክሬን የጀመሩት አረመኔያዊ ጦርነት ወቅትም ነበሩ። ለዚህም ሁሌም እናመሰግናቸዋለን።" በማለት ተናግረዋል።