ተሰናባቿ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር 115ሺህ ፓውንድ አበል እንዳይወስዱ ጥሪ ቀረበ

ሊዝ ትረስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተሰናባቿ ሊዝ ትረስ

በተሾሙ በ45 ቀናት በቃኝ ያሉት የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሚሰጠውን ልዩ የገንዘብ ጥቅም እሺ ብለው እንዳይቀበሉ ጥሪ ቀረበ።

ይህን ጥሪ ያቀረቡት የተለያዩ ፓርቲ አባላትና የሕዝብ እንደራሴዎች ናቸው።

የሌበር ፓርቲ ሊቀ መንበር ሰር ኪር ስታመር እንደተናገሩት ሊዝ ትረስ በዓመት 115ሺህ ፓውንድ ይገባኛል ማለት የለባቸውም።

ሊዝ ትረስ ግብር እቀንሳለሁ፤ ንግድን አፋፍማለሁ ያሉት አዲስ ፖሊሲ ፍጹም ያልተጠበቀ የገበያ ምስቅልቅልና ብሔራዊ ጦስ ይዞባቸው መጥቶ ነው ሥልጣን እንዲለቁ የሆኑት።

ሊዝ ትረስ ሥልጣን እንዲለቁ ጫናው ከበረታባቸው በኋላ እጅ አልሰጥም ብለው ለጥቂት ቀናት ቢፋለሙም አልሆነላቸውም።

ትረስ በይፋ በቃኝ ያሉት ባለፈው ሐሙስ ‘ነምበር ቴን’ በሚል ከሚታወቀው የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር መኖርያና ቢሮ ደጅ ላይ ሆነው ነበር።

ይህን ያወጁበት ቀን ከተሾሙበት ቀን ተነስቶ ሲሰላ 45 ቀናት ብቻ ይሆናል።

ማንኛውም የቀድሞ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር የሕዝብ አገልግሎት አበል በሚል የሚታወቀውን ጥቅማ ጥቅም ማግኘት መብት አለው።

ይህ መብት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም ሚኒስትሯ ለምን ያህል ጊዜ በዚህ ሥልጣን መቆየት እንዳለባቸው ዝቅተኛውን የጊዜ ገደብ አያስቀምጥም።

የሌበር መሪ ኪር ስታመር የሚሉት ግን ሊዝ ይህን አበል ይገባኛል ለማለት ብቁ አይደለችም ነው።

ይህን እንዲሉ ያስቻላቸው የዚህ አበል ዋና ግብ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በሕዝብ አገልግሎት ቆይተው ሰንብተው ከሥልጣን ሲለቁ ተሳትፏቸውን እንዲቀጥሉ ለማስቻል የሚከፈል ስለሆነ ነው።

ሰር ኪር ስታመር ጨምረው ለቢቢሲ ሲናገሩ፣ "ሊዝ ትረስ ይህን ገንዘብ ውሰጂ ብትባልም ይቅርብኝ ነው ማለት ያለባት፤ 44 ቀናት ቢሮ ተቀምጦ 115 ሺህ ፓውንድ በየዓመቱ ይገባኛል ማለት ስሜት አይሰጥም" ብለዋል።

የሊበራል ዲሞክራት ፓርቲ መሪ ኤድ ዴቪም እንደ ሰር ኪር ስታመር ሐሳባቸው መሳ ለመሳ ነው።

በምንም ሁኔታ ሊዝ ትረስ በዓመት ይህን ያህል ገንዘብ ሊከፈላቸው አይገባም ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጥቅማ ጥቅም ምን ያካትታል?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሚሰጥ ልዩ ጥቅማ ጥቅም እንደነርሱ አቆጣጠር በ1991 መጋቢት ወር ላይ በዚያን ጊዜ መሪ የነበሩት ጆን ሜጀር የወጠኑት ነው።

ይህም ዝነኛዋ ማርጋሬት ታቸር ሥልጣን በለቀቁ ማግስት ነበር የሆነው።

ሐሳቡ የነበረው የሕዝብ አገልግሎት የሰጡ መሪዎች በቀጣይ ሕይታቸውም ሕዝባዊ አገልግሎቶች ላይ ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማገዝ ነበር።

ስለዚህም ነው ይህ ገንዘብ በዋናነት ይህን ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያስቸሏቸውን ወጪዎች በመሸፈን ላይ ያተኮረው።

ገንዘቡ በብዛት ለጉዞ፣ ለጸሐፊና ረዳቶቻቸው ደመወዝ እና ሌሎች ወጨዎች የሚውል ተደርጎ ነው የሚታሰበው።

ይህ ልዩ ጥቅም እንደ መጦሪያ ወይም ደግሞ ቀጥተኛ ክፍያ ተደርጎ እንዲወሰድም አይፈለግም።

ይሁንና ማንኛውም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ይህን ጥቅም የመጠየቅ መብቱ የተጠበቀ ነው።

ቶኒ ብሌየር፣ ጎርደን ብራውን፣ ዳቪድ ካሜሮን እና ቴሬሳ ሜይ ይህን አበል ወስደዋል፤ እየወሰዱም ነው።

ቦሪስ ጆንሰን ግን ይህን ልዩ ገንዘብ እየተቀበሉ ስለመሆኑ እስከአሁን መረጃ አልወጣም።

ከ2011 ጀምሮ ይህ 115ሺህ ፓውንድ ገንዘብ መጠን እንዳይጨምር ተደርጓል።

ገንዘቡ እስከ ሕይወት ዘመን ቢሆንም በቀጥታ በገንዘብ የሚሰጥ አይደለም፤ ወጪ የተደረገባቸው ደረሰኞች እየቀረቡ የሚወራረድ እንጂ።

ብዙውን ጊዜ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በየዓመቱ ይህን ሙሉ ብር ላይወስዱ ይችላሉ። ከዚያ ይልቅ እንደ ወጪያቸው ከፍና ዝቅ ማለት የሚወስዱት መጠንም ሊለያይ ይችላል።

ከዚህ ሌላ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በተለየ ሁኔታ ሥልጣን ሲለቁ ሰቨራንስ የሚባል ክፍያን መጠየቅ ይችላሉ። ይህ ክፍያ የዓመት ደመዛቸውን 25 ከመቶ በአንድ ጊዜ መውሰድ የሚያስቸላቸው ነው።

አሁን የአንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓመታዊ ደመወዝ 79ሺህ ፓውንድ ነው። በዚህ ስሌት መሠረት የአንድ ጊዜ ክፍያው 19ሺህ ፓውንድ ይሆናል።

ቶኒ ብሌየር በ2020 እና በ2021 ሙሉ ገንዘብ የወሰዱ ሲሆን፣ ጎርደን ብራውን ግን 114ሺህ 712 ፓውንድ ነው የወሰዱት።

ዴቪድ ካሜሮን በበኩላቸው 113ሺህ 423 ፓውንድ ወስደዋል። ቴሬሳ ሜይ በአንጻሩ በዚያው ዓመት የወሰዱት 57ሺህ 382 ፓውንድ ብቻ ነበር።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ከዚህ ገንዘብ ጥቅም ሌላ ለረዳቶቻቸው የገንዘቡን 10 ከመቶ የጡረታ መዋጮ መጠየቅ ይችላሉ።