በማላዊ የጅምላ መቃብር ከተገኘ በኋላ የአገሪቱ ፖሊስ 72 ኢትዮጵያውያንን ያዘ

ሰንሰለት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በማላዊ 25 ኢትዮጵያውያን ያሉበት የጅምላ መቃብር መገኘቱን ተከትሎ የአገሪቱ ፖሊስ 72 ኢትዮጵያውያንን ማሰሩ ተገለጸ።

የማላዊ ፖሊስ 72 ኢትዮጵያውያን ወንዶችን ያሰረው ደን ውስጥ ተደብቀው ከተገኙ በኋላ ነው።

በማላዊ ሰሜናዊ ግዛት በምትገኘው ካሮንጋ ግዛት የሚገኝ ጥብቅ ደን ውስጥ ተደብቀው የተገኙትን ኢትዮጵያውያን ፖሊስ መያዙን ገልጿል።

በተያያዘም አሥር የማላዊ ዜጎች ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በማዘዋወር እጃቸው እንዳለበት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ ፖሊስ አክሏል።

ከሁለት ቀናት በፊት ምዚምባ በተባለ የማላዊ ግዛት በሚገኝ ጥብቅ ደን ውስጥ የ25 ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አስክሬን ያለበት የጅምላ መቃብር መገኘቱ አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ለቢቢሲ፤ ኢትዮጵያ ከማላዊ መንግሥት ጋር በመተባበር ስለ ክስተቱ ምርመራ እያደረገች ነው።

አምባሳደር መለስ ዓለም በክስተቱ ሀዘን እንደተሰማቸው ገልጸው፣ የምርመራውን ውጤት ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

72ቱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በፖሊስ የተያዙት የጅምላ መቃብሩ ከተገኘበት 300 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኘው ጥብቅ ደን ውስጥ ተደብቀው ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የአካባቢው ወጣቶች ማር ለመቁረጥ ወደ ጥብቅ ደኑ ሲገቡ አስክሬኖቹ እንደሸተቷቸው፣ ከዚያም የተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን እንዳገኙ ተገልጿል።

ወጣቶቹ ያዩትን ለአካባቢው ሽማግሌዎች ካሳወቁ በኋላ፣ ሽማግሌዎቹ ለፖሊስ አስታውቀው የጅምላ መቃብሩ እንደተገኘም ተገልጿል።

ይህ በሆነ በማግሥቱ በዛው አካባቢ ሌላ የጅምላ መቃብር ተገኝቷል። በሁለተኛው የጅምላ መቃብር አራት አስክሬኖች ተገኝተዋል።

የማላዊ የአገር ውስጥ ሚኒስትር ጄን ሴንዴዛ፣ ሁለቱንም የጅምላ መቃብሮች ከጎበኙ በኋላ፣ ሰዎቹ በምን ምክንያት እንደሞቱ ለማወቅ የአስክሬን ምርመራ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

“በስፍራው የተገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ተጎጂዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው” ሲል የማላዊ ፖሊስ ባወጣው መግለጫ አብራርቷል።ሁሉም ዕድሜያቸው ከ25 እስከ 40 እንደሆነና በምን ምክንያት እንደሞቱ ምርመራ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተገልጿል።

72ቱ ኢትዮጵያውያን እና አሥሩ የማላዊ ዜጎች ከሰሞኑ ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ፖሊስ አስታውቋል። ከሰው ዝውውር እና የስደተኞች ሕግጋትን መተላለፍ ጋር የተያያዙ ክሶች እንደሚቀርቡባቸው አክሏል።

ከዚህ ቀደምም የስደተኞች አስክሬን በማላዊ እና ሞዛምቢክ ተገኝቷል።

ማላዊ ውስጥ የሰዎች ዝውውር ፈታኝ እየሆነ መጥቷል። በሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካይነት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል።

ባለፈው ሚያዝያ 140 ሕገ-ወጥ ስደተኞችን የማላዊ ፖሊስ አስሯል። ከእነዚህ 133ቱ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ፣ ስድስቱ የባንግላዴሽ አንዱ ደግሞ የፓኪስታን ዜጎች ናቸው።

ማላዊ ውስጥ የሚያዙ አብዛኞቹ ስደተኞች በማላዊ በኩል ወደ ደቡብ አፍሪካ፣ አውሮፓ እና አሜሪካ የሚሻገሩ መሆናቸው በተደጋጋሚ ይገለጻል።

ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በማላዊ ለብዝበዛ የተጋለጡበት ድዛሌካ የስደተኞች መጠለያ

የፎቶው ባለመብት, UN

የምስሉ መግለጫ, ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በማላዊ ለብዝበዛ የተጋለጡበት ድዛሌካ የስደተኞች መጠለያ

ያለፈው ሰኔ የመንግሥታቱ ድርጅት ባወጣው መግለጫ በማላዊ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በርካታ የሕገ ወጥ ሰዎች ዝውውር ሰለባ የሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሚገኙና ብዝበዛ እንደሚደርስባቸውም ማስታወቁ አይዘነጋም።

ድዛሌካ በተሰኘው የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ በወንዶች፣ በሴቶች እና በሕጻናት ላይ መጠነ ሰፊ ብዝበዛ እንደሚደርስ ይፋ የተደረገው በተባበሩት መንግሥታት የመድኃኒት እና የወንጀል ጽሕፈት ቤት (ዩኤንኦዲሲ) እና የማላዊ ፖሊስ ባደረጉት የጥምረት ክትትል ነው።

ተቋሙ ከ90 በላይ ሰለባዎችን መታደጉን ገልጾ፣ አብዛኛዎቹ ከ18 እስከ 30 ዓመት የሚሆናቸው ኢትዮጵያውያን ወንዶች ናቸው ብሏል።

ሌሎቹ ደግሞ ከ12 እስከ 24 ዕድሜ ያሉ ታዳጊዎችና ሴቶች ሲሆኑ የኢትዮጵያ፣ የብሩንዲ እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ዜጎች ናቸው።