ሪሺ ሱናክ ቀጣዩ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ውድድሩን እየመሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በተሾሙ በ45 ቀናት ስልጣን በቃኝ ያሉትን የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስን ለመተካት የሚደረገው ውድድር ቀነ ገደብ ተቃርቧል።
በዚህ ውድድር ላይ የድጋፍ ድምፅ በማግኘት ሪሺ ሱናክ ቢመሩም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ደጋፊዎች ተስፋቸው ከፍ እንዳለ ነው።
የውድድሩ ቀነ ገደብ በተቃረበበት በዚህ ወቅት ከፍተኛ ስፍራ የተሰጣቸው ሁለቱ ተወዳዳሪዎች ቦሪስ ጆንሰን እና ሪሺ ሱናክ ተወያይተዋል።
ውይይቱ መካሄዱን ሁለት የተለያዩ ምንጮች ለቢቢሲ ቢናገሩም ሁለቱም ፖለቲከኞች ስለተወያዩባቸው ጉዳዮች ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ሪሺ ሱናክ የቀድሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን አጋሮችን ጨምሮ ከፓርቲያቸው 128 የፓርላማ አባላትን ድጋፍ በመሰብሰብ ውድድሩን እየመሩ ይገኛሉ።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በ53 የድምጽ ድጋፍ ሁለተኛ ሆነው እየተከተሉ ስለመሆናቸው ቢቢሲ መረጃ አግኝቷል።
ሆኖም ደጋፊዎቻቸው ወደ ውድድሩ ለመግባት የሚያስፈልገው የድምፅ ድጋፍ እንዳላቸው በመጥቀስ 100 የፖርላማ አባላት የድጋፍ ድምጽ እንዳገኙ ይከራከራሉ።
የሪሺ ሱናክ ደጋፊዎች በዚህ ላይ ጥርጣሬ ያላቸው ሲሆን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ማስረጃ እንዲያሳዩም ጠይቀዋል።
ፔኒ ሞርዳውንት ውድድሩ መቀላቀላቸውን በይፋ ያሳወቁ ብቸኛ እጩ ናቸው ነገር ግን በ23 የፓርላማ አባላት ድጋፍ ወደ ኋላ ቀርተዋል።
የቢቢሲዋ ላውራ ኩንስስበርግ ቦሪስ ጆንሰን እና ሪሺ ሱናክ ቅዳሜ አመሻሹ ላይ ተገናኝተው እንደነበር ገልጻ ነገር ግን በውይይታቸው ላይ መግለጫ ይወጣ እንደሆነ እርግጠኛ አልነበረችም።
ቢቢሲ ድጋፍ የሰጡ የፓርላማ አባላትን መረጃ ሲሰበስብ ቆይቷል።
ከ357 ወግ አጥባቂ የፓርላማ አባላት መካከል የ204ቱ የመምረጥ ፍላጎታቸው የሚታወቅ እና በቢቢሲ የተረጋገጠ ሲሆን በርካቶች አሁንም ገና ፍላጎታቸውን አልገለጹም።
ለውድድሩ በቂ ድጋፍ ለማግኘት እስከ ፊታችን ሰኞ 8 ሰዓት ድረስ ጊዜ አላቸው።
በዚህም ለሚቀጥለው የውድድር ደረጃ ብቁ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።
የፓርቲው የፓርላማ አባላት አንድ እጩን ብቻ የሚደግፉ ከሆነ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ዩናይትድ ኪንግደም አንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊኖራት ይችላል።
ካልሆነ ግን የወግ አጥባቂ ፓርቲ አባላት ምርጫ በኦንላይን የሚያካሂዱ ሲሆን ውጤቱም በመጪው ሳምንት አርብ ይፋ ይሆናል።
የምርጫ አስተያየቶች እንደሚያሳዩት በዚህ ኦንላይን ምርጫ ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን የአባላቱን ድምጽ ሊያሸንፉ እንደሚችሉ ነው።












