ሊዝ ትረስን ማን ሊተካቸው ይችላል?

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሊዝ ትረስ ከ45 ቀናት በኋላ ሥልጣን ለቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ያስገደዳቸው የምጣኔ ሃብት ምስቅልቅል በመፈጠሩ ነው።
ይህን ተከትሎ ወግ አጥባቂው ፓርቲ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ ይገደዳል።
ሊዝ ትረስ እርሳቸውን የሚተካ እጩ በሚቀጥለው ሳምንት እስከ ዐርብ ድረስ እንደሚመረጥ ጠቁመዋል።
የገዛ የፓርቲ አባላቶቻቸው ሊዝ ትረስ ሥልጣን እንዲለቁ ከፍተኛ ጫና አድርገውባቸዋል።
እየተመሰቃቀለ የመጣውን ኢኮኖሚ መልክ እንዲያሲዙላቸው ሊዝ ትረስ ሰሞኑን የሾሟቸው ቻንስለር ጀረሚ ሐንት በቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሆን ሰፊ ዕድል የነበራቸው ቢሆንም ‘አልወዳደርም’ ብለዋል።
ከሊዝ ትረስ በፊት ሥልጣን የለቀቁት ቦሪስ ጆንሰን ግን በድጋሚ ሊወዳደሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለ።
ምክር ቤት የገቡ የወግ አጥባቂው ፓርቲ አባላት ሊዝ ትረስ አሳካዋለሁ ብለው የወጠኑት የታክስ ቅነሳ ያልታሰበ ምስቅልቅል ካስከተለ በኋላ ፊታቸውን አዙረውባቸው ቆይተዋል።
ሊዝ ትረስ በዳውኒንግ ስትሪት ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፓርቲያቸው የመረጣቸው ከፍተኛ የታክስ ቅነሳን ተግባራዊ አድርገው ከፍተኛ የኢኮኖሚ መነቃቃት ታመጣለች ብሎ ስላመነ እንደሆነ አስታውሰው ይህን ማሳካት አልቻልኩም፤ ስለዚህ ሥልጣን መልቀቅን መርጫለሁ ብለዋል።
የሌበር ፓርቲ መሪ ኪር ስታመር የሊዝ ትረስን መልቀቅ ተከትሎ ጠቅላላ ምርጫ ይደረግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ሊዝ ትረስ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እስኪመረጥ በቦታቸው እንደሚቆዩ ተናግረዋል።
ቀጣዩ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትርና የወግ አጥባቂው ፓርቲ መሪ ማን ይሆናል የሚለው አሁን በስፋት እያነጋገረ ነው።
የፓርቲው ምንጮች ለቢቢሲ እንደተናገሩት የቢዝነስ ሚኒስትሩ ጃኮብ ሞግ እንደራሴዎች ከወዲሁ ለቦሪስ ጆንሰን ድጋፍ እንዲሰጡ ማግባባትን ይዘዋል።
በፓርቲው አሠራር መሠረት ወደ ሥልጣን የሚመጣው ሰው ቢያንስ መቶ የሕዝብ እንደራሴዎችን ድጋፍ ማግኘት አለበት።
የወግ አጥባቂው ወይም በሌላ ስሙ የቶሪ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት ቁጥር ደግሞ 357 ነው።
ይህ ማለት እጩ ሊሆኑ የሚችሉት ቢበዛ ሦስት የፓርቲ ሰዎች ብቻ ናቸው። ብዙውን ጊዜ ከአንድ በላይ እጩ ሁሉ ላይኖር ይችላል።
ይህ ከሆነ ደግሞ ድምጽ መስጠትም አስፈላጊ አይሆንም።
ይሁንና 357 የምክር ቤት አባላት መቶ- መቶ እየሆኑ ሦስት የተለያዩ እጩዎችን ደገፉ ቢባል ሦስት እጩዎች ሊኖሩ ይችላል።
ይህ ከተከሰተ ቀጣዩ አሠራር ድምጽ መስጠት ይሆናል።
በመጀመርያው የኮሮጆ ድምጽ አሰጣጥ ከሦስት አጩዎች ዝቅተኛ ድምጽ ያገኘው ይሰናበታል። ሁለተኛው ድምጽ አሰጣጥ ደግሞ በኦንላይን ይደረግና ከፍተኛ ድምጽ ያገኘው ይመረጣል።
ለ45 ቀናት ስልጣን ላይ የቆዩት ሊዝ ትረስ በዩኬ ታሪክ ለአጭር ጊዜ የቆዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመዝግበዋል።
ጆ ባይደን እና ኢማኑኤል ማክሮን፤ ሊዝ ትረስ በአጭር ቆይታቸው ላሳዩት የትብብር መንፈስ አመስግነዋል።
ሊዝ ትረስ በትናንቱ መግለጫቸው እርሳቸው ወደ ሥልጣን የመጡት ከባድ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በሰፈነበት ጊዜ መሆኑ ቆይታቸውን ፈታኝ እንዳደረገባቸው ጠቅሰዋል።
በተለይ የዩክሬን ጦርነት፣ የኑሮ መናርና የተተበተቡ ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮች ያሰቡትን ለማሳካት እንዳላስቻላቸው አውስተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በቀጣይ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በግልጽ ፍላጎቱን የገለጸ እጩ እስከአሁን ባይኖርም ቦሪስ ጆንሰንን ለመተካት ከሊዝ ትረስ ጋር እስከመጨረሻው ዙር ድረስ ተወዳድረው የተሸነፉት ሪሺ ሱናክ ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው መካከል ናቸው።
ሱናክ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲወዳደሩ ከሊዝ ትረስ ጋር ባደረጓቸው እልህ አስጨራሽ ክርክሮች የሊዝ ትረስ የታክስ ቅነሳ ከባድ ቀውስ ይዞ እንደሚመጣ ተምብየው ነበር።
ያን ጊዜ ሰሚ ቢያጡም ትንቢታቸው በ45 ቀናት እውን ሆኖ ታይቷል።
ከሱናክ ሌላ የንግድ ሚኒስትሩ ኬሚ እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ተገምተዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ቤን ዋለስ፣ በዩኬ ታሪክ የመጀመርያዋ ሴት መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ፔኒ ሞርዶንት ስማቸው እየተነሳ ነው።
አንዳቸውም ግን ፍላጎታቸውን በግልጽ አላሳዩም።
የሌበር ፓርቲ ሊቀ መንበር በበኩላቸው ወግ አጥባቂው ፓርቲ ከዚህ በኋላ አገሪቱን የመምራት ሞራል ሊኖረው አይችልምና ጠቅላላ ምርጫ ነው መደረግ ያለበት ብለዋል።
ይሁንና ወግ አጥባቂው ፓርቲ በ2019 በከፍተኛ ብልጫ ያሸነፈ ፓርቲ በመሆኑ እስከ 2024 በዩኬ ጠቅላላ ምርጫ አይደረግም።
የሊበራል ዲሞክራት ፓርቲ በበኩሉ ሊዝ ትረስ ከሥልጣን ከተሰናበቱ በኋላ ለቀድሞ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትሮች የሚሰጠውን ጥቅማ ጥቅም እንዳይቀበሉ ጠይቋል።
45 ቀን አገር መርቶ ይህን ሁሉ ጥቅማ ጥቅም መቀበል ነውር ነው ሲል ድምጽ አሰምቷል።
ሊዝ ከዚህ በኋላ ሌሎች በርካታ ጥቅማ ጥቅሞችን ሳይጨምር በየዓመት 115ሺህ ፓውንድ አበል እየተከፈላቸው መኖር ይችላሉ።
ይህም ዕድሜ ዘመናቸውን የሚያገኙት አበል ይሆናል።












