አንድ ሚሊዮን ዶላር ቤታቸው ተገኝቷል የተባሉት የጋናዋ ሚኒስትር ሥልጣን ለቀቁ

የቅንጡ መኪናዎች ስብስብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ግለሰቦች በሰረቁት ገንዘብ መኪና እና ሌሎች ቁሳቁሶች ገዝተዋል ተብለው ተወቀስዋል

የጋናው ፕሬዝዳንት በርካታ ገንዘብ ቤታቸው አሽገው አስቀምጠዋል የተባሉት ሚኒስትር ያስገቡን የሥራ መልቀቂያ ተቀበሉ።

የጋና የንፅሕና እና ውሃ ሐብት ሚኒስትር ሲሲሊያ አቤና ዳፓ መጠኑ የገዘፈ ገንዘብ ቤታቸው ተገኝቷል መባሉን ተከትሎ ወቀሳ ዘንቦባቸዋል።

በዋና ከተማዋ አክራ የሚኖሩት ሚኒስትር የቤት ሠራተኞች ከአንድ ሚሊዮን ዶላር በላይ ሰርቀዋል ተብለው ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ነገር ግን ብዙዎችን ያስገረመው ሠራተኞች በስርቆት መጠርጠራቸው ሳይሆን ሚኒስትሯ ይህን ሁሉ ገንዘብ ከየት አመጡት የሚለው ነው።

የቤት ሠራተኞች አንድ ሚሊዮን ዶላር ጥሬ ገንዘብ፣ 300 ሺህ ዩሮ፤ በርካታ ሚሊዮን የጋና ሴዲ እንዲሁም ቁሳቁስ በመስረቅ ተጠርጥረዋል።

የሕዝብ እንደራሴዎች ገንዘቡ ከየት እንደመጣ እንዲጣራ ምርምራ ይካሄድ ሲሉ ጠይቀዋል።

ሚኒስትሯ “ለሚደረገው ምርመራ ሁሉ ሙሉ ድጋፌን ለመስጠት ቃል እገባለሁ፤ እውነታውን አስረዳለሁ” ብለዋል።

የጋና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዕድሜያቸው 18 እና 30 ነው የተባሉት የቤት ሠራተኞች ከሚኒስትሯ ገንዘብ እና ሌሎች ውድ ዕቃዎችን የሰረቁት ባለፈው ዓመት መሆኑን ዘግበዋል።

ሁለቱ የቤት ሠራተኞች ወንጀል ለመፈፀም በማሴርና በስርቆት ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል።

ከዚህ ወንጀል ጋር በተያያዘ ሌሎች ሶስት ግለሰቦች ክስ እንደተመሰረተባቸው ተገልጧል።

ግለሰቦች በሰረቁት ገንዘብ መኪና እና ሌሎች ቁሳቁሶች መግዛታቸው ተገልጿል።

አክራ የሚገኘው ፍርድ ቤት ከተከሳሾቹ መካከል አንዷ የምታጠባ እናት ስለሆነች የዋስትና መብቷ እንዲጠበቅ የፈቀደ ሲሆን ቀሪዎቹ አራቱ ግን ማረሚያ ቤት ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ ወስኗል።

የስርቆቱ ዜና ከተሰማ በኋላ በርካታ ጋናውያን ሚኒስትሯ ይህን ያህል በርካታ ገንዘብ እንዴት በመኖርያ ቤታቸው ሊቀመጥ ቻለ ሲሉ ጠይቀዋል።

በጋና ዋነኛ ተቃዋሚ የሆኑት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ማሀማ በትዊተር ገፃቸው “ገራሚ ነገር” ሲሉ ተሳልቀዋል።

“ይህ ወንጀል እውነት ተፈጽሞ ቢሆን እንኳ ስለምን ይህን ያህል መጠን ያለው ጥሬ ገንዘብ ቤት ውስጥ ማስቀምጥ አስፈለገ? ፕሬዝዳንት አኩፎ አዶ በሥራቸው ላሉ የሕዝብ አገልጋዮች መልካም ምሳሌ መሆን ይችሉ ይሆን?” ሲሉ ጠይቀዋል።

በፈረንጆቹ 2013 የጋና ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት፣ ቪክቶሪያ ሐማ 1 ሚሊዮን ዶላር እስኪያካብቱ ድረስ ሥልጣን እንደማይለቁ የገለፁበት የድምጽ ቅጂ በመገኘቱ ከመንበራቸው እንዲነሱ ተደርጎ ነበር።