በኒጀር የሩሲያ ወታደሮች የአሜሪካ ወታደሮች የሚገኙበት ጦር ሰፈር ገቡ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በኒጀር የሩሲያ ወታደሮች የአሜሪካ ወታደሮች የሚገኙበት የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ገቡ።
ይህ የሆነው የኒጀር ወታደራዊ አመራር አሜሪካ በአስቸኳይ ከአገራቸው እንድትወጣ ማዘዛቸውን ተከትሎ ነው።
የአሜሪካ ወታደሮች በቀጠናው ኢስላማዊ አሸባሪዎችን ለመዋጋት ነበር በዚያ የተሰማሩት።
ስለ ክስተቱ ለሮይተርስ ዜና ወኪል ቃላቸውን የሰጡ የአሜሪካ ባለሥልጣናት፣ የሩሲያ ወታደሮች በኒጀር ዋና ከተማ ናየሚ በሚገኝ የአየር ኃይል ጦር ሰፈር መግባታቸውን አረጋግጠው፤ ነገር ግን ከአሜሪካ ወታደሮች ጋር አልተቀላቀሉም ብለዋል።
ሐዋይ የሚገኙት የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስቲን የሩሲያ ወታደሮች በአሜሪካ ወታደሮች ላይ የደቀኑት አደጋ የለም ብለዋል።
“የሩሲያ ወታደሮች በተለየ ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው ያሉት። የአሜሪካንን ሠራዊት ቁሳቁስ ወይም መሣሪያዎቹን ማግኘት አይችሉም” ብለዋል ከሐዋይ ግዛት፣ ሆኖሉሉ ከተማ በሰጡት አስተያየት።
ሎይድ፣ የሩሲያዊያን ወደ ኒጀር መግባት በአሜሪካ ወታደሮች ላይ የተደቀነ ምንም ዓይነት አደጋ የለም ሲሉ በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ኒጀር በአፍሪካ ሳህል አካባቢ የምትገኝ አገር ስትሆን የኢስላሚክ ስቴት ዋና ማዕከል እየሆነች ነው የሚል ስጋት አለ።
አሜሪካ የጦር ሰፈሩን የኢስላሚክ ስቴትን እንቅስቃሴዎች ለመቆጣጠር ነበር የምትጠቀምበት። ነገር ግን ከአዲሱ የኒጀር ወታደራዊ መንግሥት ጋር ያላት ግንኙነት እየተበላሸ በመሄዱ አገሪቱን ለቃ እንድትወጣ ተነግሯታል።
በአሜሪካ ምትክ የኒጀር ወታደራዊ ኃይል ሩሲያን ወደ አገሩ ጋብዟል።
የሩሲያ ወታደሮች ተግባርም የኢስላሚስ ስቴት እንቅስቃሴዎችን መግታት ይሆናል።
ሩሲያዊያኑ አሁን ያረፉበት ቦታ የአሜሪካ ወታደሮች ከሚገኙበት ሰፈር ቅርብ ነው።
ሮይተርስ እንዳለው የኒጀር አመራሮች 60 የሩሲያ ወታደሮች ወደ አገሪቱ እየመጡ እንደሆነ አስቀድመው ተናግረዋል።
ሆኖም ይህ አሐዝ ትክክል ይሁን የመታወቅ ነገር የለም።
አሁን በዋና ከተማዋ በሚገኘውና ‘’ቀጠና 101’’ ተብሎ በሚጠራው የአየር ኃይል ጦር ሰፈር ምን ያህል አሜሪካዊያን ወታደሮች እንዳሉ በውል የተባለ ነገር የለም።
በሩሲያና አሜሪካ መካከል ያለው መቃቃር ፑቲን በየካቲት 2022 ዓ/ም ዩክሬንን መውረራቸውን ተከትሎ ወደ ከፋ ደረጃ ደርሷል።
አሜሪካ ዩክሬንን ለመታደግ በቢሊዮን ዶላሮች ስንቅና ትጥቅ ከማቅረብ ባሻገር ምዕራብ አገራትን በማስተባበር ትታወቃለች።
የምዕራብ አፍሪካ ተንታኝ የሆኑት ፖል ሜሊ የሩሲያና አሜሪካ ወታደሮች በኒጀር በአንድ የጦር ሰፈር መቀመጣቸው እስከአሁን የፈጠረው ስጋት የለም ይላሉ።
ሜሊ እንደሚሉት አሜሪካ ወታደሮቿ በኒጀር እንዲቆዩ ከፍተኛ ጥረት ብታደርግም የኒጀር ወታደራዊ አመራር ግን ፍቃደኛ አልሆነም። ይህም በዋናነት አሜሪካ በኒጀር ወታደራዊ አመራሩ ወደ ሲቪል አመራር እንዲቀየር መጠየቋን ተከትሎ የመጣ ነው።
ሩሲያ በበኩሏ ሲቪል ካልሆነ አመራር ጋር ለመሥራት ምንም የምታስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ የለም።
አሜሪካ በአስቸኳይ አገራቸውን ለቃ እንድትወጣ ኒጀር ያሳሰበችው ባለፈው ሚያዝያ ወር ነበር።
የወታደራዊ አመራሩ ቃል አቀባይ ኮ/ል አማዱ ኒጀር ከማን ጋር መሥራት እንዳለባት አሜሪካ ልትመርጥ አትችልም ሲሉ ተችተው ነበር።
የወታደራዊ ተንታኙ ሜሊ እንደሚሉት ሩሲያ ለኒጀርም ሆነ ለማሊ ወይም ለቡርኪናፋሶ ምዕራባዊያንን ጠቅልለው ከአገራቸው እንዲያስወጡ ስለመጠየቃቸው የተጨበጠ መረጃ የለም። ሆኖም ግን ሩሲያዊያን የተፈጠረውን ዕድል ከመጠቀም ወደ ኋላ አላሉም።
በሳህል አካባቢ ከኒጀር ሌላ በርካታ አገሮች ከሩሲያ ጋር ወዳጅነታቸውን ማደርጀት ጀምረዋል።
በቅርቡ ከፈረንሳይ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የቆረጡ አገራትም ወደ ሩሲያ አማትረዋል።
የአሜሪካ ወታደሮች በቻድ ተመሳሳይ እጣ ገጥሟቸው ነበር። ማሊና ቡርኪናፋሶ በበኩላቸው የቀድሞ ቅኝ ገዢያቸው የነበረችውን ፈረንሳይን ማሰናበታቸው አይዘነጋም።












