የቀድሞው የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር 12 ዓመታትን በእስር ሊያሳልፉ ነው

የቀድሞ የማሌዢያ ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ራዛክ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የቀድሞ የማሌዢያ ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ራዛክ

የቀድሞው የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ራዛክ ለፍርድ ቤት ያቀረቡት አቤቱታ ውድቅ መሆኑን ተከትሎ ከዚህ ቀደም ተላልፎባቸው የነበረውን የ12 ዓመት እስርን ጀመሩ።

የ69 ዓመቱ ግለሰብ 'ማሌዢያ ዲቨሎፕመንት በርሃድ' ከተሰኘ መንግሥታዊ ተቋም ጋር በተያያዘ በቀረቡባቸው የሙስና ወንጀሎች ጥፋተኛ ከተባሉ በኋላ Y12 ዓመታት በእስር ተበይኖባቸው ነበር።

ናጂብ ራዛክ ከሁለት ዓመታት በፊት ጥፋተኛ ይባሉ እንጂ ላቀረቡት አቤቱታ ፍርድ እስኪሰጣቸው ድረስ በዋስ ከእስር ውጪ ሆነው ቆይተዋል።

ራዛክ ምንም ጥፋት አላጠፋሁም ይበሉ እንጂ፤ ፍርድ ቤት ከመንግሥታዊው ተቋም ወደ ግል ሂሳባቸው 9.4 ሚሊዮን ዶላር መዘዋወሩን ካረጋገጠ በኋላ እአአ 2020 ላይ በሰባት ወንጀሎች ጥፋተኛ ተብለዋል።

ይህን ተከትሎም 12 ዓመታትን በእስር እንዲያሳልፉ እና 48.8 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲከፍሉ ተፈርዶባቸዋል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የሕግ ቡድን ግን ናጂብ በግል ሂሳባቸው የነበረው ገንዘብ በሳዑዲ አረቢያ ንጉሣውያን ቤተሰብ የተሰጠ እንጂ ከመንግሥታዊው ተቋም የተላለፈ እንደሆነ እንዲያውቁ አልተደረገም ብለው ይከራከራሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የሕግ ባለሙያዎቹ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር በአሜሪካ እና በማሌዢያ የሚፈለገው የፋይናንስ ባለሙያ ጆህ ሎው አማካይነት የተሳሳተ ውሳኔን እንዲወስዱ ተደርገዋል ይላሉ።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጉዳይን ከመረመሩት ዳኞች መካከል አምስቱ በግለሰቡ ላይ የተላለፈው ብይን አግባብ መሆኑን እና በፍርደኛው የቀረበው አቤቱታ መሠረት የሌላው ነው ስለማለታቸው ተገልጿል።

በሌላ በኩል የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ባለቤትም ከታክስ ስወራ እና ከገንዘብ ዝውውር ጋር የተያያዙ ክሶች ቀርቦባቸዋል።

ሮስማህ መንሶር ከፀሐይ ብርሃን ኃይል ፕሮጀክት ጋር በተያያዘ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ከማቅረብ እና ከታክስ ስወራ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ክስ ተመስርቶባቸዋል።

የአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ባለቤት ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ከአንድ ሳምንት በኋላ ቀጠሮ ይዟል።

ናጂብ ራዛክ ከእአአ 2009 እስከ 2018 ድረስ የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩ ሲሆን፤ ወላጅ አባታቸውም ከእአአ 1970-1976 ድረስ አገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው አስተዳድረዋል።