በደብረ ብርሃን የተፈናቃዮች መጠለያ ያሉ ከ100 በላይ ሰዎች ለድንገተኛ ሕመም ተዳረጉ

ደብረ ብርሃን ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Mayor Office Of Debre Birhan City

የምስሉ መግለጫ, ደብረ ብርሃን ከተማ

በደብረ ብርሃን ከተማ፣ ወይንሸት ካምፕ ተብሎ በሚጠራው የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ዕሁድ ነሐሴ 15/2014 ዓ. ም. ከ100 በላይ ሰዎች ለድንገተኛ ሕመም መዳረጋቸው ተገለጸ።

ሰዎቹ ለድንገተኛ ሕመም የተዳረጉበትን ምክንያት ለማወቅ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በተለያየ ጊዜያት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በታጣቂዎች የተፈፀሙ ጥቃቶችን ተከትሎ ተፈናቅለው በመጠለያ ጣቢያው ተጠልለው የሚገኙት ዜጎች ለሕመም የተዳረጉት፣ በጎ ፈቃደኞች ምገባ ካደረጉ በኋላ መሆኑን የከተማው ኮምዩኒኬሽን ኃላፊመቅደስ ብዙነህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በጎ ፈቃደኞች ለተፈናቃዮች የወሰዱትን ምግብ ተመግበው ከታመሙት 117 ሰዎች መካከል 116ቱ ሕክምና ተደርጎላቸው ወደ መጠለያው እንደተመለሱና አንዲት ሴት ግን ሕክምና ላይ እንደሆነች አክለዋል።

በወቅቱ ለሕመም የተዳረጉት 117 ተፈናቃዮች ወደ ደብረ ብርሃን ሆስፒታል እና በከተማዋ ወደሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ተወስደው ሕክምና እንደተደረጋላቸውም ኃላፊዋ ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አስማረ ሳሙዔል፣ ወደ ሆስፒታላቸው አንድ ሕጻንን ጨምሮ 12 ሰዎች ገብተው እንደነበር ጠቅሰው፣ በወቅቱ ይታይባቸው የነበሩትን የሕመም ምልክቶች የጨጓራ ማቃጠል፣ ማስመለስን እና ማስቀመጥ እንደነበረ አብራርተዋል።

ታማሚዎቹ ያሳዩ የነበሩት ምልክቶች የምግብ መመረዝ እና ባክቴርያን ጨምሮ መንስኤያቸው የተለያየ ሊሆን እንደሚችል የገለጹት አቶ አስማረ፣ ለሕመም የዳረጋቸውዋነኛ ምክንያት ገና እንዳልታወቀ አክለዋል።

የኮምዩኒኬሽን ኃላፊዋ መቅደስም ጉዳዩ በፀጥታ ኃይል እንደተያዘ እና ትክክለኛ መንስኤውን ለማወቅ ከምግቡ የተወሰደ ናሙና ላይ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

“ነገሩን የፀጥታ ኃይሉ ይዞታል። የምርመራው ውጤትም ከ24 ሰዓት በኋላ ስለሚታወቅ ምክንያቱ ይገለጻል” ብለዋል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙ ሰዎች መኖራቸውንም ኃላፊዋ አክለዋል። ሰዎቹ ለድንገተኛ ሕመም የተዳረጉበትን ምክንያት ለማወቅም ምርመራ እየተካሄደ መሆኑ ተገለጿል።

በበጎ ፈቃደኞች ከሚቀርቡ ምግቦች እና መጠጦች ደኅንነት ጋር በተያያዘ፣ ከዚህ ክስተት በኋላ ትምህርት መውሰዳቸውን የሰሜን ሸዋ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አበባው መሰለ አስረድተዋል።

በቀጣይ ከመጠለያው ውጪ የሚገቡ ምግቦችን በተመለከተ በጥንቃቄ መታየት እንዳለባቸው እና ወደ መጠለያው ከመግባታቸው በፊት ምን ቅድመ ሁኔታ መከተል እንዳለባቸውም እንደሚታይ አክለዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን 77 ሺህ ተፈናቃዮች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ከ20 ሺህ በላይ የሚሆኑት በደብረ ብርሃን በሚገኙ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ እና ድንገተኛ ሕመም በተከሰተበት መጠለያ ውስጥ 6 ሺህ የሚሆኑ ተፈናቃዮች እንደተጠለሉ አቶ አበበ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም ይደረግ የነበረው ድጋፍ ሕይወት የማዳን እንደነበረና ከዚያ በዘለለ ተከታታይነት ያለውና ሁሉንም አስፈላጊ ነገሮች ያሟላ እርዳታ መስጠት እንደሚያሻም ጠቅሰዋል።

“መንግሥት ተከታታይነት ባለው መልኩ ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም፣ ሙሉ በሙሉ አስፈላጊ ነገሮችን (ዘይት እና ዱቄትን ጨምሮ) ማሟላት ላይ ክፍትተ አለ” ሲሉ አክለዋል።

ከምግብ ድጋፍ ባሻገር በመጠለያው ያሉ ሰዎች የሥነ ልቦና ማገገሚያ ድጋፍ እንዲያገኙ እና ሕጻናትም ትምህርት እንዲያገኙ በማስቻል ረገድ የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉም አያይዘው አንስተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በምዕራብ ኢትዮጵያ ታጣቂዎች በተለያዩ ጊዜያት በሰለማዊ ሰዎች ላይ በፈጸሟቸው ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው የሚታወስ ነው።

ከእነዚህ ጥቃቶች የሸሹ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን በመልቀቅ ተፈናቅለው ወደተለያዩ አካባቢዎች የሄዱ ሲሆን፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና ከተማ የሆነችው ደብረ ብርሃን ደግሞ በርካታ ተፈናቃዮችን እያስተናገደች ትገኛለች።