በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው ድርቅ ‘ከሚታሰበው በላይ ነው’ - ዩናይትድ ኪንግደም

በድርቅ የሞተ እንስሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአፍሪካ ቀንድ በአስርት ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ ሚሊዮኖች እየተሰቃዩ ነው ሲሉ የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) የአፍሪካ ጉዳዮ ሚኒስትር ተናገሩ። 

ሚኒስትሯ ቪኪ ፎርድ በአፍሪካ ቀንድ አገራት ውስጥ ያጋጠመው የድርቅ ችግር “ከሚታሰበው በላይ ነው” ብለዋል። 

በዚህም ሳቢያ ከሰባት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከፍተኛ የሰብዓዊ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።

ይህ ድርቅ በየአገራቱ ያሉ ሰዎች ምግብ እና ውሃ ለማግኘት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች እንዲጓዙ በማስገደድ የበርካቶችን መፈናቀል አስከትሏል።

አራት ተከታታይ ዝናብ አልባ ወቅቶች፣ ግጭቶች፣ የምግብ ዋጋ ንረት እና የኮቪድ-19 ተጽዕኖ የተከሰተውን ሰብአዊ ቀውስ እያባባሱት ነው ተብሏል።

ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰው ሕይወት መጥፋትን ለመከላከል አጋሮች እና ዓለም አቀፍ ለጋሾች አፋጣኝ እርምጃ እንዲወስዱ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።

በሶማሊያ ብቻ ከ380,000 በላይ ህጻናት ለከፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በመጋለጣቸው ከፈረንጆቹ ዓመት መጠናቀቅ በፊት ሕይወታቸው ሊያልፍ ይችላል ተብሎ እንደሚሰጋ ቪኪ ፎርድ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት በዚህ ዓመት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለሰብዓዊ እርዳታ 150 ሚሊዮን ዶላር (178 ሚሊዮን ዶላር) ወጪ ለማድረግ ወስኗል። እስካሁንም 76 ሚሊዮን ፓውንድ ያህሉን ወጪ አድርጓል።

በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ ቀንድን በመታው ድርቅ ሶማሊያ ክፉኛ የተጎዳች አገር ብትሆንም በደቡብ ኢትዮጵያ እና በሰሜን ኬንያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በድርቁ ምክንያት እየተሰቃዩ ነው።

በሶማሊያ ውስጥ ካለው ሕዝብ ግማሹ ያህሉ ለረሃብ የተጋለጠ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ በተለይ ህጻናት ለከፋ የምግብ እጥረት መዳረጋቸውን ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ገልጸዋል።

በዚህም ሳቢያ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከሶማሊያ ገጠራማ አካባቢዎች ቀያቸውንና ቤታቸውን ጥለው ወደ ተፈናቃዮች መጠለያ ማዕከላት እያመሩ ነው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም እንደሚለው በኬንያ፣ በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ በዚህ የአውሮፓውያን ዓመት መጨረሻ ለረሃብ የሚጋለጡ ሰዎች ቁጥር እስከ 20 ሚሊዮን የሚደርስ መሆኑን አስታውቋል።