ባይደን ከዢ ጋር ሲገናኙ የሚነጋገሩበት ዋና ጉዳይ ጦርነት ማስቀረት ነው አሉ

ዢ ዢንፒንግ እና ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ዢ ዢንፒንግ እና ጆ ባይደን

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከቻይናው አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር በቡድን-20 አገራት ስብሰባ ላይ ሲገናኙ ዋናው ጉዳይ ከቻይና ጋር ጦርነት ማስቀረት ነው አሉ።

ባይደን ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ ከዢ ጋር ፊት ለፊት ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው።

የዓለማችን ቀዳሚ ኃያላን አገራት መሪዎች ፊት ለፊት ሲገናኙ ፖለቲካ፣ ምጣኔ ሃብት እና የደኅንነት ጉዳዮች አጀንዳ እንደሚሆኑ ተመላክቷል።

ፕሬዝዳንት ባይደን ከዢ ጋር ሲገናኙ በመክፈቻ ንግግራቸው ከቻይና ጋር “ግጭት” ውስጥ ላለመግባት ጥረት ማድረጉ ቁልፍ ጉዳይ ነው ማለታቸው ተገልጿል።

ባይደን ዓለም ሁለቱ አገራት በጋራ እንዲሰሩ ይጠበቃል ያሉ ሲሆን፤ አገራቸው አሜሪካ ከቻይና ጋር የአየር ንብረት ለውጥ እና ደኅንነትን ጨምሮ በአንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ለመስራት ዝግጁ ናት ብለዋል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ቤይጂንግ ለአሜሪካ-ቻይና ግንኙነት ትኩረት እንደምትሰጥ ገልጸው፤ ሁለቱ ኃያላን አገራት በትክክለኛው አቅጣጫ ላይ መሆን አለባቸው ብለዋል።

“የሁለትዮሽ ግንኙነታችን ወደፊት እንዲሄድ እና ግንኙነትን ለማሳደርግ ትክክለኛውን አቅጣጫ መፈለግ አለብን” ብለዋል ዢ ጂንግፒንግ።

የታይዋን ጉዳይ፣ የሰሜን ኮሪያ ተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራ እና በዩክሬን ያለው ጦርነት አሜሪካ እና ቻይና በዐይነ ቁራኛ እንዲተያዩ ያደረጉ ጉዳዮች ሲሆን፤ ሁለቱ አገራት የንግድ ጦርነት ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል።

አሜሪካ የቻይና የንግድ ሥርዓትን አጥብቃ የምትተች ሲሆን፤ ቻይና በበኩሏ የቴክኖሎጂ ውጤቶቼ ላይ ገደብ ትጥላለች ስትል አሜሪካንን ትወቅሳለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ጃኔት ዬለን በሁለቱ ፕሬዝዳንቶች መካከል የሚደረግ መልካም ውይይት ለአሜሪካ ንግድ ሥራዎች መረጋጋትን ያመጣል ብለዋል።

የቻይና የዜሮ-ኮቪድ ፖሊሲ ድንበሮችን ዘግቶ እንቅስቃሴ መገደለቡ መጣኔ ሃብት መጉዳቱን ተናግረዋል።

የቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ከአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር እንደሚነጋገሩም ተገልጿል።

ግንኙነታቸው የሻከረው አውስትራሊያ እና ቻይና መሪዎቻቸው ለመጨረሻ ጊዜ ፊት ለፊት የተገናኙት እአአ በ2016 ላይ ነበር።

አውስትራሊያ ቤይጂንግን በጣልቃ ገብነት መክሰሷ እና የኮሮናቫይረስ ምንጭ እንዲመረመር በይፋ መጠየቋ ቻይናን አስቆጥቶ ነበር። ቻይና በበኩሏ ከአውስትራሊያ በሚገቡ ምርቶች ላይ ከፍ ያለ ግብር ጥላ ነበር።