በዩናይትድ 'ተካድኩኝ'፤ 'ቴን ሃግን አላከብርም' . . . አነጋጋሪው የሮናልዶ ቃለ ምልልስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ክርስቲያኖ ሮናልዶ በማንቸስተር ዩናይትድ “እንደተከድኩኝ” ይሰማኛል አለ።
ሮናልዶ ክለቡ በግዳጅ ሊያስወጣው እንደሚፈልግ እንደሚሰማውም ጨምሮ ተናግሯል።
ሮናልዶ እንዳሰበው ከዩናይትድ በመውጣት በቻምፒየንስ ሊግ ወደሚወዳደር ክለብ ባለመዘዋወሩ ስለኦልድትራፎርድ ህይወቱ የራሱን ሃሳብ እንደሚሰጥ በነሐሴ ወር ቃል ገብቶ ነበር።
ኮከቡ ፖርቹጋላዊ ከስመ ጥሩ ጋዜጠኛ ፒርስ ሞርጋን ጋር ለቶክ ቲቪ ሰፊ ቃለ ምልልስ በማድረግ ዝምታውን ሰብሯል።
ሮናልዶ ስላነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ ማንቸስተር ዩናይትድም ተጠይቋል።
በዘንድሮው ዓመት አሰልጣኝ ቴን ሃግን የሾመው ማንቸስተር ዩናይትድ ትላንት ፉልሃምን ማሸነፉን ተከትሎ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የዩናይትዶች እሱን ከክለቡ ለማስወጣት እየሞከሩ እንደሆነ ለቀረበለት ጥያቄ ሮናልዶ ምላሽ ሲሰጥ “አዎ አሰልጣኝ (ኤሪክ ቴን ሃግ) ብቻ ሳይሆን በክለቡ ዙሪያ ያሉ ሌሎች ሁለት ወይም ሦስት ሰዎች እንደከዱኝ ተሰምቶኛል” ብሏል።
የ37 ዓመቱ ኮከብ የክለቡ ከፍተኛ አመራሮችም እሱን ለማባረር እየሞከሩ እንደሆነ አጥብቆ ሲጠየቅ “እኔ ግድ የለኝም። ሰዎች እውነታውን መስማት አለባቸው” ሲል መልሷል።
"አዎ እንደተከዳሁ ተሰምቶኝ ነበር። በዚህ ዓመት ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዓመትም አንዳንድ ሰዎች እዚህ እንድቆይ እንደማይፈልጉኝ ተሰምቶኛል።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ለቴን ሃግ 'አክብሮት' የለኝም
ሮናልዶ ማንቸስትር በሊጉ በአስቶንቪላ 3-1 ከተሸነፈበት ጨዋታ በኋላ ምንነቱ ባልተገለጸ ህመም ምክንያት አልተጫወተም።
ባለፈው ወር ከቶተንሃም ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይሮ ለመግባት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከቼልሲ ጋር ከተደረገው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ውጭ እንዲሆን በቴን ሃግ ተወስኖበታል።
"ለእሱ ክብር የለኝም ምክንያቱም እሱም ለእኔ አክብሮት ስላላሳየኝ ነው። ለኔ ክብር ከሌለህ ላንተም ክብር ፈጽሞ አልሰጥህም" ሲል ሮናልዶ ለሞርጋን ተናግሯል።
ሙሉ ቃለ ምልልሱ ረቡዕ እና ሐሙስ ምሽቶች ለህዝብ ይደርሳል።
ሮናልዶ በመጋቢት ወር የልጁን ህልፈት ተከትሎ ከቀናት በኋላ በአንፊልድ በተደረገ ጨዋታ የሊቨርፑል ደጋፊዎች በሰጡት ክብር ምን ያህል እንደተነካ ለሞርጋን ገልጾለታል።
ሙሉ ቃለ ምልልሱ 90 ደቂቃ ቢረዝምም ሞርጋን ለዘ ሰን ጋዜጣ እንደጻፈው ሮናልዶ እአአ በ2021 ወደ ክለቡ ከተመለሰ በኋላ ዩናይትድን ያገኘበትን ደረጃም ይፋ አድርጓል።
"ደጋፊዎቹ እውነቱን ማወቅ አለባቸው ብዬ አስባለሁ። ለክለቡ ጥሩ ነገር እመኛለሁ። ወደ ማንቸስተር ዩናይትድ የመጣሁትም ለዚህ ነው” ብሏል።
"ሰር አሌክስ ፈርጉሰን [የቀድሞው አሰልጣኝ] ከለቀቁ በኋላ በክለቡ ምንም ዓይነት ለውጥ አላየሁም። ምንም የተለወጠ ነገር የለም።“
"ማንቸስተር ዩናይትድን እወዳለሁ፣ ደጋፊዎቹን እወዳቸዋለሁ፣ ሁሌም ከጎኔ ናቸው። የተለየ ለማድረግ ከፈለጉ… ብዙ ብዙ ነገሮችን መለወጥ አለባቸው" ብሏል።
ሮናልዶ ስለክለቡ ያለውን አመለካከት ፈርጉሰን እንደሚጋሩት ተናግሯል። ፈርጉሰን ሮናልዶ ጁቬንቱስን ለቆ ማንቸስተር ሲቲን ሊቀላቀል ከጫፍ በደረሰበት ወቅት ወደ ኦልድትራፎርድ እንዲመለስ ትልቅ ሚና ተጫውተዋል።
ሮናልዶ አክሎም “ክለቡ ሊሄድበት በሚገባው መንገድ ላይ እንዳልሆነ ከማንም በላይ ያውቀዋል ብሏል።
"እሱ ያውቃል። ሁሉም ያውቀዋል። ያንን የማያዩ ሰዎች... ማየት ስለማይፈልጉ ነው፤ ማየት የተሳናቸውም ናቸው" ብሏል።
ስለ ራይኒክ 'አልሰማም' ነበር
ሮናልዶ ወደ ክለቡ ሲመለስ የቀድሞ የቡድን አጋሩ ኦሌ ጉናር ሶልሻየር አሰልጣኝ ነበር። በኋላም ሶልሻየር በራልፍ ራይኒክ ተተካ። የአሁኑ አሰልጣኝ ቴን ሃግ ጀርመናዊውን በመተካት ኃላፊነቱን ወስደዋል።
“አሰልጣኝ ካልሆንክ እንዴት የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ትሆናለህ? ስለ እሱ ሰምቼ እንኳ አላውቅም" ብሏል ሮናልዶ ስለራይኒክ ሲናገር።
ከዘንድሮው የውድድር ዘመን ባህሪው ጋር በተያያዘ ዋይኒ ሩኒ የቀድሞ የዩናይትድ የቡድን አጋሩን ሮናልዶን ወቅሶታል። ፖርቹጋላዊው ኮከብም የቀድሞ እንግሊዛዊውን አጥቂ መልስ ምት ሰጥቷል።
"ለምን ክፉኛ እንደሚወቅሰኝ አላውቅም...ምናልባት ጫማውን በመስቀሉ እና እኔ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ እየተጫወትኩ ስለሆነ ነው" ሲል ሮናልዶ ተናግሯል።
"ከሱ የተሻልኩ ነኝ አልልም። ምክንያቱም እውነት ነው..."












