ለሳምንታት ሲዋጉ የነበሩት ታይላንድ እና ካምቦዲያ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደረሱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ታይላንድ እና ካምቦዲያ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ላይ ላይ ለመድረስ መስማማታቸውን የሁለቱ አገራት የመከላከያ ሚኒስትሮች ዛሬ ቅዳሜ ባወጡት የጋራ መግለጫ አስታወቁ።
ሁለቱም ወገኖች ሁሉንም የወታደሮች እንቅስቃሴ ለመግታት እና በድንበር አካባቢዎች የሚኖሩ ሰላማዊ ሰዎች ወደቤታቸው እንዲመለሱ ለመፍቀድ ተስማምተዋል። ይህ ስምምነት ቢያንስ 41 ሰዎች እንዲገደሉ እና አንድ ሚሊዮን ገደማ ሰዎች እንዲፈናቀሉ ምክንያት የሆነውን ለሳምንታት የዘለቀ ከፍተኛ የድንበር ውጊያ የሚያስቆም ነው።
የተኩስ አቁሙ ከዛሬ ጠዋት ሁለት ሰዓት ጀምሮ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ ተገልጿል። የተኩስ አቁሙ ተግባራዊ ከሆነ ከ72 ሰዓታት በኋላ በታይላይ የተያዙ 18 የካምቦዲያ ወታደሮች እንደሚለቀቁ መግለጫው ያስረዳል።
እዚህ ስምምነት ላይ የተደረሰውን የታይላንድ እና ካምቦዲያ ባለሥልጣናት ጦርነቱን ለማስቆም ለበርካታ ቀናት ንግግር ካደረጉ በኋላ ነው።
የጋራ መግለጫው "ግጭትን ለማርገብ" እንደሚወሰዱ ከዘረዘራቸው እርምጃዎች መካከል፤ በሰላማዊ ሰዎች፣ በሲቪል ተቋማት እና መሠረተ ልማቶች እንዲሁም በሁለቱም ወገን ባሉ ወታደራዊ ኢላማዎች ላይ የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ማቆም" የሚሉት ተካትተዋል።
መግለጫው፤ "ሁለቱም ወገኖች ያለ ትንኮሳ ተኩስ ከመክፈት ወይም ወደ ሌላኛው ወገን ይዞታዎች ወይም ወታደሮች ከመጠጋት እና ወታደራዊ እንቅስቃሴ ከማድረግን መቆጠብ አለባቸው" ሲል አስፍሯል።
መግለጫው እንደሚያስረዳው በታይላንድ የተያዙት 18 የካምቦዲያ ወታደሮች የሚለቀቁት "በኩዋላ ላምፑር ስምምነት መንፈስ" ነው። ሁለቱ አገራት ጥቅምት ላይ ይህንን ስምምነት የፈጸሙት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተገኙት ሥነ ሥርዓት ላይ ነበር።
በታኅሣሥ መጀመሪያ ግን እንደ አዲስ ግጭት ማገርሸቱን ተከትሎ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ፈርሷል። ስምምነቱ ለመፍረሱ አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ ያደርጋሉ።
የታይላንድ ጦር፤ ወታደሮቹ በታይላንድ ኡቦን ራትቻታኒ ግዛት ውስጥ ከካምቦዲያ ለተከፈተባቸው ተኩስ ምላሽ እንደሰጡ እና አንድ የታይላንድ ወታደር መገደሉን ይገልጻል።
በፕሪያ ቪሂር ግዛት ጥቃቱን የጀመሩት የታይላንድ ኃይሎች እንደሆኑ የሚገልጸው የካምቦዲያ መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ካምቦዲያ የአጸፋ እርምጃ እንዳልወሰደች በአጽንኦት አንስቷል።

የፎቶው ባለመብት, AP
ግጭቱ በታኅሣሥም በሙሉ የቀጠለ ሲሆን አርብ ዕለት ታይላንድ አወዛጋቢ በሆነው የካምቦዲያ ድንበር ግዛት የአየር ጥቃት ፈጽማለች።
የታይላንድ አየር ኃይል፤ ሰላማዊ ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው ከወጡ በኋላ "በምሽግነት ሲያገለግል የነበረን የካምቦዲያ ወታደራዊ ይዞታ" መምታቱን አስታውቋል።
የካምቦዲያ መከላከያ ሚኒስቴር ግን ጥቃቶቹ በሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ላይ የተፈጸሙ "የጅምላ ጥቃቶች" እንደሆኑ በመግለጽ ወንጅሏል።
በታይላንድ እና በካምቦዲያ መካከል ያለው የድንበር ውዝግብ ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ ያስቆጠረ ነው። በቅርቡ ግጭቱ እንደገና የተነሳው ግንቦት ላይ በተነሳ ግጨት አንድ የካምቦዲያ ወታደር መገደሉን ተከትሎ ነው።
ከሁለት ወራት በኋላ ሐምሌ ላይ በድንበሩ አካባቢ በተደረገው ለአምስት ቀናት የዘለቀ ከባድ ውጊያ በርካታ ወታደሮች እና ሰላማዊ ሰዎች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ሰላማዊ ሰዎችም ተፈናቅለዋል።
በማሌዥያ እና በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በጉዳዩ ጣልቃ መግባታቸውን ተከትሎ ሁለቱ ሀገራት ጠንካራ ያልሆነ የሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት የደረሱ ሲሆን በጥቅምት ወር መጨረሻም ፊርማቸውን አኑረዋል።
ትራምፕ ስምምነቱን "የኩዋላ ላምፑር የሰላም ስምምነት" ሲሉ ሰይመውታል። ስምምነቱ ሁለቱም ወገኖች ከባድ መሳሪያዎቻቸውን አወዛጋቢ ከሆነው ግዛት እንዲያስወጡ እና ይህንን የሚከታተል ጊዜያዊ ታዛቢ ቡድን እንዲያቋቁሙ ያዝዛል።
ይሁን እንጂ የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር አኑቲን ቻርንቪራኩል የጸጥታ ስጋቱ "በትክክል አልቀነሰም" ማለታቸውን ተከትሎ፤ ህዳር ላይ ታይላንድ ለስምምነቱ ተገዢ መሆኗል አቁማለች።















