የታይላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሾልኮ በወጣ የስልክ ንግግር ምክንያት ታገዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የታይላንድ ህገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ከቀድሞ የካምቦዲያ መሪ ሃን ሴን ጋር ያደረጉት የስልክ ንግግር ሾልኮ መውጣቱን ተከትሎ ስልጣን እንዲለቁ ጫና የበዛባቸውን የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ፓኤቶንግታርን ሺናዋትራን አገደ።
በዚህ የስልክ ንግግር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሯ "አጎቴ" ሲሉ ለጠሩት የቀድሞ የካምቦዲያ መሪ ጋር የአገራቸውን የጦር አዛዥ ሲተቹ ይሰማል።
ይህም በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን ከኃላፊነታቸውም እንዲወርዱ ፊርማዎች ተሰባስበዋል።
በታይላንድ ለሁለት አስርት ዓመታት ፖለቲካውን በበላይነት የተቆጣጠሩት ሺናዋትራ ጎሳ አባል የሆኑት ፓኤቶንግታር፣ የስልጣን ዘመናቸው ሳይጠናቀቅ ከኃላፊነት እንዲነሱ የተደረጉ ሶስተኛዋ ፖለቲከኛ ይሆናሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ የሚመሩት ጥምር መንግሥት ቁልፍ የወግ አጥባቂ ፓርቲ ከሁለት ሳምንት መውጣቱን ተከትሎ በጥቂት አብላጫ ለመምራት እየተንገታገተ ይገኛል።
የአገሪቱ ህገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ጠቅላይ ሚኒስትሯ ከስልጣን እንዲነሱ 7 ለ2 ድምጽ የሰጠ ሲሆን እሳቸውም መከላከያቸውን ለማምጣት 15 ቀናት ይኖራቸዋል።
በዚህም ወቅት የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሱሪያ ጁንግሩንግሩዋንግኪት ተጠባባቂ መሪ ሆነው የሚያገለግሉ ይሆናል።
ፓኤቶንግታር ከስልጣን የሚነሱ ከሆነ ከነሐሴ ወዲህ ከፌው ታይ ፓርቲ የተወገዱ ሁለተኛዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ።
ከሳቸው በፊት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ስሬታ ታቪሲን በእስር ላይ የነበሩትን የቀድሞ ጠበቃ በካቢኔያቸው በመሾማቸው ከስልጣን እንዲነሱ ተደርገዋል።
ከዚህ ቀደም ከስልጣን እንዲወገዱ የተደረጉት ታክሲን ሺናዋትራ ልጅ የሆኑት ፓኤቶንግታር ከቀናት በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ መሐላ አደረጉ።
የ38 ዓመቷ ጠቅላይ ሚኒስትር በአገሪቷ ታሪክ ስልጣን የተቆናጠጡ በዕድሜ ትንሽዋ እንዲሁም ከአክስቷ ይንግሉክ ሺናዋትራ በኋላ ሁለተኛዋ ሴት ናቸው።
የአገሪቱን የደከመ ምጣኔ ኃብት ለማነቃቃት እየታገሉ ያሉት መሪዋ ተቀባይነታቸው እየወረደ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ሾልኮ የወጣው የስልክ ንግግራቸውን በተመለከተ ይቅርታ ቢጠይቁም ሰሞኑን በድንበር ድርድር ምክንያት የተነሱ ውዝግቦች ጋር በተያያዘ "የድርድር ቴክኒክ" ነው ሲሉ ተከላክለዋል።
ነገር ግን የወግ አጥባቂ የፓርላማ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትሯ ለካምቦዲያ ተንበርክከዋል እንዲሁም የአገሯን ጦር ዝቅ በማድረግ ከሰዋቸዋል።
የአገሪቱን መንግሥት ከጀርባ ሆነው ያሽከረክሩታል የሚባሉት አባቷ በፖለቲካው ውስጥ የገቡትን እሰጣገባ ጋር እየታገሉ ባሉበት ወቅት ነው የፍርድ ቤቱ ውሳኔ የተላለፈው።
አባትየው ከዘጠኝ ዓመታት በፊት ለደቡብ ኮሪያ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የታይላንድን ንጉሳዊ ስርዓት ተሳድበዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
የፍርድ ሂደቱም ማክሰኞ ዕለት ተጀምሯል።
ከ15 ዓመታት ግዞት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2023 ወደ ታይላንድ የተመለሱት አወዛጋቢው የፖለቲካ መሪ በአገሪቱ አፋኝ በሚባለው 'ሌሴ ማጀስቲ' ህግ ክስ ከተመሰረተባቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል ዋነኛው ናቸው።












