እንደ አዲስ ባገረሸ የድንበር ግጭት ታይላንድ ካምቦዲያ ላይ የአየር ጥቃት ፈጸመች

የድንበር ጠባቂ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

እንደ አዲስ በተቀሰቀሰ የድንበር ግጭት ሳቢያ ታይላንድ ካምቦዲያ ላይ የአየር ጥቃት መፈጸሟን አስታወቀች።

የታይላንድ ጦር በካምቦዲያ ጥቃት ሁለት ወታደሮቹ እንደተገደሉት እና አራት ወታደሮቹ ደግሞ እንደቆሰሉ ይፋ አድርጓል።

"የካምቦዲያን ጥቃት ለመመከት የተለያዩ ወታደራዊ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት ተሰንዝሯል" ሲል ጦሩ ገልጿል።

የካምቦዲያ ጦር በበኩሉ ጥቃቱን የከፈተችው ታይላንድ እንደሆነች እና የአፀፋ ምላሽ እንዳልሰጠ አስታውቋል።

በማሌዥያ እና በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጥረት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰው የነበሩት ሁለቱ አገራት ወደ አዲስ ግጭት አምርተዋል። አንዳቸው ሌላቸውን የተኩስ አቁሙን በመጣስ እየከሰሱም ነው።

ያለፈው ሐምሌ ላይ በተነሳ እና ለአምስት ቀናት በዘለቀ የድንበር ግጭት ምክንያት ቢያንስ 48 ሰዎች ሲገደሉ 300,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል።

ታይላንድ እንዳለችው ትናንት በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል ሲ ሳ ኪት ለ35 ደቂቃ የቆየ ግጭት ተካሂዷል። ወታደሮቿ ከሲ ሳ ኪት፣ ከቡሪ ራም፣ ከሱሪን እና ከኡብሮን ራቻሀቲኒ ግዛቶች እንዲወጡም አዝዛለች።

ዛሬ በድንበር ላይ የሚገኙ የታይላንድ እና የካምቦዲያ ወታደሮች ተኩስ ከፍተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ ከወራት በፊት በሁለቱ አገራት ላይ ታሪፍ ለመጣል መዛታቸውን ተከትሎ የተኩስ አቁም ስምምነት ተፈርሟል።

በጥቅምት ወር ትራምፕ በማሌዥያ የተካሄደውን የእስያ ጉባዔ ሲታደሙ የተኩስ አቁም ተፈርሟል። ትራምፕም "ለደቡብ እስያ ታላቅ ቀን ነው" ብለዋል።

ስምምነቱ በተፈረመ በሁለት ቀናት ውስጥ በካምቦዲያ ድንበር አቅራቢያ በፈነዳ ቦምብ ሁለት የታይላንድ ወታደሮች መጎዳታቸውን ተከትሎ ታይላንድ ስምምነቱን እንደማትተገብር አስታውቃለች።

ትራምፕ ለኖቤል የሰላም ሽልማት ያጨችው ካምቦዲያ ግን የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን በተደጋጋሚ ገልጻለች።

የድንበር ግጭቱ ትናንት እንደ አዲስ ከተቀሰቀሰ በኋላ በካምቦዲያ ድንበር የሚኖሩ ወላጆች ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ሲያስወጡ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች በማኅበራዊ ሚዲያ ተጋርተዋል።

በካምቦዲያ ትምህርት ቤቶች የተፈጠረውን ድንጋጤ ከቦታው ሆኖ የዘገበው ታዋቂ ጋዜጠኛ ሜች ዳራ "ድንበር ላይ ፍንዳታ ከተሰማ በኋላ ወላጆች ልጆቻቸውን ለመውሰድ እየተጣደፉ መጥተዋል። እነዚህ ልጆች በዚህ ቀውስ ስንት ጊዜ ነው ደጋግመው የሚረበሹት?" ብሏል።

ካምቦዲያ የጦር መሣሪያ ለማዘዋወር የዘረጋችው የሽቦ ገመድ ላይ የሚጓዝ ተሽከርካሪን ማውደሙን የታይላንድ ጦር ገልጿል።

"ጦሩ ሕዝቡን እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት በሙሉ አቅሙ ይጠብቃል" ሲልም ለአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሰጥቷል።

ታይላንድ በድንበር ግዛቷ መንገድ የሚሠሩ መሀንዲሶችን እንዲጠብቁ ያሰማራቻቸው ወታደሮች ላይ ካምቦዲያ ጥቃት መሰንዘሯን ገልጻለች።

ከ15 እስከ 20 ደቂቃ በቆየው የተኩስ ልውውጥ ሁለት ወታደሮች መገደላቸውም ተዘግቧል።

ካምቦዲያ ማንኛውንም ዓይነት ጥቃት እንዳልሰነዘረች እና ለግጭቱ ተጠያቂ ታይላንድ እንደሆነች ገልጻለች።

የታይላንድ ወታደሮች ወደ ካምቦዲያ ግዛት ጥይት እና ታንክ መተኮሳቸውን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።