ታይላንድ እና ካምቦዲያ ትራምፕን ስላሸማገሏቸው ቢያመሰግኑም ውጊያቸውን ግን ቀጥለዋል

የካምቦዲያ ወታደር ሮኬቶችን በጫነ ተሽከርካሪ ላይ ቆሞ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዶናልድ ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት የካምቦዲያ እና የታይላንድ መሪዎችን በመጥራት የድንበር ግጭትን ተከትሎ አፋጣኝ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ ግፊት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት በስኮትላንድ የጎልፍ መጫወጫ ሜዳ በነበራቸው የግል ጉብኝት መጀመሪያ ላይ ሁለቱም አገራት "ወዲያውኑ ተገናኝተው የተኩስ አቁም ለማድረግ እና በመጨረሻም ሰላም ለመፍጠር ተስማምተዋል" ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ላይ ጽፈዋል።

ሁለቱም አገራት ፕሬዝዳንቱን ለሃሳባቸው እና ላሳዩት ጥረት አመስግነዋል።

ካምቦዲያ የተኩስ አቁም ምክረ ሃሳቡን ስትቀበል፤ ታይላንድ ግን በሁለቱ አገራት መካከል ውይይት እንደሚያስፈልግ አሳስባለች።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት የስልክ ጥሪ ካደረጉ በኋላ ግን በድንበር ላይ ውጊያው ቀጥሏል።

የታይላንድ እና የካምቦዲያ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ለትራምፕ ስልክ ጥሪ የሰጡት ምላሽ አዎንታዊ ቢሆንም ሁለቱም አቋማቸውን አልቀየሩም።

ካምቦዲያ አስቀድሞ የተኩስ አቁም ሐሳብ አቅርባ ነበር፤ የጦር ሠራዊቷ ከታይላንድ የበለጠ ደካማ ሲሆን በታይላንድ የጦር መሳሪያዎች የቦምብ ድብደባ እና የአየር ድብደባ ግዛቷን እና መሳሪያ እያጣች ነው።

"ለ[ትራምፕ] ካምቦዲያ በቀረበው ሀሳብ እንደተስማማች ግልፅ አድርጌያለሁ" ሲሉ የካምቦዲያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁኑ ማኔት ከስልክ ጥሪ በኋላ ተናግረው፣ የትራምፕ ሽምግልና የብዙ ወታደሮችን እና ሰላማዊ ዜጎችን ሕይወት ለመጠበቅ ይረዳል ብለዋል።

በሌላ በኩል ታይላንድ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ፍቃደኛ መሆኗን ገልጻ፣ ነገር ግን ከካምቦዲያ ጋር ድርድር ቀዳሚ መሆን አለበት የሚለውን የቀድሞ ፍላጎቷን አጥብቃ እንደምትቀጥል ተናገራለች።

ተጠባባቂው ጠቅላይ ሚንስትር ፉምተም ዌቻያቻይ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስላሳሰቡት ነገር አመስግነው ታይላንድ በመርህ ደረጃ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መስማማቷን ገልፀዋል።

"ይሁን እንጂ ታይላንድ ከካምቦዲያ በኩል ቅን ሀሳብ ማየት ትፈልጋለች" ሲል የታይላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

እአአ በሐምሌ 24 ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ ቢያንስ 33 ወታደሮች እና ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የታይላንድ እና የካምቦዲያ ዜጎች ተፈናቅለዋል።

ሰላም የለም የንግድ ንግግሮችም የሉም

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ ምንም እንኳን "ውጊው እስከሚቆም" ድረስ ውይይቶችን ማካሄድ ተገቢ ባይሆንም ከካምቦዲያ እና ከታይላንድ ጋር የንግድ ንግግሮችን ለመቀጠል በጉጉት እንደሚጠባበቁ ገልፀዋል።

በካምቦዲያ እና ታይላንድ ላይ የአሜሪካ ታሪፍ ተግባራዊ ከመሆኑ ከአንድ ሳምንት በፊት ጣልቃ ገብተዋል ።

እአአ ከነሐሴ 1 ጀምሮ በአሜሪካ ከታይላንድ ወይም ከካምቦዲያ ሸቀጦችን የሚያያስገቡ የንግድ ተቋማት ከዚያ በፊት ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ 36 በመቶ ታሪፍ መክፈል አለባቸው።

ከአንድ ቀን በፊት የታይላንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሪስ ሳንጊያምፖንግሳ "ከሦስተኛ አገር እስካሁን ምንም ዓይነት ሽምግልና የሚያስፈልገን አይመስለኝም" ያሉ ሲሆን ትራምፕ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እንዴት እንደተሳተፉ ግልፅ አይደለም።

የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ከዚህ ቀደም በታይላንድ እና በካምቦዲያ መካከል የሚደረገውን ውይይት ለማመቻቸት ጥያቄ አቅርበው ነበር።

ቅዳሜ ቀደም ብሎ ካምቦዲያ ከታይላንድ ጋር "አፋጣኝ" የተኩስ አቁም እና አለመግባባቱን በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥያቄ አቅርባ ነበር።

ትራምፕ በደቡብ አይርሻየር በሚገኘው የቅንጦት ሪዞርታቸው ከተጓዙ በኋላ፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የካምቦዲያን ጠቅላይ ሚኒስትር ሁን ማኔትን እና ፉምተምን ማነጋገራቸውን ተናግረዋል።

"ሁሉም ነገር ሲጠናቀቅ፣ እና ሰላም በቀረበ ጊዜ፣ የንግድ ስምምነታችንን ከሁለቱም ጋር ለመጨረስ እጓጓለሁ!" ሲሉ ትራምፕ ጽፈዋል።

ታይላንድ እና ካምቦዲያ እያንዳንዳቸው በዚህ የቅርብ ጊዜ ግጭት የመጀመሪያውን ጥይት በመተኮስ እርስ በርስ ተካስሰዋል።

ታይላንድ ጦርነቱ የተጀመረው የካምቦዲያ ጦር በድንበር አካባቢ የታይላንድ ወታደሮችን ለመሰለል ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ባሰማራ ጊዜ እንደሆነ ተናግራለች።

ካምቦዲያ በበኩሏ የታይላንድ ወታደሮች ወደ ክመር-ሂንዱ ቤተመቅደስ በመውጣት የቀደመውን ስምምነት ጥሰዋል በማለት ከስሳለች።

የሁለቱ አገራት ውዝግብ ከመቶ ዓመት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን ፈረንሳይ ካምቦዲያን በወረረችበት ወቅት የሁለቱ አገራት ድንበር ማስመሯን ተከትሎ የመጣ ነው