የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ በታክስ ስወራ ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን አመነ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ ሐንተር ባይደን የቀረቡበትን ዘጠኝ የፌደራል ታክስ ስወራ ክሶች በሙሉ ጥፋተኛ ነኝ ሲል አመነ።
ሐንተር ጥፋተኝነቱን ያመነው የፌደራል አቃቤ ሕግ ክሱን በችሎት ለማየት እየተዘጋጀ በነበረበት ወቅት ነው ተብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ፣ ከዚህ በፊት ለአራት ተከታታይ ዓመታት (እአአ ከ2016-2019) ሆን ብሎ 1.4 ሚሊዮን ዶላር የገቢ ታክስ ባለመክፈል የቀረበበትን ክስ ክዶ ተከራክሮ ነበር።
የፕሬዝዳንቱ ልጅ ከሚያካሄዳቸው ትልልቅ የንግድ ስምምነቶች 1.4 ሚሊዮን ዶላር ታክስ በመሰወር በተከሰሰበት ወቅት 'ይህ የፖለቲካ ሴራ ነው ሲል' ነበር ያጣጣለው።
የፕሬዝዳንቱ ልጅ ለረዥም ጊዜ አደንዛዥ ዕጽ በመጠቀም ከፖለቲካ ተቀናቃኞች ትችት ሲቀርብበት ቆይቷል።
ከዚህ በኋላም ያልተፈቀደ የጦር መሳርያ በመያዝ እና አደንዛዥ ዕጽ መጠቀም ክስ ቀርቦበት ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ሊታሰር እንደሚችል ይጠበቃል።
ሐሙስ ዕለት በሎስ አንጀለስ በተካሄደ የፌደራል ችሎት የሐንተር ጠበቆች ቀርበው ደንበኛቸው በቀረቡበት ዘጠኝ ክሶች በአጠቃላይ ጥፋተኛ አይደለሁም ብሎ የነበረውን ቃሉን በመቀየር ወንጀል መስራቱን አምኗል ብለዋል።
ጠበቆቹ ከችሎቱ የተፋጠነ ፍትህ ለማግኘትም ጥያቄ ማቅረባቸው ተሰምቷል።
ችሎት ተገኝቶ የነበረው የፕሬዝዳንቱ ልጅ የቀረቡበት ዘጠኝ ክሶች ሲነበቡለት ለእያንዳንዱ “ጥፋተኛ ነኝ” ሲል ተሰምቷል።
ይህ የአቋም ለውጥ የተሰማው ጉዳዩን ለማየት ዳኞች ይሰየማሉ ተብሎ በተቀጠረበት ቀን ነው።
ከሦስት ወር በፊት የጦር መሳርያ በመያዝ እና አደንዛዥ ዕጽ መጠቀም ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ሐንተር ባይደን፣ ይህም በወንጀል የተፈረደበት በስልጣን ላይ ያለ ፕሬዝዳነት የመጀመርያ ልጅ አድርጎታል።
ማርክ ስካርሲ የተባሉ ጉዳዩን የሚያዩ ዳኛ ሐንተር ጥፋተኛነቱን በማመኑ እስከ 15 ዓመት በሚደርስ እስራት እና ከ 500 ሺህ እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ቅጣት ይጠብቀዋል ብለዋል።
የጥፋተኝነት ውሳኔው የሚሰማው የአሜሪካ ምርጫ ከተካሄደ አንድ ወር በኋላ፣ አባቱ ስልጣናቸውን በይፋ ለቅቀው ለቀጣዩ ፕሬዝዳንት ስልጣን ከማስረከባቸው አንድ ወር ቀደም ብሎ ታሕሳስ 7 2017 ዓ.ም. ነው።
ፕሬዝዳንት ባይደን ከዚህ በፊት ልጃቸውን ለመታደግ ያላቸውን ስልጣን እንደማይጠቀሙ አስታውቀው ነበር።
አንድ አቃቤ ሕግ ሐንተር ባይደን የቀረቡበትን ክሶች ባለ 56 ገጽ ጽሑፍ ካነበቡለት በኋላ ዳኛው በቀረቡበት ክሶች ላይ ሁሉ የቀረቡበትን ክሶች በሙሉ መፈጸሙን ያምን እንደሆነ ሲጠይቁት “አዎ” ሲል ተሰምቷል።
ሐንተር በሦስት የታክስ ወንጀሎች እንዲሁም በስድስት ቅጣቱ አነስ ባለ የታክስ ማጭበርበር ወንጀል ታሕሳስ ላይ ውሳኔ ይሰጥበታል።
ይህም ታክስን ማሳወቅ፣ መክፈል፣ ስወራ እና ሐሰተኛ ታክስ ማስመዝገብ ናቸው።
በፍርድ ቤት ሐንተር ላይ የቀረበው ክስ ከአገር ውጪ ባለው የንግድ እንቅስቃሴ እንዴት 7 ሚሊዮን ዶላር በአራት ዓመት ውስጥ እንዳገኘ ይዘረዝራል።
በእነዚህ አራት ዓመታት ብቻ 5 ሚሊዮን ብር “ከታክስ ውጪ ለሁሉም ነገር” ገንዘቡን ማውጣቱም ተጠቅሷል።
ይህም ሐንተር የንግድ ወጪዎች በሚል በሐሰተኛ በማስመዝገብ ለአደንዛዥ ዕጽ፣ ለቅንጡ ሆቴሎች እና መኪኖች፣ ለልብስ፣ ለሴቶች መሆኑ ተዘርዝሯል።
ዝርዝር ክሱ ሲነበብ “ ታክሱን ለመክፈል ዳተኛ በሆነባቸው ዓመታት ሁሉ ተከሳሹ ለመክፈል የሚያስችል በቂ ገቢ ነበረው” ካለ በኋላ “ነገር ግን ላለመክፈል ወስኗል” ሲል ይደመድማል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ልጃቸው ጥፋተኝነቱን አስመልክቶ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ታቅበዋል።












