በ90 ዓመታቸው የአፍሪካ ትልቁን ተራራ 14 ጊዜ የወጡት ኤርትራዊ

የ90 ዓመቱ ናይዝጊ ገብረ መድህን (ዶ/ር) መኖርያቸውን በኬንያ ናይሮቢ ያደረጉ ኤርትራዊ ናቸው። እርሳቸው ግን በሳቅ ታጅበው “የአዲስ አበባ፤ የአራዳ ልጅ ነኝ” ይላሉ።
ወላጆቻቸው ትውልዳቸው ኤርትራ ቢሆንም እርሳቸው ግን ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ነው።
ከትግርኛቸው ይልቅ አማርኛቸው ጥርት ብሎ እንደሚሰማም አልሸሸጉም።
የጄነራል ዊንጌት ተማሪ ነበሩ። በጄነራል ዊንጌት አምስት ዓመት ከተማሩ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቅያ ፈተና ወስደው ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው በወቅቱ መሐንዲስ ኮሌጅ (ሕንጻ ኮሌጅ) ተብሎ ወደሚጠራው ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ገቡ።
ሁለት ዓመት በሕንጻ ኮሌጅ ከተማሩ በኋላ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ፈቃድ ከሌሎች ሰባት ተማሪዎች ጋር በመሆን ወደ አሜሪካ ተልከው የምህንድስናቸውን ትምህርታቸውን አጠናቅቀዋል።
ከዚያ በኋላም ትምህርታቸውን በጀመሩበት ኮሌጅ በመምህርነት አገልግለዋል።
በዚህም የኮሌጁ ዲን እስከመሆን የደረሱት ናይዝጊ ወደ አሜሪካ አቅንተው በኧርባን ፕላኒንግ እና አርክቴክቸር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ጨርሰዋል።
ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በግላቸው እየሰሩ በነበረበት ሰዓት ወታደራዊው መንግሥት ወደ ስልጣን በመምጣቱ በግላቸው መስራት እንዳይችሉ አደረጋቸው።
ከዚያም በኋላ ወንድማቸው በመገደላቸው እኤአ በ1974 ወደ ናይሮቢ መጥተው መኖር ጀመሩ።
በኋላም ሦስት ልጆቻው እና ባለቤታቸው መጥተው ተቀላቅለዋቸዋል።
ማውንት ኬንያን 14 ጊዜ የወጡት ናይዝጊ
በ90 ዓመታቸው በአፍሪካ በትልቅነቱ ሁለተኛ የሆነውን ማውንት ኬንያን ለ14ኛ ጊዜ ወጥተው ነው ቢቢሲ ያገኛቸው። “አይከብድም?” ሲባሉ “ተራራ መውጣት እንኳን በ90፣ በ25 ዓመትም ከባድ ነው” ሲሉ ይመልሳሉ።
ከባሕር ጠለል በላይ ከ5000 ሜትር በላይ ከፍ የሚለው ማውንት ኬንያን ወጥቶ ለመጨረስ ሦስት ቀን ፈጅቶባቸዋል። ይህንን የኬንያ ተራሮች አውራ 14 ጊዜ ወጥተዋል።
በአፍሪካ በትልቅነቱ አንደኛ የሆነውን የታንዛንያውን ኪሊማንጃሮ ደግሞ አራት ጊዜ መውጣታቸውን ይጠቅሳሉ።
ገና የ25 ዓመት ወጣት ሳሉ፣ በሕንጻ ኮሌጅ ባልደረቦቻቸው ከነበሩ ፈረንጆች ጋር ለመዝናናት በመኪና ወደኬንያ በመጡበት ነው ታንዛንያ ሄደው ኪሎማንጃሮን የወጡት።
ያኔ ኬንያም ሆኑ ታንዛንያ (የቀድሞዋ ታንጋኒካ) በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ነበሩ።
ሞምባሳ ሄዶ ለመዝናናት ከፈረንጅ ጓደኞቻቸው ጋር ናይሮቢ የደረሱት ወጣቱ ናይዝጊ ሆቴል ገብቶ ለማደር፣ አንደልብ ለመንቀሳቀስ ጥቁር በመሆናቸው ብቻ ስለተቸገሩ መኪና ውስጥ ለማደር ተገድደው ነበር።
ለዚያ ነው ለጓደኞቻቸው ወደ ሞምባሳ እንደሚሄዱ ተናግረው እርሳቸው ወደ ኪሊማንጃሮ ያቀኑት።
ከዚህ በፊት ተራራ የመውጣት ልምድ ያልነበራቸው ናይዝጊ፣ ፎጣ ጣል አድርገው፣ ሳሳ ያለች ኮፍያ ጭንቅላታቸው ላይ ደፍተው ኪሊማንጃሮን ተያያዙት።
ተራራው ብቻ ሳይሆን ፀሀዩም ቆዳቸውን ፈተነው። ቢሆንም የእድሜ ልክ ልምድ ይዘው ከተራራው ወረዱ።
“በጣም ደስ አለኝ። ግን ሀይለኛ ስለነበር ቆዳዬ ተላላጠ። ቢከብደኝም ግን ወደድኩት” ይላሉ የወቅቱን ስሜታቸውን ሲያስታውሱ።
ኪሊማንጃሮን በ25 ዓመታቸው የወጡት ናይዝጊ 50 ዓመት ሲሞላቸው ሁለት ልጆቻቸውን ይዘው ደገሙት።
በርግጥ ሁለት ልጆቻቸው የእርሳቸውን ያህል ብርታት እና ድፍረት ስላልነበራቸው ለመውጣት አልደፈሩም።
ለሦስተኛ ጊዘ ደግሞ 75 ዓመት ሲሞላቸው፣ በመጨረሻም የ80 ዓመት አዛውንት ሆነው መውጣታቸውን ይናገራሉ።
ተራራ መውጣት የደስታቸው ምንጭ የሆነላቸው ናይዝጊ አሜሪካም ለጉብኝት በሄዱበት ወቅትም አነስ ያሉ ይሁኑ እንጂ ወጥተዋል።
ኤቨረስትንም ለመውጣት ፈልገው የነበረ ቢሆንም በሄዱበት ወቅት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ስጋት የነበረ በመሆኑ ሳይፈቀድላቸው በመቅረቱ ይቆጫቸዋል።
ኪሊማንጃሮን እና ማውንት ኬንያን የወጡት አዛውንቱ ናይዝጊ ከኢትዮጵያ ተራሮችስ ተብለው ሲጠየቁ ራስዳሸንን አልሞከርኩም ያው እንጦጦ ሰፈሬ ስለነበርን በልጅነቴ ላይ ታች ብዬበታለሁ ይላሉ በሳቅ ታጅበው።

ሦስት ትውልዶችን ይዞ ተራራ መውጣት
የሁለት ወንዶች እና አንድ ሴት ልጅ አባት የሆኑት አቶ ናይዝጊ ለ14ኛ ጊዜ ማውንት ኬንያን ሲወጡ ብቻቸውን አልነበሩም።
እንደ እርሳቸው በተራራ መውጣት ፍቅር የወደቀችው ሴት ልጃቸው ማርታ እና የልጅ ልጆቻቸው አብረዋቸው ነበሩ።
አቶ ናይዝጊ ከወንዶቹ ልጆቻቸው ይልቅ ሴቷ ልጃቸው “ታታሪ ተራራ ወጪ” መሆኗን ይመሰክራሉ።
ማርታም ይህንኑ ተራራ የመውጣት ፍቅር ለልጆቿ አውርሳ፣ አቶ ናይዝጊ ለ14ኛ ጊዜ ማውንት ኬንያ ተራራ እግር ስር ሲገኙ ከሁለት ልጆቿ ጋር በመሆን አብራቸው ለመውጣት መወሰኗን ይናገራሉ።
ይህ ብቻም ሳይሆን የአንድ ወንድ ልጃቸው ልጅም የዚህ የተራራ ጉዙ አካል ሆኗል።
በርግጥ ይላሉ አቶ ናይዝጊ፣ 80 ዓመቴ ላይ ኪሊማንጃሮን ስወጣም ማርታ አብራኝ ነበረች።
ከሦስት የልጅ ልጆቻቸው እና ከሴት ልጃቸው ጋር ማውንት ኬንያን የወጡት አቶ ናይዝጊ፣ ከሦስት ትውልድ ጋር ተራራ መውጣት የፈጠረባቸውን ስሜት ሲናገሩ “ሰላም፣ ደስታ፣ አምላኬን ተመስገን የማለት ስሜት ነው የሚሰማኝ” ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, NAIZGI
በ90 ዓመታቸው ተራራ ለመውጣት ምስጢሩ ምንድን ነው?
ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ እንጦጦ አካባቢ በመሆኑ ለአሁኑ ጥንካሬያቸው አስተዋጽኦ ማድረጉን ያምናሉ።
“አንድ ጊዜ ተመርምሬ በደሜ ውስጥ ያለው ቀይ የደም ሴል ከሌሎች የእድሜ እኩዮቼ እንደሚበልጥ ነግረውኛል። ምናልባት ደጋማ አካባቢ ስለተወለድኩ ይሆናል።”
ይህ ተፈጥሯዊ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን “ጨከን ብሎ ለጤና ትኩረት መስጠትም” በ90 ዓመታቸው ተራራን ቀልጠፍ ብሎ ለመውጣት እንደረዳቸው ያምናሉ።
“ጨከን ብሎ፣ ድካምን ወደዚያ ብሎ፣ ትንሽ ታታሪ መሆን የሚያስፈልግ ይመስለኛል።”
የ90 ዓመቱ ናይዝጊ፣ የጄነራል ዊንጌት ተማሪ ሳሉ ቦክሰኛ ነበሩ። “በወቅቱ ሌሎች ተማሪዎች ቦክስን በጣም ይጠሉት ነበር፤ እኔ ግን በቁመትም እምብዛም ባልሆንም፣ ጥሩ ቦክሰኛ ሆኜ ነበር፤ የመኪና ሽቅድምድምም ሁለት ሦስት ጊዜ ገብቼ ተወዳድሬያለሁ።”
ጋራ ለመውጣት ያበረታታቸው የእነዚህ ስፖርቶች ፍቅር ይሁን ሌላ በውል ባይለዩትም “እኔ ግን ታታሪ ነኝ እላለሁ” ይላሉ።
ተራራ መውጣት ከአካላዊ ጥንካሬ ወዲህ የስነልቦና ብርታት ይጠይቃል።
ታድያ የ90 ዓመቱ አዛውንት ይህንን ከየት አመጡት?
“መቀመጥ መቆመጥ ማለት ነው። ቁጭ ማለት ሁል ጊዜ ሰውነታችንን ያጠምነዋል። እኔ ሁል ጊዜ እንቀሳቀሳለሁ። በእግር እሄዳለሁ፣ ፑሽአፕ እሰራለሁ። በጣም አድርጌ አንቀሳቀሳለሁ። ይህ የጠቀመኝ ይመስለኛል” ይላሉ።
አካላዊ እንቅስቃሴ፣ የመንፈስ ጽናት ብቻ አይደለም የአዛውንቱ የብርታት ምስጢር፣ ምግባቸው ላይም ጥንቃቄ አንደሚያደርጉ አክለውም ገልጸዋል።
አስተዳደጋቸው እንደ ማንኛውም ዝቅተኛ ኑሮ እንደሚኖር ኢትዮጵያዊ ከስጋ ተለያይተው፣ ሽሮ እና ምስር ያዘወትሩ እንደነበር ያስታውሳሉ።
አሁንም ቢሆን በዕለት ተዕለት አመጋገባቸው ውስጥ የሚያዘወትሩት አትክልት እና ጥራጥሬ መሆኑን እነሽሮ፣ ምስር አተር ክክ ገበታቸው ላይ እንደማይጠፋ ገልጸው “ ያ ረድቶኝ ይሆናል ባይ ነኝ” ብለዋል።
ሌላው ይላሉ አዛውንቱ “ በሰውነት ላይ መጨከን. . . ደከመኝ የሚለውን በቀላሉ አልቀበለውም። አይዞህ ነው የምለው። ተነስ እላለሁ ራሴን። ድሮም በደንብ እንቀሳቀስ ነበር አሁንም እንቀሳቀሳለሁ”
አካል ብቻ ሳይሆን አእምሮም መገንባት አለበት የሚሉት አቶ ናይግዚ፣ በቀላሉ እንዳይደክም የተለያዩ አይነት አእምሮን የሚፈትኑ ጨዋታዎች (ፐዝልስ) ያስፈልገዋል ባይ ናቸው።
ስለዚህ አእምሯቸውን ለማንቀሳቀስ የሚገጣጠሙ ጨዋታዎች (ጂግሶው ፐዝልስ) ይጫወታሉ።
“ሱዶኮ እጫወታለሁ። ያም ጠቅሞኛል።”
“ብዙ ነገር አነባለሁ” የሚሉት አቶ ናይግዚ፣ ምንም አንኳ ሙዚቃ ባይጫወቱም ክላሲክ ሙዚቃዎችን እንደሚያደምጡ ይህም እንደጠቀማቸው ያምናሉ።
መደሰት ያስፈልጋል የሚሉት አዛውንቱ ናይግዚ፣ “በባህላችን ጮክ ብሎ የሚስቅ ከቁምነገርም አይወሰደም። ፊቱን ጠቆር የሚያደርግ ነው ተመራጭ፤ ይህ ትክክል አይደለም። ለሰውነታችን ፈገግታ፣ ሳቅ ያስፈልጋል፤ ለመደሰት መሞከር ከባድ የጤና ሚስጥር አለው” ይላሉ።
ቁዘማ ላይ ችክ ማለት እንደማይወዱ የሚናገሩት አቶ ናይግዚ እርሳቸውም አዘውትረው ለመደሰት እና ለመሳቅ እንደሚጥሩ ይናገራሉ።
የአቶ ናይዝጊ አንድ ቀን ውሎ ምን ይመስላል?
ማለዳ ተነስተው መጽሐፍ ቅዱስ በሦስት ቋንቋዎች ሦሰት ሦሰት ምዕራፍ ያነባሉ።
በአማርኛ፣ በትግርኛ እና በእንግሊዘኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባቸውን ከጨረሱ በኋላ፣ ጸልየው አልጋቸው ላይ እንዳሉ እግራቸውን እና ወገባቸውን ከፍ እያደረጉ ስፖርት ይሰራሉ።
ከዚያ ሲነሱ አጃ፣ ዘቢብ፣ ኦቾሎኒ አድርገው በወተት ቁርሳቸውን ይበላሉ።
በመቀጠል በእግራቸው ከ10ሺህ እስከ 15 ሺህ እርምጃዎች ይጓዛሉ።
“ይህ እንግዲህ በኪሎሜትር ሲሰላ 7ኪሎ ሜትር ይሆናል። ይህንን ሁሌ አላቋርጥም።
ከዚያ በኋላ መጽሐፍት አነባለሁ። አትክልቶችንም በጣም ስለምወድ በመጠኑ አትክልቶቼን የሚተከልም ካለ እተክላለሁ፤ የሚከረከምም ካለ እየከረከምኩ እንከባከባለሁ” ይላሉ።
አቶ ናይዝጊ የሚኖሩበት ምድረ ግቢ ሰፊ ነው። እርሳቸው እንደሚሉት ከ4ሺህ እስከ 5 ሺህ ካሬ ሜትር ይሆናል።”
በዚህ ምድረ ግቢ ጌሾ፣ ቡና፣ ጥድ፣ የኮሶ፣ የአባካዶ ዛፎች በብዛት ይገኛሉ።
“እዚህ የሚኖሩ ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውን ጠላ መጥመቅ ሲፈልጉ እኔ ቤት መጥቶ ነው የሚቆርጡት” ይላሉ በሳቅ እንደታጀቡ።












