የኤሌክትሪክ ታሪፍ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በየሦስት ወሩ ጭማሪ ሊደረግበት ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከመጪው መስከረም 2017 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2020 ዓ.ም. ድረስ በየሦስት ወሩ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ላይ ጭማሪ እንደሚያደርግ አስታወቀ።
በአዲሱ የታሪፍ ማሻሻያ መሰረት የመኖሪያ ቤት ኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚዎች በአራት ዓመት ውስጥ ከ256.4 እስከ 477.7 በመቶ የሚደርስ የክፍያ ጭማሪ ይደረግባቸዋል።
መንግሥታዊው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሻጭ ተቋም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፤ ይህንን ያስታወቀው ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 29፤ 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
መግለጫው፤ የተቋሙ የ2016 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2017 “የትኩረት መስኮች” ላይ ያተኮረ ሲሆን አገልግሎቱ ከመጪው ዓመት ጀምሮ ሊተገብር ስላቀደው የታሪፍ ጭማሪም ገለጻ ተደርጎበታል።
ከመስከረም 2017 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው አዲሱ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ጭማሪ፤ በመኖሪያ ቤት እና ንግድ ተጠቃሚዎች እንዲሁም የአነስተኛ እና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች የፍጆታ ክፍያን የሚመለከት ነው። የመንገድ መብራት ታሪፍም በዚሁ የታሪፍ ማስተካከያ ውስጥ እንደተካተተ ተቋሙ ማሻሻያውን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በፅሁፍ በሰጠው መረጃ ላይ ተጠቅሷል።
ኤሌክትሪክ አገልግሎት ይህንን ጭማሪ ያደረገው “ከሁለት ዓመት በፊት” መደረግ የነበረበት የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ተግባራዊ ሳይሆን በመቆየቱ እንደሆነ አስታውቋል። በአሁኑ ወቅት ኤሌክትሪክ የሚሸጥበት ዋጋ ተቋሙ መሰረተ ልማት ዝርጋታ እና ለመልሶ ግንባታ ስራ “የሚያወጣውን ወጪ የሚሸፍን” እንዳልሆነ ተገልጿል።
ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ውስጥ በመሰረተ ልማት ግብዓቶች የገበያ ዋጋ ላይ በታየው ጭማሪ ምክንያት ተቋሙ ሊያወጣ አቅዶ የነበረው 13.7 ቢሊዮን ብር የኢንቨስትመንት ወጪ ወደ 19.6 ቢሊዮን ብር ማደጉን በማሳያነት ጠቅሷል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት በተጠናቀቀው የ2016 በጀት ዓመት ከኢነርጂ ሽያጭ እና ከተለያዩ ገቢዎች 42.47 ቢሊየን ብር ያገኘ ቢሆንም በዚሁ በጀት ዓመት ያወጣው ወጪ የ11.43 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው አስታውቋል። ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት ለኢነርጂ ኃይል ግዢ እንዲሁም ለመደበኛ እና ለካፒታል በጀት ያወጣው ከ53.9 ቢሊዮን ብር በላይ ነው ተብሏል።
በተቋሙ ወጪ ከፍተኛነት ምክንያት እንደሚደረግ የተገለጸው የታሪፍ ማሻሻያ፤ ለአንድ ዓመት ያህል “በሶስተኛ ወገን ባለሙያዎች” እንዲሁም የኤሌክትሪክ ኃይል እና ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለሙያዎች በጋራ ጥናት የተደረገበት እንደሆነ ተቋሙ ገልጿል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሰኔ 13/2016 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ በጥናቱ የተገኘውን የማሻሻያ መጠን እንዳጸደቀውም አክሏል።
የታሪፍ ጭማሪው ትግበራ “የዋጋ ውድነትን እና ዋጋ ግሽበትን እንዳያባብስ” እንዲሁም የጭማሪውን “ጫናን ለመቀነስ” ሁለት ተግባራት እንደሚከናወኑ ተቋሙ ገልጿል። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎችን “የመክፈል አቅም ያገነዘበ” ድጎማ እንደሚደረግ ያስታወቀው አገልግሎቱ፤ የድጎማው ተጠቃሚ የሚሆኑት ከዜሮ እስከ 200 ኪሎ ዋት ፍጆታ ላላቸው ተጠቃሚዎች እንደሆነ ጠቅሷል።

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Electric Utility
ከዜሮ እስከ 50 ኪሎ ዋት የሚጠቀሙ ደንበኞች መደረግ ከነበረበት የታሪፍ ጭማሪ ውስጥ 84 በመቶውን እንደሚደጎሙ የተቋሙ መረጃ ያሳያል። ከ51 እስከ 100 ኪሎ ዋት ፍጆታ ያላቸው ተጠቃሚዎች የሚደረግላቸው ድጎማ 61 በመቶ ሲሆን ከ101 እስከ 200 ኪሎ ዋት ባለው ምድብ ውስጥ የሚወድቁት 35 በመቶ ይደጎማሉ ተብሏል።
የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያደርገው የታሪፍ ጭማሪ በአንድ ጊዜ መተግብሩ የሚያስከትለውን ጫና ለመቀነስ ሲባል ማሻሻያው እስከ 2020 ድረስ እንዲደረግ መወሰኑን ተቋሙ አስታውቋል። “አሁን ተግባራዊ የሚደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ከመስከረም 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በየሩብ ዓመቱ ተከፋፍሎ ለአራት ተከታታይ ዓመት እስከ 2020 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ ይሆናል” ሲል ተቋሙ እቅዱን አስረድቷል።
በወርሃዊ የአሌክትሪክ ፍጆታቸው በተለያየ ምድብ ውስጥ ከሚገኙ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚዎች መካከል በአራት ዓመት ውስጥ ከፍተኛ የሆነው የ477.7 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ የሚደረገው ከዜሮ እስከ 50 ኪሎ ዋት በሚጠቀሙ ደንበኞች ላይ ነው።
ዝቅተኛ የሆነው የ254.4 በመቶ ጭማሪ የሚደረገው ደግሞ ከ101 እስከ 200 ኪሎ ዋት ተጠቃሚ በሆኑ የመኖሪያ ቤት ደንበኞች ላይ ነው።
ከ201 እስከ 300 ኪሎ ዋት ባለው መደብ ውስጥ የሚወድቁ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ደንበኞች በአራት ዓመት ውስጥ ክፍያቸው በ367.5 በመቶ ይጨምራል።
ለምሳሌ፤ በወር ውስጥ 300 ኪሎ ዋት የሚጠቀም ደንበኛ አሁን ባለው ታሪፍ የአገልግሎት ክፍያን ጨምሮ 642 ብር ይከፍላል። አሁን የሚደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ሲተገበር ከአራት ዓመት በኋላ የደንበኛው ወርሃዊ ክፍያ 2,847 ብር ይደርሳል።












