የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ በግድያ እና እገታ የጸጥታ ኃይሎች እጅ እንዳለበት አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, SM
የአማራ ክልል መንግሥት ከሰሞኑ የሕዝብ ቁጣ በቀሰቀሰው ግድያ እና እገታ የጸጥታ አስከባሪዎች ተሳታፊ መሆናቸውን ገለጸ።
የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ትናንት ነሐሴ 28/2016 ዓ.ም. ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በሁሉም የአማራ ክልል አካባቢዎች ግድያ እና እገታ መኖሩን ጠቁሟል።
መግለጫው የወጣው በጎንደር ከተማ የሁለት ዓመት ህጻን በአጋቾች መገደሏን ተከትሎ ቁጣቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡ ሰልፈኞች “በመንግሥት ኃይሎች” መገደላቸው ከተገለጸ በኋላ ነው።
ቢሮ ለክልሉ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል የሰላም እጦት ዋነኛ ችግር መሆኑን በጠቆመበት መግለጫው፤ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በግድያ እና እገታዎች እጃቸው እንዳለበት አምኗል።
በጎንደር ከተማ የሚፈጸሙ ግድያ እና እገታ “ታቅዶ የሚፈጸም የጠላት አጀንዳ” ነው ያለው ሰላምና ጸጥታ ቢሮው፤ “ጥቂት” ያላቸው የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ያሉ ኃይሎች “አባሪ እና ተባባሪ” መሆናቸውን አስታውቋል።
ቢሮው 14 የጸጥታ ኃይሎችን በግድያ እና እገታ ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር እንዳዋለ በመግለጽ ምርመራ ከፍቻለሁ ብሏል።
“. . . ጥቂት የሥነ ምግባር ብልሽት ያለባቸው አካላት በዚህ ድርጊት [ግድያ እና እገታ] ተሳታፊ ናቸው በሚል ተጠርጥረው አስፈላጊው እርምጃ እየተወሰደባቸው ይገኛል” ብሏል።
ቢሮው ስለ ምርመራው፣ በቁጥጥር ስር አዋልኳቸው ስላላቸው የጸጥታ ኃይሎች ደረጀም ሆነ በየትኛው የጸጥታ መዋቅር እንዳሉ ግን አልጠቀሰም።
በአማራ ክልል መከላከያ ሰራዊትን ጨምሮ ሌሎች የፌደራል የጸጥታ ኃይሎች፣ የክልሉ ፖሊስ፣ አድማ ብተና እና ሚሊሻ የሚባሉ የጸጥታ አደረጃጀቶች ይገኛሉ።
ሆኖም የአማራ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ በክልሉ እየተፈጸመ ላለው ግድያ እና እገታ በስም ያልጠቀሰው “ታጣቂ ቡድን” የሀብት ማግኛ መንገድ አድርጎ “በዋነኛነት” እየፈጸመ ነው ሲል ከሷል።
“ፕሮጀክት” ሲል የጠራውን ግድያ እና እገታ የሚፈጽመው “ታጣቂ ቡድኑ” እንደሆነ ማረጋገጫ “መረጃ እና ማስረጃ” እንዳለው የገለጸው ቢሮው፤ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጿል።
ሰሞኑን በጎንደር ከተማ የተፈጸሙትን ግድያዎች እና እገታዎች ገንዘብ ከማግኘት ባሻገር ናቸው ያለው ቢሮው፤ “ታጣቂ ቡድኑ” ሕዝቡ መንግሥት ላይ እንዲያምጽ ለማድረግ “ከአገር ውስጥ እና ከውጭ ጠላቶች” ጋር የያዘው እቅድ ነው ሲል ወንጅሏል።
እውነቱ ይህ ቢሆንም ችግሩን ጠቅልሎ ለመንግሥት መስጠት “አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ነው” ሲል ኃላፊነቱ የእርሱ ብቻ እንዳልሆነም ጠቁሟል።
“. . .እውነቱን በማድበስበስ ችግሩን ለመንግሥት አካል ጠቅልሎ በመስጠት አጥፊውን ኃይል ነጻ ለማድረግ መሞከር አህያውን ትቶ ዳውለውን እንዲሉ የማደናገሪያ አጀንዳ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት በመሆኑ ሊታረም ይገባል” ብሏል።
ሕዝቡ “ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳ” አላቸው ባላቸው ኃይሎች ተጠልፎ “ያልተገባ ቅስቀሳ እና የአመጽ ጥሪ፣ የተሸከርካሪ ገደብ፣ የስራ እንቅስቃሴን ማስተጓጎል” የመሰሉ እርምጃዎች “ውጤት አልባ እና የኋላቀርነት ማሳያ” አድርጎ ሊወሰድ ይገባል” ሲልም አሳስቧል።
የክልሉ መንግሥት አወስዳለሁ ላለው እርምጃ ‘የሚስጥር ጥቆማ መስጫ እና ነጻ የስልክ መስመር’ እንደሚዘረጋም ጠቁሞ፤ ለዚህም ሕዝቡ እንዲተባበረው ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሕግ ማስከበሩ በመላላቱ ሰላማዊ ዜጎች በታጣቂዎች፣ በተደራጁ ቡድኖች እና በአንዳንድ የመንግሥት የጸጥታ አካላት የሚደርስባቸው እገታ ተባብሷል ብሏል።
በአማራ ክልል ከሐምሌ 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ በመንግሥት እና በፋኖ ኃይሎች መካከል የትጥቅ ግጭት የተጀመረ ሲሆን፤ ነዋሪዎች ግድያ እና እገታን ጨምሮ እስራት፣ እንግልት፣ አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ መገደድ፣ የእንቅስቃሴ እና ስራ ገደብ እና ሌሎች ጥሰቶች እንደሚገጥሟቸው ይናገራሉ።












