የአቶ ታዬ የዋስትና ጥያቄ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, Prosperity Party
የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታ አቶ ታዬ ደንደአ የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቡት ጥያቄ በችሎቱ ውድቅ ተደረገ።
አቶ ታዬ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸው እንዲከበር ይግባኝ የጠየቁት ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም. በነበረ ችሎት በከፍተኛ ፍርድ ቤት የዋስትና መብት ጥያቄያቸው ውድቅ ከተደረገ በኋላ ነው።
የቀድሞ ሚኒስትር ዲኤታ እና የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት አባሉ ፀረ ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ እና ጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት በሚሉ ወንጀሎች ተከሰው ጉዳያቸው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲታይ መቆየቱ ይታወሳል።
ዐቃቤ ሕግ አቶ ታዬ ደንደአ መገናኛ ብዙኃን እና ማኅበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ሁከት የሚያስነሱ እና “ፀረ ሰላም የሆኑ የኦነግ-ሸኔ እና ፋኖ ኃይሎችን” ዓላማዎች የሚያሳኩ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ነበር እንዲሁም ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት የሚሉ ሦስት ክሶች መስርቶባቸው እንደነበረ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ አቶ ታዬ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋሯቸው ጽሑፎች የሰላም ጥሪ እንጂ ሁከት ቀስቃሽ አለመሆናቸውን እንዲሁም በመኖሪያ ቤታቸው የተገኘው ጦር መሳሪያ መንግሥት ለደኅንነታቸው ሲባል ያስታጠቃቸው መሆኑን በመናገር ከዚህ ቀደም ተከራክረዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ መንግሥት እና የሽብር ወንጀል ችሎት ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም. በዋለው ችሎት አቶ ታዬ ያስተላለፏቸው መልዕክቶች ሁከት የሚያስነሱ መሆን አለመሆናቸውን እንዲሁም የሕዝብ ሞራል እና የግለሰቦች መብትን የሚጣረሱ መሆን አለመሆናቸውን መመርመሩን ገልጿል።
በዚህ መሠረት አመጽ መቀስቀስ እና ፀረ ሰላም ኃይሎችን መደገፍ በሚል የቀረበባቸውን ክስ መከላከል ሳያስፈልጋቸው አቶ ታዬ ነጻ ተብለው በሦስተኛው ክስ ግን እራሳቸውን እንዲከላከሉ ተወስኗል።
ይህን ተከትሎ አቶ ታዬ በዕለቱ (ሐምሌ 30/2016 ዓ.ም.) ከቀረቡባቸው ሦስት ክሶች መካከል በሁለቱ ነጻ መባላቸውን ተከትሎ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸው እንዲጠብቅላቸው ጠይቀው ነበር።
ይሁን እንጂ የአቶ ታዬ አንዲከላከሉ የታዘዙበት ክስ እስከ 20 ዓመት የሚያስቀጣ ነው በማለት የዋስትና ጥያቄያቸውን ዐቃቤ ሕግ ተቃውሞ ተከራክሯል። ችሎቱም የዐቃቤ ህግን መከራከሪያ በመቀበል የአቶ ታዬ የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አድርጓል።
የዋስትና ጥያቄያቸው ውድቅ የተደረገባቸው አቶ ታዬ ይግባኝ ሲሉ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርበዋል።
ከዚህ ቀደም በጠበቆቻቸው ላይ ማስፈራራት እየደረሰ በመሆኑ ብቻቸውን ችሎት ፊት ቀርበው የነበሩት አቶ ታዬ፤ በዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 29/2016 ዓ.ም. በነበረው ችሎትም እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ያለ ጠበቃ ነበር የተገኙት።
ጠቅላይ ፍርድ ቤት በዛሬው ውሎው አቶ ታዬ የተከሰሱበት ሦስተኛው ክስ ከ8-25 ዓመታት በእስር እንደሚያስቀጣ እንዲሁም ተከሳሹ በሚፈለጉበት ጊዜ ፍርድ ቤት ላይቀርቡ ይችላሉ በሚል የታችኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን አጽንቷል።
አቶ ታዬ በቀረበባቸው ሦስተኛው ክስ መከላከያቸውን እንዲያቀርቡ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ለጥቅምት 8/2017 ዓ.ም. ለተዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።












