በዩኬ መኪና ስር ተደብቆ ከእስር ቤት ያመለጠውን የሽብር ተጠርጣሪ ለመያዝ ሰፊ ዘመቻ ተጀመረ

የፎቶው ባለመብት, MET POLICE
በዩናይትድ ኪንግደም በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ በእስር ላይ የነበረው ወታደር ከእስር ቤት ካመለጠ በኋላ በመላው አገሪቱ እስረኛውን ለመያዘ ፍለጋ ተጀመረ።
የ21 ዓመቱ ዳንኤል ከህሊፍ በአንድ ወታደራዊ ጣቢያ ሐሰተኛ ቦምብ በማስቀመጥ እና ለውጭ ጠላት መረጃ ለማቀበል በመመሳጠር ነበር ክስ የተመሰረተበት።
የክስ ሂደቱን ሲጠባበቅ የነበረው የቀድሞ የአገሪቱ ሠራዊት አባል ለእስር ቤቱ ምግብ በሚያመላልስ መኪና ስር ተደብቆ ትናንት ጠዋት ከእስር ቤቱ መውጣቱ ተገልጿል።
ዳንኤል ከህሊፍን ለመያዝ ፖሊስ በአየር ማረፊያዎች እና በወደቦች ፍተሻ እያደረገ ሲሆን እንደ ሂትሮው እና ማንቸስተር አየር ማረፊያዎች እንዲሁም በዶቨር ወደብ ተጓዦች መዘግየት እና መጉላለት እያጋጠማቸው ነው ተብሏል።
የአገሪቱ ማረሚያ ቤቶች አስተዳዳሪ እስረኛው እንዴት ሊያመልጥ እንደቻለ “አስቸኳይ ምርመራ” ለማድረግ ከፖሊስ ጋር ተጣምሮ እየሰራ ነው።
እአአ 2019 ላይ የዩኬን ጦር ሠራዊት የተቀላቀለው ዳንኤል ከህሊፍን ለመያዝ በመላ አገሪቱ ፍለጋው ቢጠናከርም እስካሁን ድረስ የሽብር ተጠርጣሪውን መልሶ ለመያዝ የሚያችል ምንም አይነት ፍንጭ አለማግኘቱን ፖሊስ አስታውቋል።
የፖሊስ የጸረ ሽብር አዛዥ የሆኑት ዶሚኒክ መርፊ በአገሪቱ ያሉ ሁሉም የፖሊስ አባላት እንዲሁም የድንበር ጠባቂዎች ከእስር ስላመለጠው የሽብር ተጠርጣሪ እንዲያውቁት ተደርጓል ብለዋል።
ዶሚኒክ መርፊ ተጠርጣሪው ይኖርበታል የተባለ የለንደን አካባቢ ላይ ትኩረት ተደርጎ ፍለጋው ቢጠናከርም ግለሰቡ ግን በየትኛውም የአገሪቱ ከፍል ውስጥ ሊኖር ይችላል ብለዋል።
ዳንኤል ከህሊፍ ሐሰተኛ ቦምብ በጦር ሰፈር አስቀምጧል ከሚለው ክስ በተጨማሪ የዩኬ ባላጣ ለሆነ አገር ሚስጥራዊ መረጃ አሳልፎ ለመስጠት ሲያሴር ነበር የሚል ክስም ቀርቦበታል።
የግለሰቡን ከእስር ማምለጥ ተከትሎ በዩኬ መንግሥት ላይ ትችቶች እየተሰነዘሩ ነው። የተቃዋሚው ሌበር ፓርቲ አመራሮች ዳንኤሌ ከህሊፍ ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግበት እስር ቤት መቆየት ነበረበት ሲሉ የትችት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል።
በተመሳሳይ የደኅንነት ባለሙያዎች እንዳ ዳንኤል ከህሊፍ ያሉ የብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሆኑ እስረኞች የደኅንነት ጥበቃቸው ከፍተኛ ባልሆኑ እስር ቤቶች መያዝ የለባቸውም ይላሉ።
በዩኬ እስረኛ ከማረሚያ ቤት አምልጧል የሚል ዜና መስመት የተለመደ አይደለም። ከእአአ 2017 ጀምሮ ከእስር ቤት ያመለጡ እስረኞች ቁጥር ከአምስት አይበልጥም።












