ሕጻናትን ሲሸጥ በቢቢሲ የተጋለጠው ኬንያዊ የሆስፒታል ሠራተኛ ጥፋተኛ ተባለ

ጨቅላ ሕጻናትን ከሆስፒታል ሰርቆ በጥቁር ገበያ ሲሸጥ በቢቢሲ የምርመራ ዘገባ የተጋለጠው ኬንያዊ የሆስፒታል ሠራተኛ ጥፋተኛ ተባለ።
ፍሬድ ሌፓራን የተባለው ግለሰብ የማማ ሉሲ ኪባኪ ሆስፒታል ሠራተኛ ሳለ በሆስፒታሉ የነበረን አንድ ጨቅላ ወንድ ልጅን በ2ሺህ 500 ዶላር ለመሸጥ ገንዘብ ሲቀበል በቢቢሲ ተቀርጿል።
ግለሰቡ የምርመራ ዘገባውን ተከትሎ እአአ 2020 ላይ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን ከሁለት ሳምንታት በኋላ ደግሞ የእስር ፍርድ ውሳኔ ይሰጠዋል።
የቢቢሲ አፍሪካ አይ ሪፖርተር ገዢ በመምሰል ፍሬድ ሌፓራን ከቀረበች በኋላ ግለሰቡ ከሆስፒታሉ ወደ መንግሥታዊ የሕጻናት መንከባከቢያ ማዕከል ከሚዘዋወሩ ሕጻናት መካከል አንድ ወንድ ልጅ ሊሸጥላት ተስማምቷል።
ሌፓራን ጨቅላውን ለገዢዋ በሚያስረክብበት ዕለት ሦስት ጨቅላ ሕጻናት ወደ መንግሥታዊው ተቋም የሚሸጋገሩ ቢሆንም ከሆስፒታሉ ወደ ሕጻናት መንከባከቢያ ማዕከሉ ሁለት ሕጻናት ብቻ እንደሚዘዋወሩ በማስመሰል ሰነድ አጭበርብሯል።
ምንም እንኳ ግለሰቡ ወንጀሉን ሲፈጽም የሚያሳዩ ማስረጃዎች ቢኖሩም ፍሬድ በኬንያ ያሉ ጠንካራ የሕግ አማካሪዎችን በመቅጠር ከሁለት ዓመታት በላይ የቀረበበትን ክስ ሲከራከር ቆይቷል።
ይሁን እንጂ የቀረበበትን የሰው እና ሰነድ ማስረጃ መከላከል ሳይችል የቀረ ሲሆን ሕጻን ልጅ ለመሸጥ ሲስማማ እና ገንዘብ ሲቀበል በቢቢሲ የተቀረጸው እርሱ ስለመሆኑ ከብዙ ክርክር በኋላ አምኗል።
ቢቢሲ በዚህ የምርመራ ዘገባው ማማ ሉሲ ኪባኪ ከተባለው ሆስፒታል የአንድ ልጅ ሕገ-ወጥ የሽያጭ ሙከራን ያጋልጥ እንጂ አንድ የተቋሙ ሠራተኛ በሁለት ወራት ውስጥ ብቻ 12 ሕጻናት የገቡበት መጥፋቱን ለቢቢሲ ቃሉን ሰጥቷል።
“ብዙ ሰዎች ሙሰኞች ናቸው። ትንሽ ነገር ከተሰጣቸው ምንም ነገር አይናገሩም” በማለት በሆስፒታሉ ሠራተኞች ውስጥ ስላለው ብልሹ አሰራር ተናግሯል።
በኬንያ መሃንነት እና ልጅን በማደጎ መውሰድ የሚያስከትለውን መገለል እና የተንዛዛ የሕግ አሰራርን በመሸሽ በርካቶች የተሰረቁ ልጆችን እንደ አማራጭ ይወስዳሉ።
ቢቢሲ አፍሪካ አይ በአንድ ሆስፒታል ውስጥ ያለን የጨቅላ ልጆች ስርቆትን በተመለከት ያለውን ሕገ-ወጥ አሰራር አጋለጠ እንጂ በኬንያ በግል ክሊኒኮች የልጆች ሽያጭ ይካሄዳል።
በርካታ ሕጻናት ከመንገድ ላይ በኃይል ታፍነው ይሰረቃሉ፤ እንዲሁም ቤት አልባ እና አቅም የሌላቸው እናቶች ልጆቻቸውን ይነጠቃሉ።
በኬንያ ናይሮቢ ሕጻናት ከሚሸጡባቸው ክሊኒኮች መካከል አንዱ ሜሪ ኡማ የተባለች ሴት የምታስተዳድረው ክሊኒክ ይገኝበታል።
በዚህ ክሊኒክ ተጋላጭ የሆኑ ነብሰ ጡር እናቶች በክሊኒኩ ገንዘብ ተከፍሏቸው ከወለዱ በኋላ የወለዱትን ጨቅላ ጥለው ይሄዳሉ። ሜሪ ኡማ የተባለችው ሴትም አዲስ የተወለዱትን ጨቅላ ልጆች በትርፍ ትሸጣለች።
ቢቢሲ ይህን ክሊኒክ በምርመራ ዘገባው ካጋለጠ በኋላ የሜሪ አድራሻ የጠፋ ሲሆን ክሊኒኩም ዝግ ሆኗል።
እንደ ኬንያ መንግሥት አሃዝ ከሆነ ከሐምሌ 2014 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 2015 ዓ.ም. ድረስ 8ሺህ 841 ሕጻናት የጠፉ ተብለው የተመዘገቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 1ሺህ 296 የሚሆኑት ብቻ ናቸው ከቤተሰቦቻቸው ጋር መልሰው መቀላቀል የቻሉት።
የኬንያ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት አባል የሆኑት ሙኤኒ ሙቲስይ በየሳምንቱ ቢያንስ የአምስት ልጆች መጥፋት ሪፖርት እንደሚደርሳቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።












