ግብጽ ወታደሮቿን በሶማሊያ ማስፈሯ ያለው አንድምታ ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, MAAT GROUP
በቅርቡ በሶማሊያ እና በግብጽ መካከል የተፈረመው ወታደራዊ ስምምነት ተግባራዊ ወደ መሆን ተሸጋግሯል።
ለዚያም ነው የግብጽ ሁለት ወታደራዊ አውሮፕላኖች በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ የጦር ጄነራሎችን እና መሳርያዎችን ይዘው ማረፋቸው የተሰማው።
በግብጽ የሶማሊያ አምባሳደር አሊ አብዲ አዋሬ፣ ይህ የግብጽ ጦር ከጥር 2025 ጀምሮ የአፍሪካ ህብረት ጥላ ሥር በመሆን የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)ን የሚተካው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ከመተካቱ በፊት የሆነ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም በመጪው ዓመት ጥር ወር የሚጠናቀቀው በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ)ን የሚተካው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ በተለያዩ ጊዜያት የሚሰማሩ 10 ሺህ ወታደሮችን ግብጽ ለማሰማራት ዕቅድ ይዛለች።
የግብጽ ጦር የሶማሊያ መሬት ላይ እግሩን ማሳረፉ በኢትዮጵያ ዘንድ በበጎ አልታየም።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ባለው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት፣ ራስን እንደ ነጻ አገር ካወጀችው እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር የባህር ኃይል ጣብያ ለማግኘት ባደረገችው ስምምነት የተነሳ ከግብጽ እና ከሶማሊያ ጋር ሆድና ጀርባ ከሆነች ሰንበትበት ብሏል።
ምንም እንኳ ግብጽ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ አየር ማረፍያ ስለደረሱት የጦር ጄነራሎቿ እና መሳርያዎቿ ያለችው ነገር ባይኖርም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ግን፣ በአፍሪካ ቀንድ ውጥረት መንገሱን የጦርነት ነጋሪት ጉሰማ መሆኑን በማንሳት ይህ ለአዲስ አበባ የተላከ መልዕክት ነው እያሉ ይገኛሉ።
ሌሎች ደግሞ ግብጽ ሶማሊያ ለጠየቀችው ድጋፍ በተለይ ደግሞ በቀይ ባሕር ላይ የራሷን ብሔራዊ ፍላጎት ለማስጠበቅ እና ለመከላከል ላቀረበችው ጥያቄ የተሰነዘረ የበጎነት እጅ የውጪ ጉዳይዋ ፖሊሲ አካል ነው ይላሉ።
ይህ የሁለቱ አገራት ጥምረት ግን ዳግም በአፍሪካ ቀንድ የውጪ አገራት ፍላጎት እና ተሳትፎ ላይ በተለይም ቱርክ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ያላቸው ፍላጎት ላይ ትኩረት እንዲደረግ ያደረገ ነው።
የግብጽ ፍላጎት
ባለፉት ዓመታት ግብጽ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ያላትን ወታደራዊ እና የደኅንነት ትብብሮችን ለማስፋት ፍላጎት ስታሳይ ቆይታለች።
ግብጽ ከኢትዮጵያ ጋር በህዳሴ ግድብ ላይ የምታደርገው ድርድር መቋጫ ባያገኝም፣ በሱዳን ግጭት ውስጥ ሊኖራት የምትፈልገው ተጽዕኖ የምትፈልገውን ያህል ውጤት ባያመጣም፣ በቀይ ባሕር ላይ የየመኖቹ ሁቲዎች የሚያደርሱት ጥቃት ቢጨምርም እየተዳከመ የሚገኘው የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዋ ላይ ለውጥ የማድረግ ፍላጎት አላት።
የግብጽ አዲሱ የትብብር ርዕይ ኡጋንዳን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን፣ ካሜሮንን፣ ኬንያን፣ ደቡብ ሱዳንን፣ ማዕከላዊ ሪፐብሊክ አፍሪካን፣ ጂቡቲን፣ ኤርትራን፣ ታንዛንያን፣ ሶማሊያን እና ናይጄርያን ያካተተ ነው።
ግብጽ በአዲሱ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲዋ በማንኛውም የአገር ውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት አትፈልግም።
ሉዓላዊነታቸውን አልያም የግዛት አንድነታቸውን የሚጎዳ ጉዳይ ላይ ላለመሳተፍ አቋም ይዛለች።
ከዚያ ይልቅ ግጭቶችን በድርድር እና በትብብር እንዲፈቱ ለመስራት ትጥራለች።
ይህ ከግምት ገብቶ ግብጽ በሶማሊያ የሚኖራት ተሳትፎ ሲመዘን፣ ኢትዮጵያ ሶማሊያ የግዛቷ አንድ አካል አድርጋ ከምትቆጥራት ሶማሊላንድ ጋር በኤደን ባህረ ሰላጤ ላይ የባሕር በር የማግኘት እና በምትኩ ዕውቅና የመስጠት ስምምነትን መፈረሟን ተከትሎ ለቀረበላት የድጋፍ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ልትፈልግ ትችላለች።
አንዳንድ ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ አካላት ኢትዮጵያ “በቀይ ባሕር ላይ ያላት ፍላጎት” የባሕር ኃይል በሶማሌላንድ እስከ መገንባት ከደረሰ፣ የግብጽ ዋነኛ የንግድ መስመር እና የገቢ ምንጭ የሆነው ስዊዝ ካናል ላይ አደጋ ሊኖረው ይችላል የሚል ስጋት ቀስቅሷል ይላሉ።
ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ፕሬዝደንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ለሥራ ጉብኝት ግብጽ ከነበሩት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሐሙድ ጋር በመሆን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አገራቸው ሶማሊያ ደኅንነት ላይ የሚደቀን ማንኛውንም አደጋ አትፈቅድም ሲሉ የተናገሩ ሲሆን ይህም በበርካቶች ለኢትዮጵያ የተላለፈ መልዕክት ተደርጎ ተወስዷል።
በቀጣዩ ወራትም በሶማሊያ እና በግብጽ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያደገ ሲሆን፣ ይህም ከካይሮ ሞቃዲሹ የቀጥታ የአየር በረራ በመጀመር፤ ግብጽ በሞቃዲሹ ኤምባሲዋን በመክፈት ታይቷል።
የሶማሊያ ፕሬዝደንት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ካይሮ ባቀኑበት ወቅትም ሁለቱ አገራት ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል።
የኢትዮጵያ ስጋት
ኢትዮጵያ ወታደሮችን እንዲሁም የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ሁለት የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች በሞቃዲሾ የአየር ማረፊያ ደርሰዋል መባሉን ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት "ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ስትል ከስሳለች።
ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እርምጃ የሚወስዱ ሌሎች ተዋናዮች አሉ ብላለች።
የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ መሥርያ ቤቱ ባወጣው በዚህ መግለጫ ላይ የአፍሪካ ቀንድን ለማተራመስ እርምጃ እየወሰዱ ነው ያለቻቸውን "ሌሎች ተዋናዮች"ም ሆነ የውጭ ኃይሎች ማንነት እንዲሁም በምን መንገድ እንደሆነ አልገለጸችም።
ግብጽ በበኩሏ በሶማሊያ ስለሚኖራት ወታደራዊ ተሳትፎ ወይንም የጦር አውሮፕላኖቿ ሞቃዶሾ ማረፋቸውን ተከትሎ በወጣው መግለጫ ዙርያ ያለችው አንዳችም ነገር የለም።
ኢትየጵያ “ለሶማሊያና ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ መስፈን፣ ለጋራ ዕድገት እና በክልሉ ያሉ ሕዝቦች መካከል ያለውን የጠበቀ የእርስ በርስ ትስስር ይበልጥ እንዲጎለብት ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን” ያስታወሰው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፣ አክሎም“ቀደም ሲል አህጉራዊ እና አለምአቀፋዊ አሸባሪ ቡድኖች ላይ የተገኘውን አበረታች ውጤት አደጋ ላይ የሚጥሉና የሚቀለብሱ ድርጊቶች ኢትዮጵያ አትታገስም” ብሏል።
የአፍሪካ ህብረት ሽግግር ተልዕኮን የሚተካው የሰላም ተልዕኮ አወቃቀር ሁኔታ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ላይ አዲስ ስጋት ይዞ መምጣቱን ይህም ለአገሪቱ አሳሳቢ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዚሁ መግለጫው ጠቁሟል።
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ወታደሮቿን ያዋጣችበት የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) በመጪው ዓመት ጥር ወር ተልዕኮውን አጠናቆ የጸጥታ ሁኔታውን የሶማሊያ መንግሥት እንዲረከብ እንደሚደረግ ተገልጿል።
ሆኖም በሶማሊያ የጸጥታ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ከአስር ሺህ የማይበልጡ ወታደሮች ያሉበት የሰላም አስከባሪዎች ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ባለበት እንደሚሰማራ ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ስምምነት አዲሱ ተልዕኮ ከሚወሰንበት፣ ከሰኔ መጨረሻ በፊት ካልሰረዘች በአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ሥር እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት የሰፈሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንደሚወጡ እንደሚደረግ የአገሪቱ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሑሴን አሊ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ መውጣታቸው አገሪቷን ለጂሃዲስቶች ጥቃት እንድትጋለጥ ያደርጋል የሚሉ ቀጣናውን በቅርበት የሚከታተሉ ባለሙያዎች አሉ።
የግብጽ ወታደሮች በሶማሊያ ምሥራቃዊ ድንበር ላይ እንዲሰማሩ መታቀዱ ለኢትዮጵያ ስጋት መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
በዚህም የተነሳ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ከሚመራው የሰላም አስከባሪ ኃይል ውጪ ጦሯ በሶማሊያ እንዲቆይ ልታደርግ ትችላለች በማለት ይህ እድል ዝግ አለመሆኑንም አስምረውበታል።

በቀጠናው ውጥረት ለመንገሱ ማሳያ የሆኑት ነገሮች
የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ መታየታቸውን ተከትሎ ከሶማሊያ ተገንጥላ ራስ ገዝ አስተዳደር የሆነችው ሶማሊላንድ የግብጽ ጦር በሶማሊያ ተሰማርቶ የቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ ሲወድቅ በዝምታ አልመለከትም ብላለች።
የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በቅርቡ የግብጽ ጦር በሶማሊያ እንዲሰማራ መደረጉ ለሶማሊያ እና ለአጠቃላዩ የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ደኅንነት አሳሳቢ ነው ብሏል።
የሶማሊያ መንግሥት ከግብጽ ጋር የገባው ስምምነት ከሳውዝ ዌስት ግዛት ከተወከሉት የፓርላማ አባላትም ተቃውሞ ገጥሞታል።
በሳዌዝ ዌስት ግዛት ውስጥ የምትገኘው ሁዱር ከተማ ነዋሪዎች በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ውስጥ እያገለገሉ ላሉት የኢትዮጵያ ወታደሮች ድጋፋቸውን በመግለጽ ሰልፍ ማድረጋቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሰልፍ የወጡት ነዋሪዎች፤ በመጪው ዓመት ጥር ወር የሚጠናቀቀውን በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮን (አትሚስ) በሚተካው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ውስጥ የግብጽ ወታደሮች እንደሚሰማሩ መገለጹን እንደተቃወሙም ተዘግቧል።
በኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረው ውጥረት አይሎ ግብጽን ወደ ቀጠናው ካመጣ በኋላ ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ የሚያጠናክር ነው በተባለ መንገድ በልዩ መልዕክተኛ ደረጃ ለነበረው የሐርጌሳ ቆንስላ አምባሳደር ሾማለች።
አምባሳደር ተሾመ ሹንዴ ሐሚቶ ነሐሴ 23/2016 ዓ.ም. የሹመት ደብዳቤያቸውን ለራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ አቅርበዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩት ልዩ መልዕክተኛ በአምሳደር መተካታቸው በአዲስ አበባ እና ሐርጌሳ መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙት የበለጠ ያጠናክራል ተብሏል።
የግብጽ ጦር ማሰልጠኛ አማካሪ የሆኑት ሜጀር ጄነራል ናስር ሳሌም ለአረብ ዊክሊ ዜና ምንጭ የግብጽ እና ሶማሊያ ወዳጅነት ተከትሎ አገራቸው የወሰደቻቸውን እርምጃ ሲጠየቁ “ለኢትዮጵያ እርምጃ መልዕክት . . . “ በማለት ነበር ።
ግብጽ በአፍሪካ ቀንድ መከላከል የምትፈልገው ምንድን ነው?
ግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ዋነኛ ዓላማ በቀይ ባሕር እና በስዊዝ ካናል ላይ ያላትን ብሔራዊ ጥቅም መከላከል ነው።
እንዲሁም የውሃ ድርሻዋን ለማስጠበቅም ከአባይ ተፋሰስ አገራት ጋር እና ጎረቤቶቻቸው ጋር ያላትን መልካም ግንኙነት ማስቀጠል ትፈልጋለች።
የባሕር በር አልባዋ ኢትዮጵያ የንግድ መተላለፊያ ወደብ ለማግኘት እና የባሕር ኃይሏን ለማጠናከር ካላት ፍላጎት የተነሳ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ስምምነት ፈርማለች።
ይህ ስምምነት ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ደግሞ ግዙፍ ሕዝብ እና ምጣኔ ሀብት ያላት ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ሚና እንዲኖራት በማድረግ ተጨማሪ ኃይል ወደ መድረኩ ያመጣል።
የግብጹ አል አህራም ዋና አዘጋጅ ለአል አረቢያ አል ሀዳት ቲቪ እንደተናገረው ከሆነ የካይሮ እና ሞቃዲሹ ወዳጅነት ሁለቱ አገራት ካላቸው ታሪካዊ ግንኙነት አንጻር ተፈጥሯዊ እርምጃ ነው።
ምክንያቱም ግብጽ ቀይ ባሕር ላይ ካላት ብሔራዊ ጥቅም አንጻር መሆኑን ጠቅሶ ሁቲዎች በሚፈጽሙት ጥቃት ብቻ ግብጽ “ከስዊዝ ካናል የምታገኘውን ገቢ 50 በመቶ ወይም 5 ቢሊዮን ዶላር ያህል አጥታለች” ብሏል።
በተመሳሳይ የብሔራዊ ደኅንነት ተንታኝ የሆነው ሞሀመድ አብደል ዋሂድ ለኒው አረብ ድረ ገጽ የግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ላይ ያላት ስትራቴጂ ብሔራዊ ደኅንነትን “ቀድሞ የመከላከል” መሆኑን በመግለጽ ቀጠናው ላይ ያሏት ወሳኝ አጋሮች “ የደኅንነት አደጋ የተጋረጠባቸው” መሆኑን ይዘረዝራል።
እነዚህ የግብጽ አጋር የተባሉ አገራት “ተገንጣይነት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል፣ በደቡባዊ ቀይ ባሕር ላይ ዓለም አቀፍ ፉክክር እና ውጥረት” እንደተጋረጠባቸውም ይዘረዝራል።
ሆኖም ግብጽ በእነዚህ ወዳጅ አገራት ያላት ተሳትፎ "ብሔራዊ ጥቅሟን መከላከል" ብቻ ነው ብለው የማያምኑ ኢትዮጵያውያን አሉ።
የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ያሲን አህመድ ለግብጽ ድረገጽ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ የግብጽ ዓላማ “በቀጠናው ያላትን የጸጥታ ሚና ማሳደግ እና በቀጠናው ኢትዮጵያን መፎካከር” መሆኑን ይናገራሉ።
በቀጠናው የተፈጠረው ውጥረት ሊባባስ ይችላል?
ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የተፈራረመችውን የመግባቢያ ስምምነት ካልሰረዘች በአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ሥር እንዲሁም በሁለትዮሽ ስምምነት የሰፈሩት ሁሉም የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ከአገሪቱ እንደሚወጡ እንደሚደረግ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አስጠንቅቀዋል።
ኢትዮጵያ በአትሚስ ሥር 3 ሺህ ያህል ወታደሮችን እንዲሁም ከሶማሊያ ጋር ባላት የሁለትዮሽ ስምምነት እስከ 7 ሺህ የሚሆኑ ወታደሮችን አሰማርታለች።
የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር “ለሶማሊያና ለአካባቢው ሰላምና ፀጥታ መስፈን፣ ለጋራ ዕድገት እና በክልሉ ያሉ ሕዝቦች መካከል ያለውን የጠበቀ የእርስ በርስ ትስስር ይበልጥ እንዲጎለብት ያላሰለሰ ጥረት ስታደርግ መቆየቷን” በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።
ምንም እንኳ የሶማሊያ መንግሥት ፍላጎት ባይሆንም ኢትዮጵያ ጦሯን በሶማሊያ ውስጥ ልታቆይ የምትችልበት እድል የተዘጋ አለመሆኑን የሶማሊያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ይናገራሉ።
እንደነዚህ የፖለቲካ ተንታኞች አመለካከት ኢትዮጵያ ከሶማላሌላንድ ጋር የተፈራረመችው ስምምነት ባይኖር እንኳ በሶማሊያ ውስጥ በቀላሉ ወታደሮቿን ለማቆየት የሚያስችል አጋርነት መፍጠር ትችላለች።
ከስድስቱ የሶማሌ ፌደራል ግዛቶች አንዱ የሆነው የሶማሌ ሳውዝ ዌስት ግዛት በቀጠናው የኢትዮጵያ ወታደሮች መኖርን እንደሚደግፍ ቀደም ብሎ አስታውቆ ነበር።
የፑንትላንድ ግዛት በበኩሉ ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ሲሆን ይህም በቀላሉ ኢትዮጵያ ልትጠቀምበት እንደምትችል ተጠቅሷል።
የግብጽ ጦር በሶማሊያ መሰማራት በአገሪቱ ውስጥ ለሚገኙ ሁሉ ውጥረትን የሚያባብስ ሲሆን በቀጠናው በቀጥታ አልያም በተዘዋዋሪ ለሚደረግ ጦርነት ሰበብ ይሆናል ተብሎ ተሰግቷል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቀይ ባሕር ላይ ያላት ተሳትፎ የጨመረው ቱርክ እኤአ በ2017 ከሱዳን ባሕር ዳርቻ ወጣ ብሎ በሚገኘው በሱአኪን ወደብ ላይ የጦር ሰፈር ለመገንባት የሚያስችላትን የ99 ዓመት ሊዝ ተፈራርማለች።
ከሶማሊያም ጋር በመከላከያ እና ደኅንነት ዙርያ ለመስራት የሚያስችላት ዘርፈ ብዙ ስምምነት ተፈራርማለች።
ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን ለማደራደር እየሞከረች የምትገኘው ቱርክ፣ ከግብጽ ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ሲሆን ይህም በቀጠናው ያለውን ውጥረት ለማርገብ ያግዝ ይሆናል ተብሏል።
ቱርክ በስዊዝ ካናል ላይ የኢንዱስትሪ ዞን ለመገንባት የሚያስችላትን ስምምነት ከካይሮ ጋር የተፈራረመች ሲሆን፣ ይህም ሁለቱ አገራት በቀይ ባሕር ላይ ያላቸውን ብሔራዊ ፍላጎት በጋራ እንዲያስጠብቁ ሊያደርግ ይችላል።
ባለፉት ዓመታት የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ያጠናከረች ሲሆን አንዳንዶች አቡዳቢ ኢትዮጵያን ወደ አፍሪካ መግብያ በር አድርጋ እደምትቆጥራት ይናገራሉ።
ይህንንም ቀይ ባሕርን ከአረብ ባሕር ጋር የሚያገናኘው ባብ አል ማንደብ ላይ ያላትን ፍላጎት እና ተጽዕኖ ለማሳደግ ትጠቀምበታለች ሲሉ ተንታኞች ትንበያቸውን ያስቀምጣሉ።
የኢትዮጵያን ጦር ትደግፋለች የምትባለው ዩኤኢ በግብጽ በጥርጣሬ የምትታይ አገር ናት።












