ግብጽ የውሃ ድርሻዬን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን እወስዳለሁ ስትል ለጸጥታው ምክር ቤት አሳወቀች

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali
ግብጽ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየገነባች ባለችው ግድብ ምክንያት የውሃ ደኅንነቴን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን እርምጃ የመውሰድ መብት አለኝ አለች።
ካይሮ ይህን ያለችው በአዲሱ የውጭ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስትሩ ዶ/ር ባዳረ አብዱላቲ በኩል ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በላከችው ደብዳቤ ነው።
ሚኒስትሩ ትናንት እሁድ ነሐሴ 26/2016 ዓ.ም. ለጸጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በጻፉት ደብዳቤ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ላይ የያዘችውን የተናጠል ፖሊሲ ግብጽ ሙሉ በሙሉ አትቀበልም ብለዋል።
ግብጽ ይህን ጠንከር ያለ ደብዳቤ ለጸጥታው ምክር ቤት የላከችው ጦሯን በሶማሊያ በማሰማራቷ ምክንያት በአፍሪካ ቀንድ አዲስ ውጥረት ከተፈጠረ በኋላ ነው።
በቅርቡ ካይሮ እና ሞቃዲሹ የደረሱትን ወታደራዊ ስምምነት ተከትሎ ግብጽ በሶማሊያ ወታደሮቿን ማሰማራቷ ተዘግቧል።
ይህን ተከትሎ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የግብጽ ጦር በሶማሊያ እንዲሰማራ መደረጉ ለሶማሊያ እና ለአጠቃላዩ የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት እና ደኅንነት አሳሳቢ ነው ማለታቸው ይታወሳል።
ወታደሮችን እና የጦር መሳሪያዎችን የጫኑ ሁለት የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች ሞቃዲሹ ከደረሱ በኋላ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የሶማሊያ መንግሥት "ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ኃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ማለቱ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ፤ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር የሚያስገኝላትን ስምምነት ከተፈራረመች በኋላ በአዲስ አበባ እና ሞቃዲሹ መካከል የነበረው ወዳጅነት እጅጉን ሻክሯል።
የአዲስ አበባ እና የሐርጌሳ ስምምነት ሉዓላዊነቴን እና የግዛት አንድነቴን የሚጥስ ነው ስትል የቆየችው ሶማሊያ አዲስ አጋር ፍለጋ ፊቷን ወደ ካይሮ ካዞረች ሰንበትበት ብላለች።
ሰኔ 2016 ዓ.ም. ማብቂያ ላይ የአገሪቱን የውጪ ጉዳይ እና የመስኖ ሚኒስቴር በጣምራነት እንዲመሩ የተሾሙት ዶ/ር ባዳር አብዱላቲ፤ ለጸጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቅርቡ አምስተኛው ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መካሄዱን ይፋ አድርገዋል ብለዋል።
ሚኒስትሩ ይህን ይበሉ እንጂ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 3ኛ እና 4ኛ ተርባይኖች ሥራ መጀመራቸውን፤ በዚህም ተጨማሪ 2800 ሜ/ኪ ውሃ በሰከንድ ማፍሰስ በመጀመራቸው ለታችኛው የተፋሰስ አገራት መልካም ዜና ነው ከማለት ውጪ የአምስተኛው ዙር ውሃ ሙሌት ስለመደረጉ በይፋ ያሉት ነገር የለም።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “በዚህ ዓመት የአባይ ወንዝ ውሃን የተወሰነ ክፍል በመያዝ የኮንክሪት ግንባታ ስለማጠናቀቅ መግለጻቸው ጨርሶ በግብጽ ተቀባይነት የለውም።” ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Abiy Ahmed Ali
ከዚህ በተጨማሪም ዶ/ር ባደር አቡዱላቲ በደብዳቤያቸው ኢትዮጵያ አምስተኛውን ዙር የውሃ ሙሌት ያካሄደችው የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎች እና ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ እአአ 2015 ላይ የተፈራረሙትን የመርሆች ስምምነት እንዲሁም የጸጥታው ምክር ቤት 2021 ላይ ያወጣውን ፕሬዝዳንታዊ መግለጫ በመጣስ ነው ብለዋል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደብዳቤ “እነዚህ የኢትዮጵያ ድርጊቶች አገሪቱ ከጎረቤት አገራት ጋር የምትፈጥረው ችግር ማሳያ ናቸው” ያለ ሲሆን፣ ከግድቡ ግንባታ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የምትወስዳቸው የተናጠል እርምጃዎች የግዛቱን መረጋጋት አደጋ ላይ ይጥላል ብሏል።
“ግብጽ ሕልውናዋን ለመከላከል እና የሕዝቦቿን ጥቅም ለማስከበር በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር መሠረት ሁሉንም እርምጃዎች ለመውሰድ ዝግጁ ናት” ብለዋል።
በቅርቡ የግብጽ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚመሩት “የግብጽ ጠቅላይ ኮሚቴ ለናይል” የተባለው ኮሚቴ ለስብሰባ መቀመጡን የገለጹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ ኮሚቴው ግብጽ የውሃ ድርሻዋን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ የያዘችውን አቋም አረጋግጧል ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ ድርድር
ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ለበርካታ ዓመታት በሕዳሴ ግንባታ እና ኦፕሬሽን ዙሪያ ሲያደርጉት የቆዩት ድርድር ያለ ስምምነት መበተኑ ይታወሳል።
በግድቡ ዙሪያ ግብጽ እና ኢትዮጵያ ባላቸው መሠረታዊ ልዩነቶች ምክንያት ከስምምነት መድረስ አልተቻለም። ሁለቱ አገራት ለድርድሩ አለመሳካት አንዳቸው ሌላኛቸውን ተጠያቂ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ግንባታው ከተጀመረ 13 ዓመታት ያስቆጠረውን ግዙፍ ግድብን ውሃ መሙላት ከመጀመሯ በፊት አስገዳጅ ስምምነት ላይ መደረስ አለበት በማለት ግብጽ እና ሱዳን ሲወተውቱ ቆይተዋል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከአባይ ውሃ ፍትሐዊ የሆነ ድርሻዬን መጠቀም አለብኝ በማለት አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረስ ግድቡ ውሃ እንዲይዝ ስታደርግ ቆይታለች።












