በለንደን ከተካሄደው የአደባባይ ድግስ በኋላ ታዋቂው ትውልደ ኤርትራዊን ጨምሮ ሁለት ሰዎች ተገደሉ

ሙሴ እምነቱ እና ቼር ማክሲሜን

የፎቶው ባለመብት, Met Police

የምስሉ መግለጫ, ሙሴ እምነቱ እና ቼር ማክሲሜን

በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ ከሚሳተፍበት የለንደኑ ኖቲንግ ሊል ካርኒቫል በኋላ ትውልደ ኤርትራዊውን ታዋቂ ሼፍን ጨምሮ ሁለት ሰዎች ተገደሉ።

በተለያዩ አጋማጣሚዎች የተገደሉት ሁለቱ ሰዎች የ32 ዓመቷ ቼር ማክሲሜን እና ኤርትራ የተወለደው የ41 ዓመቱ እውቁ ሼፍ ሙሴ እምነቱ ናቸው።

ፖሊስ እንዳለው ቼር ባለፈው ሳምንት እሁድ ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም. በካርኒቫሉ ላይ ከሦስት ዓመት ሴት ልጇ ጋር ሳለች በስለት ከተወጋች በኋላ ትናንት ቅዳሜ ነሐሴ 25 ሕይወቷ አልፏል።

ሙሴ እምነቱ ደግሞ በፌስቲቫሉ የመጨረሻ ቀን ሰኞ ነሐሴ 20 እራሱን ስቶ ከተገኘ በኋላ በደረሰበት ጉዳት አርብ ነሐሴ 24 በሆስፒታል ሳለ ሕይወቱ አልፏል።

የፖሊስ አዛዥ የሆኑት ቻርሜይን ብሬንያህ የሁለቱ ግለሰቦች ሞት “ለሁለቱም ቤተሰቦች ከፍተኛ ሐዘን ፈጥሯል” ካሉ በኋላ ፖሊስ የሞት ምክንያቱን በግድያ ወንጀል እየመረመረ መሆኑን ተናግረዋል።

የኖቲንግ ሂል ካርኒቫል አዘጋጆች እንዲሁ በሁለቱ ሰዎች ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

ቼር የተባለችው ሴት በስለት የተወጋችው ጸብ ላይ የነበሩ ሰዎችን ለመገላገል መሃል ከባች በኋላ መሆኑ ተገልጿል።

ከሚሰራበት ዱባይ ለጉብኝት በመጣበት ሕይወቱ ያለፈው ሙሴ እምነቱ ደግሞ ለሕልፈት የዳረገው በጭንቅላቱ ላይ የደረሰ ጉዳት መሆኑን የፖሊስ መግለጫ አመልክቷል።

ሙሴ ሰኞ ምሽት እራሱን ስቶ ከተገኘ በኋላ ሆስፒታል ቢወሰድም ሕይወቱን ማትረፍ አለመቻሉን የገለጹት የፖሊስ ባልደረባ፤ “የሙሴ እምነቱ የሞት ዜና በለንደን፣ ዱባይ፣ ስዊድን እና ኤርትራ ላሉ ወዳጅ ዘመዶቹ ካበድ ድንጋጤ እና ሐዘን ፈጥሯል” ብለዋል።

ሙሴ በዱባይ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬትስ በሚገኝ ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በአባልነት የሚሰባሰቡበት ‘አርት ክለብ’ ዋና ምግብ አብሳይ ሆኖ ይሰራ ነበር።

በኤርትራ ተወልዶ ስዊድን ያደገው ሙሴ በበርካታ የዓለም ክፍሎች ተዘዋውሮ የሰራ፤ ከዚህ ቀደም ጎርደን ራምሴይ እና ማርከስ ዌሪንግ ከተባሉት ዝነኛ ሼፎች ጋር ጭምር አብሮ መስራት የቻለ ዋና ሼፍ ነበር።

በኖሪንግ ሂል ፌስቲቫል የካረቢያን አገራት ባሕል እና አርት ይከበራል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኖሪንግ ሂል ፌስቲቫል የካረቢያን አገራት ባሕል እና አርት ይከበራል።

በሁለቱ ሰዎች ግድያ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

በቼር ሞት የ20 ዓመት ወጣት በግድያ ክስ ተመስርቶበታል። ከሙሴ ሞት ጋር በተያያዘ ደግሞ አንድ የ31 ዓመት ሰው ሆነ ብሎ በአካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረስ በሚል ክስ ቀርቦበት ፍርድ ቤት ቀርቧል።

የሁለቱ ሰዎች ሕልፈተን ተከትሎ የለንደን ከተማ ከንቲባ ሳዲቅ ካሃን እንዲሁም የዩናትድ ኪንግደም የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ያቨት ኩፐር ሐዘናቸውን ገልጸው ጥቃቶቹን አውግዘዋል።

ኖቲንግ ሂል ፌስቲቫል የካረቢያን አገራት ባሕል እና አርት የሚከበርበት ከእአአ 1960ዎቹ ጀምሮ በለንደን ሲከበር የቆየ የአደባባይ ላይ የሙዚቃ ድግስ ነው።